በጋዛ ከተኩስ አቁም ፋታው በኋላ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ

ለሰባት ቀናት የቆየውን የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ15 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 6 ሺህ ህጻናት መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የጋዛ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ሊያበቃ ቢቃረብም ለማራዘም ጥረት እየተደረገ ነው

    ዛሬ ሰኞ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ለአራት ቀናት የተደረሰው ጦርነት ጋብ የማድረግ ስምምነት የሚያበቃበት ዕለት ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተኩስ አቁሙ እንዲራዘም ግፊት እያደረገ ነው።

    ባለፉት ሦስት ቀናት ሐማስ ከእስራኤል አግቶ ከወሰዳቸው ሰዎች መካከል የለቀቀ ሲሆን እስራኤል ደግሞ በእስር ቤቶቿ ውስጥ የነበሩ በርካታ ፍልስጤማውያንን ፈትታለች።

    ከዚህም ባሻገር ለሳምንታት በእስራኤል ጥቃት ምክንያት በመሠረታዊ አቅርቦቶች እጦት ሲሰቃዩ ለቆዩት የጋዛ ነዋሪዎች ሰብዓዊ እርዳታ እና ነዳጅ መግባት ችሏል።

    ይህ ለቀናት የቆየው ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ዛሬ ሌሊት ከማብቃቱ በፊት እንዲራዘም ጥረት እየተደረገ ነው። የኔቶው ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ እና የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ጥሪ ካቀረቡት መካከል ናቸው።

    የመጀመሪያው ስምምነት እንዲደረስ ወሳኝ ሚና የነበራት ኳታር፣ ግብፅ፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ስፔን፤ እስራኤል እና ሐማስ ጋዛ ውስጥ የደረሱት ጊዜያዊ ተኩስ አቁሙ እንዲራዘም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የፍልስጤም ብሔራዊ ባለሥልጣን ሪያድ አል-ማሊኪ ተናግረዋል።

    የግብፅ የደኅንነት ምንጮች ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ጦርነት የቆመበት ፋታ በቀናት ለማራዘም የሚደረገው ጥረት ወደ ስምምነት እየተጠጋ መሆኑን አመልክተዋል።

    ሐማስ የተኩስ አቁሙ እንዲራዘም እና ተጨማሪ ታጋቾችን ለመልቀቅ ፍላጎት እንዳለው ያሳወቀ ሲሆን፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁም ስምምነቱ እንዲራዘም የማድረግ ዕድል እንዳለ ገልጸው፣ ነገር ግን ከስምምነቱ ማብቃት በኋላ በጋዛ ውስጥ ሠራዊታቸው የሚያካሂደው ዘመቻ በሙሉ ኃይል እንደሚጀመር ተናግረዋል።

  2. እስካሁን ስንት ታጋቾች እና እስረኞች ተለቀቁ?

    በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው የእስረኞች እና የታጋቾች ልውውጥ ስምምነት የውስብስብ እና ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ነው።

    በድርድሩ በርካታ አካላት ታሳትፈዋል። በዚህም እስካሁን 58 ታጋቾች ነጻ የወጡ ሲሆን ከአርብ ዕለት ጀምሮ 117 ፍልስጥኤማውያን እስረኞች ተለቀዋል።

    ዛሬ ሰኞ እኩለ ሌሊት ላይ በሚያበቃው የእስራኤል እና የሐማስ ስምምነት መሠረት 50 እስራኤላውያን ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ በምላሹ 150 ፍልስጥኤማውያን ከእስር ይፈታሉ።

    ለመሆኑ ቁጥሮቹ ለምን ተለያዩ? ስለተለቀቁ ሰዎች ቁጥር እስካሁን የምናውቀው ምንድን ነው?

    • በእስራኤል እና በሐማስ ስምምነት መሠረት እስካሁን በጋዛ ታግተው የነበሩ 39 እስራኤላውያን ተለቀዋል።
    • በእስረኞች እና በታጋቾች ልውውጡ በእስራኤል እስር ቤት ታስረው የነበሩ 117 ፍልስጥኤማውያን ከእስር ተፈተዋል።
    • ሌላ ሮኒ ክሪቮይ የተባለ ሩሲያዊ-እስራኤላዊ ታጋችም እሑድ ዕለት በሐማስ ተለቋል። ሆኖም ታጋቹ የተለቀቀው በሦስት ፍልስጤማውያን እስረኞች ለውጥ አይደለም።
    • ከሐማስ ጋር በተደረገ ሌላ ድርድርም በተመሳሳይ ቀን በሐማስ ታግተው የነበሩ አንድ የፍሊፒንስ ዜጋ እና 17 የታይላንድ ዜጎች ተለቀዋል።

    ይህ ስምምነት አርብ ዕለት ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ በፊት ደግሞ ሦስት እስራኤላዊ ታጋቾች የተለቀቁ ሲሆን፣ አራተኛው በእስራኤል ጦር አማካኝነት ነጻ መውጣት ችሎ ነበር።

    መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈፀመውን ድንበር ዘለል ጥቃት ተከትሎ በአጠቃላይ ወደ 240 የሚጠጉ ሰዎች በጋዛ ታግተዋል ተብሎ ይታመናል።

  3. የእስራኤል ወታደርን ሕይወት የታደገው ኤርትራዊ ጥገኝነት ጠያቂ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ተሰጠው

  4. አራተኛ ቀኑን በያዘው የተኩስ አቁም ፋታ የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮች

    • በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ አራተኛ ቀኑን ይዟል። በስምምነቱ መሰረት የመጨረሻው ቀንም ነው ተብሏል። በዛሬው ዕለትም ሐማስ እና እስራኤል ተጨማሪ የታጋቾቸ እና የእስረኞች ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
    • በሐማስ ከተለቀቁት እስራኤላዊ ታጋቾች መካከል የ84 ዓመቷ የዕድሜ ባለጸጋ በከፋ ህመም ላይ እንደሆኑ ተነግሯል። እናቱ ህይወታቸውን ለማቆየት እየታገሉ እንደሆነ ልጃቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።
    • የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ፋታው ሊራዘም እንደሚችል ተናግረው ነገር እስራኤል በጋዛ እያደረገችው ያለው ዘመቻ "ሐማስን እስኪያጠፋ" ድረስ እንደሚቀጥልም አጽንኦት ሰጥተዋል።
    • የተኩስ አቁም ፋታውን ለማራዘም በኳታር እና ግብጽ አሸማጋይነት አማካኝነት ንግግሮች መቀጠላቸውም እየተዘገበ ይገኛል።
    • በትናንትናው ዕለት ሐማስ 14 እስራኤላውያንና ሶስት የውጭ አገር ዜጎች በአጠቃላይ 17 ታጋቾችን ሲለቅ በልውውጡ ደግሞ እስራኤል 39 ህጻናትና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።
  5. ከተለቀቁት እስራኤላውያን ታጋቾች መካከል የአራት ዓመት ህጻን እንዳለችበት ተገለጸ

  6. የፍልስጤም ታዳጊዎች መለቀቅ እና ስምምነቱ ሊራዘም ይችላል መባሉ የጫረው ተስፋ

  7. በአሜሪካ ሦስት ፍልስጤማውያን ተማሪዎች በተከፈተባቸው ተኩስ ቆሰሉ

  8. ሐማስ የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ፋታው መራዘሙን እንደሚሻ አስታወቀ

    ሐማስ በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል የተባለው የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ፋታው መራዘሙን እንደሚሻ አስታውቋል።

    በኳታር አሸማጋይነት የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ በዛሬው ዕለት የሚጠናቀቅ ሲሆን ስለመራዘሙ የተባለ ነገር የለም።

    በነዚህም ቀናት ሐማስ በሶስት ዙሮች 58 ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን እስራኤል በበኩሏ 117 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች። ሐማስ ባወጣው መግለጫ "የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ፋታው እንዲራዘም እንፈልጋን። በሰብዓዊ የተኩሱ አቁሙ መሰረትም የሚለቀቁ ታጋቾችም ቁጥርም ይጨምራል" ብሏል።

    በኳታር እየተካሄደ ያለውን ድርድር በቅርበት እየተከታተሉ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን በበኩላቸው ሐማስ የተኩስ አቁም ፋታውን ከ2 እስከ 4 ቀናት ለማራዘም ፍላጎት እንዳለው ለአሸማጋዮቹ ማስታወቁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በነዚህም ቀናት ከ20-40 እስራኤውያን እስረኞች ሊፈቱ እንደሚችሉም ተጠቁሟል።

    በአራቱ ቀናት የተኩስ አቁም ፋታው ሐማስ 50 ታጋቾችን ለመልቀቅ እንዲሁም እስራኤል 150 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመፍታት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

    የእስራኤል መንግሥት የሐማስን መግለጫ አስመልክቶ ያለው ነገር የለም።

    ሆኖም ከዚህ ቀደም እስራኤል በየዕለቱ 10 እስራኤላዊ ታጋቾች የሚለቀቁ ከሆነ ፋታው በአንድ ቀን እንደሚራዘም አስታውቃለች። ሆኖም የተኩስ አቁም ፋታው ጊዜያዊ እንደሆነ እና ጦርነቱም ሐማስ ከምድረ ገጽ እስኪጠፋ ድረስ ይቀጥላል ብላለች።

  9. በሶስት ዙሮች ሐማስ 58 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል 117 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታች

    በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰውን የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ ሐማስ 58 ታጋቾችን በሶስት ዙሮች ለቋል። እስራኤል በበኩሏ 117 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።

    በትናንትናው ዕለት ሐማስ 14 እስራኤላውያን እና ሶስት የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን እስራኤል ደግሞ 39 እስረኞችን ፈታለች።

    በአራቱ ቀናት የተኩስ አቁም ፋታው ሐማስ 50 ታጋቾችን ለመልቀቅ እንዲሁም እስራኤል 150 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመፈታት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

    በኳታር አሸማጋይነት የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታው በዛሬው ዕለት የሚጠናቀቅ ሲሆን ስለመራዘሙ የተባለ ነገር የለም።

    ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡብ እስራኤል የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ 1 200 ሰዎች ሲገደሉ ከ200 በላይ ሰዎች ታግተዋል። እስራኤል በበኩሏ በጋዛ ሰርጥ ላይ በፈጸመችው የማያባራ የአየር ጥቃት ከ14 ሺህ 500 በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

  10. የጋዛ ነዋሪዎች በተኩስ አቁም ፋታው የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን እየፈለጉ ነው

  11. በዌስት ባንክ በአንድ ምሸት ሰባት ፍልስጤማውያን በእስራኤል ኃይል ተገድለዋል ተባለ

    እስራኤል በኃይል ይዛት በምትገኘው ዌስት ባንክ ግዛት በትናንትናው ምሽት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት አስታወቁ።

    ከነዚህም ውስጥ አምስቱ የተገደሉት በጄኒን ሲሆን የእስራኤል ጦር በነሐሴ ወር በተፈጸመ ጥቃት ተሳትፏል የተባለ ግለሰብን በቁጥጥር ስር ለማዋል በፈጸመው ወረራ መሆኑን የዜና ኤጀንሲዎች ዘግበዋል።

    ጄኒን ከተማ "ከየአቅጣጫው በእስራኤል ኃይል እንደተተኮሰባትም" የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ ዘግቧል።

    ጦሩ "የመንግሥት ሆስፒታል እንዲሁም አለም አቀፉ የቀይ ጨረቃ ዋና መስሪያ ቤትን" በከበባ ውስጥ ማስገባቱንም አክሏልል።

    የእስራኤል ቡልዶዘሮች በጄኒን በርካታ ጎዳናዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም ዋፋ በተጨማሪ ዘግቧል።

  12. ሐማስ 41 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል 78 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታች

    በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረገውን የቀናት የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ ሐማስ 41 ታጋቾችን በሁለት ዙር ለቋል።

    ከነዚህም ውስጥ 26ቱ እስራኤላውያን ሲሆኑ 14ቱ የታይላንድ ዜጎች እንዲሁም አንድ የፊሊፒንስ ዜጋ ተካተውበታል።

    እስራኤል በበኩሏ 78 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈትታለች። እስራኤል ትናንት ማምሻውን በሶስተኛ ዙር የሚለቀቁ ታጋቾችን ዝርዝር ማግኘቷን አስታውቃለች።

    በኳታር አሸማጋይነት በተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ መሰረት ሁለቱ አካላት እስረኞች እና ታጋቾች የሚቀያየሩ ይሆናል።

    በዛሬው ዕለትም እስራኤል በእስር ቤቶቿ ካሰረቻቸው መካከል ህጻናት እና ሴቶችን የምትፈታ ይሆናል። በአጠቃላይም በአራቱ ቀናት ሐማስ 50 ታጋቾችን የሚለቅ ሲሆን እስራኤል ደግሞ 150 እሰስኞችን የምትፈታ ይሆናል።

  13. በሐማስ ታግተው የነበሩ ተጨማሪ እስራኤላውያን ከሰዓታት ጭንቅ በኋላ ተለቀቁ

  14. እስራኤል ከፈታቻቸው ፍልስጤማውያን አንዷ

    የሐማስ እና እስራኤል ስምምነትን ተከትሎ ከእስራኤል እስር ቤት ከተፈቱት ፍልስጤማውያን መካከል ኢስራ ጃቢስ አንዷ ናት።

    በዌስት ባንክ በሚገኝ የፍተሻ ኬላ 1.5 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ባለው አውራ ጎዳና ላይ መኪናዋ በተበላበሸበት ወቅት ነው በቁጥጥር ስር የዋለችው።

    ይህም በአውሮፓውያኖቹ 2015 ሲሆን ለስምንት ዓመታት ያህልም በእስር ቆይታለች። መኪናዋ የተበላሸበት ምክንያት አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል።

    እስራኤል በመኪና ላይ የቦምብ ጥቃት ለማድረስ የተቃጣ ነው ስትል የአረብ ሚዲያዎች በበኩላቸው የመኪናዋ ሞተር አልሰራም በማለቱ ምክንያት መኪናዋ መቆሙን ተናግረዋል። የሞተሩ ብልሽትም በመኪናዋ ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ሆኗል።

    ኢስራም ፊቷን ጨምሮ በእሳት ቃጠሎው ጉዳት ደርሶባታል። በእስራኤል 11 ዓመት ተፈርዶባት ስምንት ዓመት በእስር ቆይታለች።

    ባለፈው ዓመትም በእሳት ቃጠሎው የደረሰባትን ጉዳት ተከትሎም አፍንጫዋ ላይ የቀዶ ህክምና ለማድረግ ለእስራኤል ማረሚያ ቤቶች ጥያቄ ብታቀርብም ውድቅ ተደርጎባታል።

    ከእስር ከተፈታች በኋላም በአሁኑ ወቅት የ15 ዓመት ልጇ የሆነውን ሙአታሲምንም አቅፋ ታይታለች። እስር ቤት ስትገባ ልጇ የስምንት ዓመት ህጻን ነበር።

  15. ከእስር የተፈታችው ፍልስጤማዊት ቤቷ ከመሄዷ በፊት የአጎቷን ልጅ መቃብር ስፍራ መጎብኘት አለብኝ አለች

    የሐማስ እና የእስራኤልን የቀናት የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ ከተፈቱት ውስጥ አንዷ ኑርሃን አዋድ ናት።

    በ15 ዓመቷ ለእስር ስትዳረግም አብሯት የነበረው የአጎቷ ልጅ በእስራኤል ወታደር ተገደለ። ኑርሃን አዋድ ከስምንት አመታት እስር ቆይታ በኋላም ቤቷ ከመሄዷ በፊት የአጎቷን ልጅ የመቃብር ስፍራም መጎብኘት እንዳለባት ተናግራለች።

    በአሁኑ ወቅት የ23 ዓመት ዕድሜ ያላት ኑርሃን ከእስር ስትፈታም በቃላንዲያ የሚገኙ ቤተሰቦቿም ደስታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ታይተዋል።

    እሷም እየሮጠች ቤተሰቦቿን አቅፋቸዋለች። በአውሮፓውያኑ 2015 ስትታሰርም ሶስት ጊዜ በጥይት ተመትታለች።

    በወቅቱ 15 ዓመቷ የነበረችው ኑርሃን በእየሩሳሌም የስለት ጥቃት ዘመቻ አካል ናት በሚልም ተጠርጥራ ነው ተብሏል። አስር ዓመት የተፈረደባት ሲሆን ከዚህም ውስጥ ስምንት ዓመት በእስር ቆይታለች።

  16. ሶስተኛ ቀኑን በያዘው የእስራኤል- ሐማስ የተኩስ አቁም ፋታ የተከሰቱ ዓብይ ነገሮች

    በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የተደረሰውን የቀናት የተኩስ አቁም ፋታ ስምምነት ተከትሎ ታጋቾች እና እስረኞች እየተለቀቁ ይገኛሉ ።

    • እስራኤል በእስር ቤቶቿ ውስጥ ካሉት በሺዎች ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መካከል በትናንትናው ዕለት ተጨማሪ 39 እስረኞችን መልቀቋን አረጋግጣለች። የተለቀቁት ፍልስጤማውያን እስረኞች ሁሉም ሴቶች ወይም እድሜያቸው 18 እና ከዚያ በታች የሆኑ ህጻናት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ሶስት እስር ቤቶች ታስረው እንደነበር ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
    • 39ኙ በምስራቅ እየሩሳሌም ወይም እስራኤል በኃይል ይዛው ባለችው ዌስት ባንክ ወደሚገኘው ቤታቸውም እየተመለሱ ይገኛሉ።
    • በአራቱ ቀናት የተኩስ አቁም ሐማስ 50 ታጋቾችን ለመልቀቅ የተስማማ ሲሆን እስራኤል ደግሞ በእስር ቤቶቿ ያሉ 150 ሴቶችን እና ህጻናትን ትፈታለች።
    • ትናንት፣ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ስድስት ሴቶች እና ሰባት ህጻናት በአጠቃላይ 13 እስራኤላውያን ታጋቾች እስራኤል መድረሳቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
    • ሐማስ እስራኤል ለአራት ቀናት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ፋታ እንደጣሰች ያስታወቀ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የታጋቾች መለቀቅ ለሰዓታት ዘግይቶ ነበር። እስራኤል ክሱን አስተባብላለች።
    • ታጋቾቹ በልዩ ኃይሎች ታጅበው የህክምና ምርመራ የሚደረግላቸው ሲሆን ከዚያም በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚቀላቀሉ ይሆናል።
    • ከእስራኤላውያኑ በተጨማሪ አራት የታይላንድ ዜጎችም በትናንትናው ዕለት ተለቀዋል።
    • በኳታር አሸማጋይነት መሰረት የተደረገውን የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ እስረኞች እና ታጋቾች በሁለተኛ ዙር ተለቀዋል።
    • የእስራኤል ባለስልጣናት 195 ታጋቾች በጋዛ እንደሚገኙ ያስታወቁ ሲሆን የፍልስጤም ባለስልጣናት በበኩላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እና ህጻናት በእስራኤል እስር ቤቶች ይገኛሉ ብለዋል።
  17. የሕዝባቸውን ሰቆቃ በርቀት ሆነው እየተጋፈጡ ያሉት ፍልስጤማዊ አሜሪካውያን

  18. 42 ፍልስጤማውያን ነጻ እንደሚወጡ ተገለጸ

    በሁለተኛው ቀን የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ 42 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል እስር ቤት እንደሚለቀቁ የተገለጸ ሲሆን ሐማስ ደግሞ 14 እስራኤላውያንን ከእገታ ነጻ ያወጣል ተብሏል።

    የፍልስጤም የታራማዊች ማኅበር ዛሬ ነጻ ይወጣሉ የተባሉ የ42 ፍልስጤማውያን ዝርዝር ከእስራኤል መንግሥት እንደደረሰው አስታውቋል።

    ማኅበሩ ከእነዚህ መካከል 18ቱ ሴቶች ሲሆኑ 24ቱ ደግሞ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው ብሏል።

    ፍልስጤማውያኑ እና እስራኤላውያኑ የሚለቀቁበት ሰዓት አልተገለጸም።

  19. ከእገታ ነጻ የወጡ ሰዎች ጤና ‘ጥሩ’ መሆኑን ያከማቸው ሆስፒታል አስታወቀ

    ትናንት ከሐማስ እገታ ነጻ ከወጣቱ 13 እስራኤላውያን መካከል ለ8ቱ የሕክምና አገልግሎት የሰጠው ሆስፒታል የታካሚዎቹ ጤና ‘ጥሩ’ የሚባል መሆኑን ገለጸ።

    በቴል አቪቭ የሚገኘው ሽናይደር ሆስፒታል የተቀበልኳቸው 4 ሕጻናት እና 4 ሴቶች ጤና ጥሩ ነው ብሏል።

    ሆስፒታሉ ጨምሮም ከእገታ ነጻ የወጡት ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ለእነርሱ ተብሎ በተዘጋጀ የሆስፒታሉ ክፍል ውስጥ በጤና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትል እየደረገላቸው እንደሆነ ገልጿል።

    ትናንት ሐማስ ለ7 ሳምንታት ያክል አግቶ ያቆያቸውን 13 እስራኤላውያንን፣ 10 የታይላንድ እና 1 የፊሊፒንስ ዜጋ መልቀቁ ይታወሳል።

  20. ዛሬ ተጨማሪ ታጋቾች ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃለ

    እስራኤል ዛሬ ተጨማሪ 13 ታጋቾች ይለቀቃሉ ብዬ እጠብቃለሁ አለች።

    በአንጻሩ እስራኤል ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ፍልስጤማውያንን ከእስር ቤት እንደምትለቅ ይጠበቃል።

    ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳ ቁስ የጫኑ ከባድ የደረቅ ጭንት መኪኖች ወደ ጋዛ ለመግባት ግብጽ ድንበር ላይ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

    ምንም እንኳ በኳታር አደራዳሪነት በሐማስ እና እስራኤል መካከል ለጦርነቱ ፋታ ለመስጠት ከስምምነት ቢደረስም በጋዛ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ እንዳለ እየተገለጸ ነው።

    ነዳጅ፣ ምግብ፣ ውሃ እና የሕክምና መሳሪያዎች ከፍተኛ እጥረት አለ።

    ትናንት አርብ ወደ 200 የሚጠጉ ከባድ ተሸከርካሪዎች ጋዛ ደርሰው ነበር ይህም ከመስከረም 26 በኋላ ትልቁ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።