ኬንያውያን ከብሪታኒያ ነጻ ከወጡ በኋላ አምስተኛውን የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ባለፈው ሳምንት ድምጽ ሰጥተው አሸናፊውን ለማወቅ በጉጉት እየጠበቁ ነው።
የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በተቀራረበ ውጤት ለፕሬዝዳንትነት ሲፎካከሩ ቆይተዋል።
የ77 ዓመቱ ራይላ አዲንጋ አራት ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው ሳይቀናቸው ቢቀርም፣ ተስፋ ሳይቆርጡ አሁን ለአምስተኛ ጊዜ እየተወዳደሩ ነው።
አባታቸው ጭምር ፖለቲከኛ እና ባለሥልጣን የነበሩት ኦዲንጋ፣ ከአስር ዓመት በፊት ግን አወዛጋቢውን ምርጫ ተከትሎ የኬንያ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን አገለግለዋል። ለዓመታት ሲደግፏቸው የቆዩ በርካታ ደጋፊዎች ያሏቸው ኦዲንጋ አድናቂዎቻቸው “ባባ” (አባት) በሚል ይጠሯቸዋል።
ከድሃ ቤተሰብ እንደመጡ የሚነገርላቸው ዊሊያም ሩቶ ባለፉት አስር ዓመታት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ከኡሁሩ ኬንያታ ጋር በሥልጣን ላይ ቆይተዋል።
ሩቶ ‘ኬንያ ኩዋንዛ’ ወይም ኬንያ ትቅደም በሚል መርኅ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ እና የሥራ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሕዝብ ሕይወት መቀየር ዋነኛ ትኩረታቸው ነው።
የ55 ዓመቱ ዊሊያም ሩቶ በመጀመሪያ የሰሜን ኤልዶሬት ምርጫ ክልል የሕዝብ እንደራሴ በመሆን ወደ ዋነኛው የአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ መጥተዋል።
ከአሁኑ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ ጋር በመወዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሁለተኛው የአገሪቱ ኃያል ፖለቲከኛ ሆነው ከርመዋል።
ሩቶ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከፕሬዝዳንት ኬንያ ጋር የነበራቸው አንድንት ላልቶ ወደ አለመግባባት ከተሻገረ በኋላ፣ ለምርጫው በራሳቸው ፓርቲ አማካይነት ሲዘጋጁ ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንት ኬንያታም ከምክትላቸው ይልቅ ተቃዋሚውን ራይላ ኦዲንጋን በመደገፍ እንዲመረጡ ሲያግዙ ነበር። በጠባብ የውጤት ልዩነት ሲፎካከሩ የቆዩት የሁለቱ ዕጩዎች ውጤት ዛሬ ይፋ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።