የኬንያ አምስተኛው ፕሬዝዳንት፡ ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ

የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን በ2022 ብሔራዊ ምርጫ ለአስር ዓመታት አገሪቱን በምክትል ፕሬዝዳንትንት የመሩት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ ቀጣይ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን አሳውቋል። ዊሊያም ሩቶ ከባድ ፉክክር በተካሄደበት ምርጫ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ጋር ተወዳድረው ነው በጠባብ የድምጽ ልዩነት ፕሬዝዳንታዊውን ምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ የተደረገው። ሩቶ ላላፉት 10 ዓመታት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የሰሩ ሲሆን፣ ከፕሬዝዳንት ኬንያታ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ እንዲተኳቸው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የራይላ ደጋፊዎች መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ እየገለጹ ነው

    ተቃውሞ የሚገልጹ የራይላ ደጋፊዎች

    በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ፉክክር በጠባብ የድምጽ ልዩነት የተሸነፉት የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች መንገድ በመዝጋት ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።

    ዊሊያም ሩቶ አምስተኛው የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው መገለጹን ተከትሎ፣ የኦዲንጋ ደጋፊዎች በተለያዩ ስፍራዎች ቁጣቸውን በአደባባይ እየገለጹ ይገኛሉ።

    ኦዲንጋ አምስት ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው አምስቱንም ጊዜ አልተሳካላቸውም።

    የዘንድሮው ሙከራ የመጨረሻቸው ይሆናል ብለው ደጋፊዎቻቸው ይሰጋሉ።

    ራይላ ጠንካራ የደጋፊ መሠረት ባላቸው እንደ ኪሱሙ ባሉ ግዛቶች ውስጥ ቁጣ እየተስተጋባ ይገኛል።

    አንዳንዶች መንገድ ዘግተዋል።

    ቀደም ሲል እድማ በታኝ ፖሊሶች ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መሰማራታቸው ተገልጿል።

  2. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዊሊያም ሩቶን እንኳን ደስ አለዎ አሉ

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነው ለተመረጡት ዊሊያም ሩቶን የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላለፉ።

    “እንኳን ደስ አለዎ። መልካሙን ሁሉ እመኝልዎታለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

    ጨምረውም በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙርያ ሁለቱ መሪዎች በጋራ እንደሚሠሩ እንደሚጠብቁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።

    የኬንያምርጫ ኮሚሽን በ2022 ብሔራዊ ምርጫ ለአስር ዓመታት አገሪቱን በምክትል ፕሬዝዳንትነት የመሩት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ ቀጣይ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን አሳውቋል።

  3. የኬንያ አምስተኛው ፕሬዝዳንት፡ ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ

    ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ

    የፎቶው ባለመብት, ቢቢሲ

    የምስሉ መግለጫ, ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ

    የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን በ2022 ብሔራዊ ምርጫ ለአስር ዓመታት አገሪቱን በምክትል ፕሬዝዳንትንት የመሩት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ ቀጣይ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን አሳውቋል።

    ዊሊያም ሩቶ ከባድ ፉክክር በተካሄደበት ምርጫ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ጋር ተወዳድረው ነው በጠባብ የድምጽ ልዩነት ፕሬዝዳንታዊውን ምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ የተደረገው።

    ውጤቱን በማሳወቅ በኩል ውዝግብ የተነሳ ሲሆን አራት የምርጫ ኮሚሽን አባላት የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውጤት አያያዝ “ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ፣ ውጤቱን በኃላፊነት ለመውሰድ አንችልም” በማለት እራሳቸውን አግልለዋል።

    የ55 ዓመቱ ሩቶ መመረጣቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ባደረጉት ንግግር በሁሉም መስኮች አገራቸውን ወደ ፊት ለማራመድ ተባብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

    ሩቶ ላላፉት 10 ዓመታት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የሰሩ ሲሆን፣ ከፕሬዝዳንት ኬንያታ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ እንዲተኳቸው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

    ዊሊያም ሩቶ የፕሬዝዳንታዊው ምርጫ አሸናፊነታቸው የታወጀው ከአጠቃላዩ መራጭ የ50.49 በመቶውን ድምጽ በማግኘታቸው ነው።

    ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ 48.85 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።

  4. የምርጫ ኮሚሽኑ በውጤት አገላላጹ ላይ ለሁለት ተከፈለ

    ተቃውሟቸውን የተገለጹት የኮሚሽኑ አባላት
    የምስሉ መግለጫ, ተቃውሟቸውን የተገለጹት የኮሚሽኑ አባላት

    ባለፈው ማክሰኞ በኬንያ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ዛሬ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ይፋ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ጊዜ አለመግባባት እና ውዝግብ ተፈጥሯል።

    የፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ውጤት ያሳውቃሉ ተብለው በሚጠበቁት የምርጫ ኮሚሽን ባለሥልጣንት መካከል ክፍፍል ተፈጥሯል።

    በዚህም መሠረት አራት የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በይፋ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውጤት ከሚነገርበት ማዕከል ውጪ መሃል ናይሮቢ በሚገኘው ሴሬና ሆቴል ውስጥ ሂደቱን ጥያቄ ላይ በሚጥል ሁኔታ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

    በዚህም ከሰባቱ ኮሚሽነሮች አራቱ በሰጡት መግለጫ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውጤት አያያዝ “ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ፣ ውጤቱን በኃላፊነት ለመውሰድ አንችልም” በማለት ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንታዊው ውጤት በኮሚሽነሩ ዋፉላ ቺቡካቲ አማካይነት ይፋ ይደረግበታል በተባለው የቦማስ ማዕከል ውዝግብና ግብግብ ተፈጥሮ ታይቷል።

    ውጤቱ ዛሬ ይገለጽ እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም በማዕከሉ የታደሙት ሰዎች እየተጠባበቁ ነው።

    ውጥረቱ ከአዳራሹ ባሻገርም በተለያዩ የኬንያ አካባቢዎች ነግሷል።

  5. ራይላ ኦዲንጋ የት ናቸው?

    የምርጫው ውጤት ይፋ የሚደረግበት ማዕከል አሁን
    የምስሉ መግለጫ, የምርጫው ውጤት ይፋ የሚደረግበት ማዕከል አሁን

    የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ለማሳወቅ እየተዘጋጀ ባላበት በአሁኑ ወቅት የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊ ኬንያውያን ዕጯቸው የት አሉ እያሉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየጠየቁ ነው።

    ዋነኛው ተፎካካሪ ዊሊያም ሩቶን ጨምሮ በምርጫው ለፕሬዳንትንት የተፎካከሩት ዕጩዎች ውጤቱ በሚነገርበት አዳራሽ ውስጥ የተገኙ ሲሆን ኦዲንጋ ግን እስካሁን አልታዩም። ለዚህም ነው ደጋፊዎቻቸው ኦዲንጋ የት አሉ የሚሉት።

    በውጤት ማሳወቂያው ስፍራ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከእናታቸው ጋር መድረሳቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ኣሰውቀዋል።

    ቢቢሲ ከኦዲንጋ ጠባቂዎች እንደተረዳው ዕጩው ፕሬዝዳንት አሁንም ከውጤት ማሳወቂያው ማዕከል ርቀው ነው ያሉት።

    ኦዲንጋ ወደ ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይደርሳሉ ተብሎ አይጠበቅም።

    ቢሆንም ግን ውጤቱን ለማሳወቅ ተወዳዳሪዎች መገኘት የግድ አይደለም፤ ራይላ ኦዲንጋ በተወዳደሩባቸው ባለፉት አራት የምርጫ ውድድሮች የውጤት ማሳወቂ ሥነ ሥርዓት ላይ አልተገኙም።

  6. የኬንያ ምርጫ ውጤት ሊሆን የሚችለው

    ኬንያውያን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ውጤት በጉጉት እየጠበቁ ነው
    የምስሉ መግለጫ, ኬንያውያን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ውጤት በጉጉት እየጠበቁ ነው

    የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ከአገሪቱ ባሻገር በአብዛኞቹ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

    አስካሁን ጥርት ባለ የድምጽ ብልጫ ያሸነፈ ዕጩ የለም። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ከሚከተሉት ውጤቶች አንዱን ያሳውቃል፡

    • የዊሊያም ሩቶን አሸናፊነት

    • የራይላ ኦዲንጋን አሸናፊነት

    • ሁለተኛ ዙር ምርጫ

    ሁለተኛ ዙር ምጫው እንዲካሄድ የሚወሰነው ሁለቱ ተፎካካሪ ዕጩዎች ከተሰጠው ድምጽ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ድምጽን ማግኘት ካልቻሉ ነው።

    የምርጫው ውጤት ዛሬ በኮሚሽኑ ከታወጀ በኋላ ቅሬታ ያላቸው ዕጩዎች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውስድ ሊቃወሙት ይችላሉ። ለዚህም በቀጣዮቹ ሰባት ቀናት ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በውጤቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ።

  7. ከውጤት በፊት አደባባይ የወጡት የራይላ ደጋፊዎች

    የራይላ ደጋፊዎች ኪሱሙ ውስጥ
    የምስሉ መግለጫ, የራይላ ደጋፊዎች ኪሱሙ ውስጥ

    ኬንያውያን የሚደግፏቸው ዕጩዎች ምርጫውን ያሸንፋሉ ብለው ወደ ጎዳና በመውጣት ደስታቸውን መግለጽ ጀምረዋል።

    ራይላ ኦዲንጋ ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው በሚባለው የምዕራብ ኬንያ ግዛት በሆነችው ኪሱሙ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ወጥተዋል።

    ባለፈው ማክሰኞ በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ የሆነውን ዕጩ ለማሳወቅ የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓትን እየጠበቀ ነው።

    ነገር ግን ሁለቱ ዕጩዎች በተቀራረበ ውጤት እየተፎካከሩ በመሆናቸው አስካሁን በከፍተኛ የበላይነት አሸናፊ የሆነ ዕጩ የለም። ቢሆንም ግን ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እየመሩ ይገኛሉ።

    ኪሱሙ ውስጥ የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎችን የሚያሳዩ ፎቶዎች

    የራይላ ደጋፊዎች ኪሱሙ ውስጥ
    የምስሉ መግለጫ, የራይላ ደጋፊዎች ኪሱሙ ውስጥ
    የራይላ ደጋፊዎች ኪሱሙ ውስጥ
    የምስሉ መግለጫ, የራይላ ደጋፊዎች ኪሱሙ ውስጥ
    ፊሽካ እየሸጠ ያለ የራይላ ደጋፊ በኪሱሙ
    የምስሉ መግለጫ, ፊሽካ እየሸጠ ያለ የራይላ ደጋፊ በኪሱሙ
  8. የሩቶ ደጋፊዎች ፕሬዝዳንታዊ ውጤት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው

    የምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ደጋፊዎች
    የምስሉ መግለጫ, የምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ደጋፊዎች

    በምዕራብ ኬንያ በምትገኘው ኤልዶሬት ከተማ ነዋሪዎች የምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን በጉጉት እየጠበቁ ነው።

    ምንም እንኳ ሁለቱ ዕጩዎች እጅግ ተቀራራቢ ውጤት ቢያስመዘግቡም፤ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ሩቶ ያሸንፋሉ ብለው የሚጠብቁት ደጋፊዎች ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን በጭፈራ እየገለጹ ይገኛሉ።

    የምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ደጋፊዎች
    የምስሉ መግለጫ, የምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ደጋፊዎች
  9. የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ሊያሸንፉ ይችላሉ የተባሉት የቀድሞ የዶሮ ነጋዴ

    ዊሊያም ሩቶ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ

    ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ በአሁኑ ወቅት በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ ሁለተኛው ኃያል ሰው ናቸው።

    በዘንድሮ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ተፎካካሪያቸውን በጠበበ ውጤት እየመሩ ይገኛሉ።

    የቀድሞ የዶሮ ነጋዴ፤ የዛሬው ዕጩ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ማን ናቸው?

  10. አሁናዊ የድምጽ ቆጠራን ይመልከቱ

    ራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ
    የምስሉ መግለጫ, ራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ

    ሁለቱ የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች አንገተ ለአንገተ ተያይዘዋል።

    ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን ዛሬ ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. ከሰዓት 9 ሰዓት ላይ አሸናፊውን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

    በድምጽ ቆጠራ አሁን ላይ ማን እየመራ ይገኛል?

    አሁናዊ የድምጽ ቆጠራ ውጤቱን እየዚህ ይመልከቱ

  11. በአባታቸው ያልተሳካውን የፕሬዝዳንትነት መንበር የሚናፍቁት ራይላ

    ራይላ ኦዲንጋ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, ራይላ ኦዲንጋ

    ራይላ ኦዲንጋ በኬንያ ፖለቲካ ታዋቂ ከሆነ ቤተሰብ የተገኙ ናቸው።

    ለአስርት ዓመታት የዘለቀው የፖለቲካ ሕይወታቸው ግን ቤተ መንግሥት አላደረሳቸውም።

    የዘንድሮው ምርጫ ፕሬዝዳንት የመሆን እድላቸውን የሚያሳኩበት የመጨረሻው ዕድላቸው ነው።

  12. ዛሬ ውጤቱ በጉጉት የሚጠበቀው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ

    ዊሊያም ሩቶ እና ራይለ ኦዲንጋ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ዊሊያም ሩቶ (ግራ) እና ራይለ ኦዲንጋ (ቀኝ)

    ኬንያውያን ከብሪታኒያ ነጻ ከወጡ በኋላ አምስተኛውን የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ባለፈው ሳምንት ድምጽ ሰጥተው አሸናፊውን ለማወቅ በጉጉት እየጠበቁ ነው።

    የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በተቀራረበ ውጤት ለፕሬዝዳንትነት ሲፎካከሩ ቆይተዋል።

    የ77 ዓመቱ ራይላ አዲንጋ አራት ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው ሳይቀናቸው ቢቀርም፣ ተስፋ ሳይቆርጡ አሁን ለአምስተኛ ጊዜ እየተወዳደሩ ነው።

    አባታቸው ጭምር ፖለቲከኛ እና ባለሥልጣን የነበሩት ኦዲንጋ፣ ከአስር ዓመት በፊት ግን አወዛጋቢውን ምርጫ ተከትሎ የኬንያ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን አገለግለዋል። ለዓመታት ሲደግፏቸው የቆዩ በርካታ ደጋፊዎች ያሏቸው ኦዲንጋ አድናቂዎቻቸው “ባባ” (አባት) በሚል ይጠሯቸዋል።

    ከድሃ ቤተሰብ እንደመጡ የሚነገርላቸው ዊሊያም ሩቶ ባለፉት አስር ዓመታት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ከኡሁሩ ኬንያታ ጋር በሥልጣን ላይ ቆይተዋል።

    ሩቶ ‘ኬንያ ኩዋንዛ’ ወይም ኬንያ ትቅደም በሚል መርኅ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ እና የሥራ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሕዝብ ሕይወት መቀየር ዋነኛ ትኩረታቸው ነው።

    የ55 ዓመቱ ዊሊያም ሩቶ በመጀመሪያ የሰሜን ኤልዶሬት ምርጫ ክልል የሕዝብ እንደራሴ በመሆን ወደ ዋነኛው የአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ መጥተዋል።

    ከአሁኑ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ ጋር በመወዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሁለተኛው የአገሪቱ ኃያል ፖለቲከኛ ሆነው ከርመዋል።

    ሩቶ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከፕሬዝዳንት ኬንያ ጋር የነበራቸው አንድንት ላልቶ ወደ አለመግባባት ከተሻገረ በኋላ፣ ለምርጫው በራሳቸው ፓርቲ አማካይነት ሲዘጋጁ ቆይተዋል።

    ፕሬዝዳንት ኬንያታም ከምክትላቸው ይልቅ ተቃዋሚውን ራይላ ኦዲንጋን በመደገፍ እንዲመረጡ ሲያግዙ ነበር። በጠባብ የውጤት ልዩነት ሲፎካከሩ የቆዩት የሁለቱ ዕጩዎች ውጤት ዛሬ ይፋ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

  13. ዲፕሎማቶች የምርጫ ውጤት ለመስማት ተሰይመዋል

    ምዕራባውያን

    የፎቶው ባለመብት, @annesoy

    የኬንያ ፕሬዝዳታዊ ምርጫ ውጤት ለመስማት ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ቦማስ በሚባለው የድምጽ ቆጠራ ማዕከል ተገኝተዋል።

    ከምዕራባውያኑ በተጨማሪ ሁለቱ ዋነኛ ጥምር ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የምርጫ ውጤት ይፋ በሚደረግበት ቦታ ይገኛሉ።

    ዛሬ ምርጫ አስፈጻሚው አካል የምርጫ ውጤቱን እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።

  14. ውጤት በሚገለጽበት ቦታ ጠንካራ ጥበቃ እየተካሄደ ነው

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የድምጽ ቆጠራ ሲካሄድ በቆየበትና ዛሬ ውጤቱ ይገለጽበታል በተባለው ስፍራ ፖሊስ ጠንካራ የፀጥታ ጥበቃ እያደረገ ነው።

    የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ አን ሶይ በማዕከሉ አድማ በታኝ እና ፈጥኖ ደራሽ የፀጥታ ኃይሎች በስፋት መሰማራታቸውን ተመክታለች።

    የኬንያ ገለልተኛ የድንበር እና የምርጫ ኮሚሽን ከሳምንት በፊት የተካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ዛሬ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

  15. የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ዛሬ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል

    የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሁናዊ ውጤቶች
    የምስሉ መግለጫ, የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሁናዊ ውጤቶች

    በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ምክትል ፕሬዝዳንቱ በጠባብ ውጤት እየመሩ ሲሆን የምርጫ ውጤቱ ዛሬ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።

    ዛሬ ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. ረፋድ 5 ሰዓት 35 ደቂቃ ላይ የተገኘ የድምጽ ቆጠራ ውጤቶች እንደሚያሳየው ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ 50.7 በመቶ ድምጽ በማግኘት በጠባብ ልዩነት እየመሩ ይገኛሉ።

    ሥልጣን ላይ ባሉት ፕሬዝዳንት የሚደገፉት እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ ተመሳሳይ ሰዓት ላይ 48.7 ድምጽ ሰብስበዋል።

    የኬንያ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. አገሪቱን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራትን መሪ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።