የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ ባይደን እንደሚያሸንፉ ተነበዩ

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካ እስካሁን ባለው ከ99 ሚሊዮን አሜሪካውያን በላይ ቀድመው መምረጣቸው ተገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአሜሪካ ምርጫ፡ አሸናፊውን እስካሁን ያላወቅነው ለምንድነው?

    አሜሪካውያን እንዲህ ባለ መልኩ በንቃትና በከፍተኛ ቁጥር ሲሳተፉበት በቅርብ ዓመታት አልታየም በተባለው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፤ ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን አስስከመጨረሻዋ ሰዓት አንገት ላንገት ተናንቀዋል።

    ለመሆኑ በምርጫው አሸንፎ ፕሬዝደንት የሚሆነው ማነው?

    ይህ ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም። ጆ ባይደንም ሆነ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

    እንደውም በኮሮረናቫይረስ ምክንያት በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ የተባለ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በፖስታ በኩል ድምጻቸውን መላካቸውን ተከትሎ የምርጫ ቆጠራውና ይፋዊ ውጤቱ ከዚህ በኋላ ቀናት ሊፈጅ እንደሚችል ይገመታል።

  2. በአሜሪካ ፕሬዘዳንት የሚመረጠው እንዴት ነው?

    በአሜሪካ የምርጫ ሥርዓት አብላጫ ድምጽ ያገኘ ፕሬዝደንት ሆኖ ይመረጣል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ከ100 ሚሊዮን ድምጽ ሰጪዎች 60 ሚሊዮን ያገኘ እጩ ፕሬዝደንት ሆኖ የማይመረጥበት አጋጣሚ ይኖራል።

    ለምሳሌ እአአ 2016 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ፤ ሂላሪ ክሊንተን ከትራምፕ በበለጠ በርካታ ድምጽ አግኝተው ነበር። ይህ ግን የአሜሪካ ፕሬዝደንት አላደረጋቸውም።

    ለዚህ ምክንያቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የሚመረጠው ቀጥታ በመራጮች ሳይሆን በኤሌክቶራል ኮሌጅ ስለሆነ ነው።

    ኤሌክቶራል ኮሌጅ ምንድነው? ዝርዝሩን ይመልከቱ

  3. ዘር እና ጦር መሳሪያን በተመለከተ የባይደን እና ትራምፕ ልዩነት

    ዘርና ዘረኝነትን በተመለከተ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡-በአሜሪካ ፖሊስና ጸጥታ አስከባሪዎች ዘንድ መዋቅራዊ ዘረኝነት የለም ብለው ያምናሉ። ፖሊስ ማንቁርት ማነቁን ባይደግፉም ሕግን ማስከበር አለበት፣ ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ መፈቀድ የለበትም ይላሉ። ከፖሊስ ይልቅ ወንበዴዎች የሚሏቸውን ሰልፈኞች ማውገዝ ይመርጣሉ።

    ጆ ባይደን፡-ዘረኝነት በፖሊስና ጸጥታ አስከባሪዎች ዘንድ መዋቅራዊ ቅርጽ ይዟል ብለው ያምናሉ። ይህንንም ለማጥፋት እሰራለሁ ብለዋል።

    የጦር መሣሪያን በተመለከተ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- ትራምፕ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት 2ኛው ማሻሻያ ለአሜሪካዊያን የጦር መሣሪያ የመታጠቅ ሙሉ መብትን አጎናጽፏል ብለው የተለጠጠ ትርጓሜ ይሰጡታል።

    የጦር መሣሪያ ገዢዎች ላይ የኋላ ታሪክ ጥናት መደረግ አለበት ብለው ነበር፣ በ2019 ዓ.ም የደረሱ ግብታዊ ጥቃቶችን ተከትሎ። ሆኖም እስከዛሬ በዚህ ረገድ ተግባራዊ ያደረጉት አንዳችም ነገር የለም።

    ጆ ባይደን፡- በጦር መሣሪያ ረገድ ቁጥጥር ማጥበቅ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ የገዢዎችን የኋላ ታሪክ ማጥናትና መመዝገብ፣ አንድ ዜጋ በወር መግዛት የሚችለው የመሣሪያ ብዛት አንድ ብቻ እንዲሆን ማድረግ፣ ቸልተኛ የመሣሪያ አምራቾችና ሻጮችን ተጠያቂ ማድረግ፣ ለዜጎች መሸጥ የሚችሉ የጦር መሣሪያ ዓይነትም በሕግ እንዲወሰን ማድረግ ይፈልጋሉ።

  4. አሸናፊውን መለየት ያልተቻለባቸው ግዛቶች

    በጆርጂያ ድምጽ ተቆጥሮ አልተጠናቀቀም። እስከ እኩለ ለሊለት ድረስ ያልተቆጠረ 90 ሺህ ድምጽ አለ።

    በጆርጂያ ትራምፕ በ28ሺህ ድምጽ ባይደን እየመሩ ይገኛሉ።

    በኔቫዳም ፉክክሩ በእጅጉ የጠበበ ሆኗል። ጆ ባይደን በ7647 ድምጽ ልዩነት በጠባቡ እየመሩ ይገኛሉ።

    በአሪዞና ድምጽ ተቆጥሮ አልተጠናቀቀም። በዚህ ግዛት አሸናፊው ማን ሊሆን እንደሚችል መገመት አልተቻለም።

    ዊስኮንሲን በዚህ ግዛትም አሸናፊውን መለየት አልተቻለም። ጆ ባይደን በአሁኑ ሰአት በ20 ሺ 510 ድምጽ እየመሩ ነው።

    ፔንስለቬኒያ ዶናልድ ትራምፕ በፔንስልቬኒያ የነበራቸው የበላይነትም ቀስ በቀስ እየጠበበ መጥቷል። 90 በመቶ የሚሆነው ድምጽ በተቆጠረባት በዚች ግዛት ዶናልድ ትራምፕ በ164 ሺ 414 ድምጽ እየመሩ ይገኛሉ።

    ኖርዝ ካሮላይና 96 በመቶ የሚሆነው ድምጽ በተቆጠረባት ኖርዝ ካሮላይና ደግሞ እስከ ረቡዕ ከሰአት ድረስ ዶናልድ ትራምፕ በ76 ሺ 737 ድምጽ የበላይነት ወስደው ነበር።

  5. ባይደን መሪነታቸውን አጠናክረዋል

    እስካሁን 43 ግዛቶች ውጤት አሳውቀዋል።

    በዚህም መሠረት ባይደን 243 ለ 214 በሆነ ውጤት እየመሩ ይገኛሉ።

    ይህ ውጤት የተመዘገበው ጥቅምት 26 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ ነው።

    ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

  6. ፌስቡክ ትራምፕ ድል ማወጃቸውን ተከትሎ ማስጠንቂያ ሰጥቷል

    የአሜሪካው ፖሬዝደንት ምርጫው ሳይጠናቀቅ አሸናፊነታቸውን ማወጃቸውን ተከትሎ ተጠቃሚዎችን አስጠንቅቋል።

    የፌስቡክ ቃል አቀባይ ኤንቢሲ ለተሰኘው ጣቢያ 'ፖሬዝደንት ትራምፕ ምርጫው ሳይጠናቀቅ አሸንፍያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ፌስቡክና ኢንስታግራም ላይ ለተጠቃሚዎች ምርጫው ገና አልተጠናቀቀም የሚል ማስጠንቀቂያ ፅፈናል' ብለዋል።

    ወሳኝ በሚባሉት ፔንሲልቬኒያ፣ ሚሺጋንና ዊስኮንሲን እንዲሁም ሌሎች ግዛቶች አሁንም የሚሊዮኖች ድምፅ አልተቆጠረም።

    የምርጫ ጣቢያ ሰዎች ጠቅላላው ድምፅ ተቆጥሮ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ቀናት ሊወስድ ይችላል እያሉ ነው።

    ትዊተርም ቢሆን ልክ እንደፌስቡክ የአሜሪካ ምርጫን በተመለከተ አሳሳች መረጃ የሚያሰራጩ መልዕክቶችን አግዳለሁ ብሏል።

    ትራምፕ ከሰዓታት በፊት 'ምርጫውን ለመስረቅ እየሞከሩ ነው' ብለው ትዊተር ግድግዳቸው ላይ የለጠፉትን መልዕክት ሃሰተኛ ሊሆን ይችላል ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

  7. የአሜሪካ ምርጫ ውጤት የት ደረሰ?

    የአሜሪካ ምርጫ አሁን አልተገባደደም። ፕሬዝደንት ትራምፕና የዴሞክራት ፓርቲው ዕጩ ጆ ባይደን አንገት ለአንገት ተያይዘዋል።

    ዕጩዎች ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ለመግባት 270 ኢሌክቶራል ኮልጅ ድምፆች ያስፈልጓቸዋል።

    በአሁኑ ሰዓት ጆ ባይደን 224 ሲኖራቸው ፕሬዝደንት ትራምፕ ደግሞ 213 አላቸው።

    ወሳኝ ናቸው በሚባሉ ግዛቶች አሁንም ድምፅ ሙሉ በሙሉ አልተቆጠረም። በፔንሲልቬንያ፣ ሚሺጋን እና ዊስኮንሲን ጠቅላላ ውጤት ቀናት ሳይታወቅ ቀናት ሊቆጠሩ ይችላሉ እየተባለ ነው።

    ከጥቂት ሰዓታት በፊት መግለጫ የሰጡት ፕሬዝደንት ትራምፕ የምርጫው ውጤት ከመታወቁ በፊት ምርጫውን አሸንፈናል ሲሉ ተደምጠዋል። ምክትላቸው ማይክ ፔንስ ግን ለዘበትኛ አስተያየት ሰጥተዋል።

    ትራምፕ ምርጫውን የማያሸንፉ ከሆነ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊሄዱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

    ይህ የትራምፕ ንግግር ዴሞክራቶችን እንዲሁም ሪፐብሊካኖችን አስቆጥቷል።

    ጆ ባይደን በበኩላቸው በሰጡት መግለጫ 'በትክክለኛ መሥመር ላይ ነን፤ ምርጫውን ልናሸንፍ እንችላለን' ብለዋል።

    የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ በጣም በርካታ ሰዎች ድምፃቸውን የሰጡበት ነው ተብሏል።

    በዋሸንግተን ዲሲ ከተማ ትራምፕን የተቃወሙ ሰዎች መንገድ ላይ ድምፃቸውን ሲያሰሙ አምሽተዋል።

  8. የዓለም መገናኛ ብዙኃን ስለ ምርጫው ምን አሉ?

    በተለያዩ አገሮች የአሜሪካ ምርጫ በምን መልኩ ሽፋን እንደተሰጠው እንመልከት፡-

    ሩስያ፡ ምርጫው ከተገለጸበት መንገድ አንዱ “የአሜሪካ ምርጫ ውጥንቅጥ” ሲሆን ውጤቱ በጉጉት እየተጠበቀ መሆኑም ተጠቁሟል።

    ዩክሬን፡ ባይደን እና ትራምፕም ድል ተቀዳጅተው ደስታቸውን ለመግለጽ እየጠበቁ ነው ተብሏል።

    ላቲን አሜሪካ፡ ተፎካካሪዎቹ በጥቂት ነጥብ ልዩነት እየተፎካከሩ መሆኑ ተዘግቧል።

    ኢራን፡ “ምርጫውን ከውጪ ለሚመለከተው አስፈሪ ነው” የሚልና “የግጭት ስጋት አለ” የሚል መረጃ በብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ተላልፏል።

    ቻይና፡ ብሔራዊው የቻይና ጣቢያን ጨምሮ ሌሎቸም የእስያ መገናኛ ብዙሀን በአሜሪካ አለመረጋጋት ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል።ጀርመን፡ ጆ ባይደን ያሸንፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ትራምፕ የሚያሸንፉበት እድል ይኖር ይሆን? የሚል መረጃ ያለው ዘገባ ተነቧል።

    ፈረንሳይ፡ አንድ ጦማሪ “ከፉክክሮች ሁሉ የላቀ መሆኑን አሜሪካውያን ተገንዝበዋል” ብለው ጽፈዋል።

    ጣልያን፡ አሜሪካውያን በከፍተኛ ጉጉት ውጤቱን እየጠበቁ መሆኑ ተዘግቧል።

    ቱርክ፡ “ትራምፕ በድጋሚ እንደሚመረጡ ጽኑ እምነት አላቸው” የሚል እንዲሁም ባይደን የተጠበቀው ያህል ብቃት እንዳላሳዩ የሚጠቁም መረጃ ወጥቷል።

    ግብፅ፡ ምርጫው “ታሪካዊ” በሆነ ደረጃ ተሳታፊ እንዳለው ተነግሯል።

    ኬንያ፡ ከምርጫው በኋላ የግጭት ስጋት እንዳለ የሚጠቁም ካርቱን በ ዘ ስታር ጋዜጣ ላይ ታትሟል።

  9. ስለ አሜሪካ ምርጫ ምን ልንሰማ እንችላለን?

    በስተመጨረሻም እንዳይደርሱት የለ ጊዜው ደርሷል። የመጨረሻው መጨረሻ። በጉጉት የተጠበቀው የአሜሪካ ምርጫ ቁርጡ ሊለይለት ነው።

    የዘንድሮው ምርጫ እንደሌሎቹ ጊዜዎች አይደለም። ግራ አጋቢ ዜናዎች የተሰሙበት፣ የሚጠብቁት ቀርቶ የማይጠብቁት የሚሆንበት ነው ተብሏል።

    ድምጽ ተቆጥሮ ሲጠናቀቅ ከሚከለቱ አንዱን ልንሰማ እንችላለን፡ የአሜሪካ ምርጫ፡ ምን ዜና ልንሰማ እንችላለን?

  10. የትራምፕ ንግግር ሪፐብሊካኖችን አስቆጣ

    በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድምጾች ገና ባይቆጠሩም፤ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን “እንዳሸነፉ” የሚጠቁም ንግግር በዋይት ሀውስ አድርገዋል።

    ከፍተኛ የሪፐብሊካን መሪዎች እና ወግ አጥባቂ ተንታኞች፤ ፕሬዘዳንቱ በመረጃ ያልተደገፈ ንግግር ማድረጋቸው አሳሳቢ ነው ብለዋል።

    የቀድሞው የኒው ጀርዚ አረገ ገዢ እና የትራምፕ አማካሪ ክሪስ ክርስቲ፤ ንግግሩ ትክክለኛ አካሄድ አልነበረም ብለዋል።

    የቀድሞ የሪፐብሊካን የፔንሰልቬንያ ሴናተር ሪክ ሳንቶረም፤ “የፕሬዘዳንቱ ንግግር አሳስቦኛል። የምርጫ መጭበርበር የሚል ቃል መናገራቸው ተገቢ አይመስለኝም” ብለዋል።

    ወግ አጥባቂ ተንታኝና የትራምፕ ተቺ ቤን ሻፒሮ፤ የፕሬዘዳንቱ ትዊት “ኃላፊነት የጎደለው ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

  11. ትራምፕ “ጥሩ ውጤት እያስመዘገብን ነው” አሉ

    ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሁን በዋይት ሀውስ ባደረጉት ንግግር “እያሸነፍን ነው። ደስታችንን ለመግለጽ እየተዘጋጀን ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ በፍሎሪዳ ባስመዘገቡት ድል ደስታቸውን ገልጸዋል።

    “ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በብዙ ነጥብ አሸንፈናል” ብለዋል።

    ፔንስልቬንያ ውስጥም ተፎካካሪያቸው ጆ ባይደንን እየመሩ መሆኑን ተናግረዋል።

    ምርጫውን “እንዳሸነፉ” እና ምርጫው ግን “እንደትጨበረበረ” የተናገሩት ትራምፕ፤ ውጤቱን በተመለከተ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ገልጸዋል።

    በሌላ በኩል ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ብዙ ድምጽ አግኝተናል ግን መርጫውን ለማጭበርበር እየሞከሩ ነው” ብለው ትዊት ካደረጉ በኋላ፤ ትዊተር ጽሁፉን “አሳሳች” ሲል ፈርጆታል።

    የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ዳይሬክተር ቲም ሙታግ “ሲልከን ቫሊ የፕሬዘዳንቱን ድምጽ ለማፈን ሳንሱር ማድረጉን ቀጥሏል” ሲሉ የትዊተርን ፍረጃ ተቃውመዋል።

    ትራምፕ በተደጋጋሚ የምርጫው ተአማኒነት ላይ ጥያቄ ቢያነሱም እስካሁን አስተያየታቸውን የሚደግፍ ማስረጃ አላቀረቡም።

  12. ባይደን መልሰው መምራት ጀመሩ

    ባይደን በሚኒሶት ግዛት ማሸነፋቸውን ተከትሎ በጠባብ ልዩነት ምርጫውን ዳግም መምራት ጀምረዋል።

    ትራምፕ ቁልፍ በሆኑት ቴክሳስ እና ፍሎሪዳ ማሸነፋቸውን ተከትሎ መምራት ጀምረው ነበር።

    እስካሁን 40 ግዛቶች ውጤት አሳውቀዋል። በዚህም መሠረት ባይደን 220 ለ 213 በሆነ ውጤት ትራምፕን መምራት ጀምረዋል።

    ይህ ውጤት የተመዘገበው ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ47 ደቂቃ ላይ ነው።

    ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

  13. ትራምፕ ምርጫውን መምራት ጀመሩ

    ትራምፕ ቁልፍ በሆኑት ቴክሳስ እና ፍሎሪዳ ግዛቶች ማሸነፋቸውን ተከትሎ ምርጫውን መምራት ጀምረዋል።

    እስካሁን 39 ግዛቶች ውጤት አሳውቀዋል። በዚህም መሠረት ትራምፕ 212 ለ 209 በሆነ ውጤት መምራት ጀምረዋል።

    ይህ ውጤት የተመዘገበው ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ26 ደቂቃ ላይ ነው። ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

  14. ትራምፕ በፍሎሪዳ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ልዩነቱን አጠበቡ

    ዶናልድ ትራምፕ ቁልፍ በምትባለው ፍሎሪዳ ግዛት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ከጆ ባይደን ጋር ያላቸውን ልዩነት ማጥበብ ችለዋል።

    እስካሁን በ35 ግዛቶች ምርጫውን ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ተገምቷል።

    በዚህም መሠረት ጆ ባይደን 205 ለ 165 በሆነ ልዩነት እየመሩ ይገኛሉ። ይህ ውጤት የተመዘገበው 2ሰዓት ከ47 ደቂቃ ላይ ነው።

    ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

  15. 34 ግዛቶች ውጤት አሳውቀዋል

    ይህ ውጤት የተመዘገበው ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ ነው።

    በ34 ግዛቶች ምርጫውን ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ተገምቷል። በዚህም መሠረት ጆ ባይደን 205 ለ 136 በሆነ ልዩነት እየመሩ ይገኛሉ።

    ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

  16. የአሜሪካን ምርጫ በቀላሉ መረዳት የሚያስችሉ ነጥቦች

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ ዜጎች በተጨማሪ የበርካቶችን ሕይወት የሚነካ ስልጣን አለው።

    ጥቅምት 24 ደግሞ የምርጫ ካርዳቸውን የወሰዱ አሜሪካውያን ዶናልድ ትራምፕን አልያም ጆ ባይደንን ፕሬዝዳንታቸው አድርገው ለመምረጥ ድምጻቸውን የሚሰጡበት ቀን ነው።

    የምርጫው ውጤት ሁሉንም ይመለከታል።

    ምርጫውን ለመከታተል የሚያስችሏችሁን ቁልፍ ነጥቦች ማስፈንጠሪያውን በመጫን ታገኛላችሁ፡ የአሜሪካ ምርጫ፡ ምርጫውን በቀላሉ መረዳት የሚያስችሉ ነጥቦች

  17. ባይደን በሰፊ ልዩነት መምራት ጀመሩ

    ዲሞክራቱ እጩ ጆ ባይደን ሰፊ ሊባል በሚችል ልዩነት ትራምፕን መምራት ጀምረዋል።

    በ31 ግዛቶች ምርጫውን ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ተገምቷል።

    በዚህም መሠረት ባይደን 192 ለ 114 በሆነ ልዩነት እየመሩ ይገኛሉ።

    ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

    ይህ ውጤት የተመዘገበው 1፡20 ላይ ነው።

  18. በ25 ግዛቶች የምርጫው አሸናፊ ተገምቷል

    ከ50 የአሜሪካ ግዛቶች በ25 ግዛቶች የትኛው እጩ ሊያሸንፍ እንደሚችል ተገምቷል።

    በዚህም መሠረት ከተሰጠው ድምጽ ጆ ባይደን 118 ለ 99 ትራምፕን እየመሩ ይገኛሉ።ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

    ይህ ውጤት የተመዘገበው ንጋት 12:51 ላይ ነው።

  19. በ23 ግዛቶች ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ተገምቷል

    ከ50 የአሜሪካ ግዛቶች የ18 ግዛቶች የምርጫ ውጤት የትኛው እጩ ሊያሸንፍ እንደሚችል ተገምቷል።

    እስካሁን ያሉት የምርጫ ውጤቶች ጆ ባይደን ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ናቸው።

    ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

    ዶናልድ ትራምፕ በሚከተሉት ግዛቶች እንደሚያሸንፉ ተገምቷል።

    ሳውዝ ካሮላይና 9 ድምጽ

    አላባማ 9 ድምጽ

    ኖርዝ ዳኮታ 3

    ሳውዝ ዳኮታ 3

    አርካንሰስ

    ዌስት ቨርጂኒያ

    ቴኔሲ

    ኬንታኪ 8 ድምጽ

    ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ቁልፍ ግዛት በሆነችው ኒው ዮርክ ጨምሮ በሚከተሉት ግዛቶች ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

    ኮሎራዶ 9 ድምጽ

    ኮኔቲከት 7 ድምጽ

    ኒው ዮርክ 29 ድምጽ

    ኒው ጀርሲ 11 ድምጽ

    ቨርሞንት 3 ድምጽ

  20. ንጋት 12 ሰዓት ላይ ያለው የምርጫ ውጤት

    የአሜሪካ ምርጫ ውጤት ጥቅምት 25 ንጋት 12 ሰዓት ላይ።