በዓለማችን ከ500 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ሕይወታቸውን
እንዳጡ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ አመለከተ፡፡
ባለፈው ዓመት ቫይረሱ በቻይና ከጀመረ አንስቶም ከ10 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
ከእነዚህ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ግማሽ የሚሆነው ቁጥር የተመዘገበው በአሜሪካና በአውሮፓ ቢሆንም
አሁንም በአሜሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡
ቫይረሱ ደቡብ እስያንና አፍሪካንም እያጠቃ ነው፡፡
ወረርሽኙ አሁንም በርካታ የዓለም አገራትን እያዳረሰ ሲሆን ባለፉት ስድስት ቀናት ብቻ አንድ ሚሊየን አዲስ
ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
በአሜሪካ
እስካሁን 2.5 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 125 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህ ከሌሎች አገራት
ጋር ሲነጻጸርም ቁጥሩ ከፍተኛ ነው፡፡
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአሜሪካ በተለይ በደቡባዊ ግዛቷ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡
ይህንን
ተከትሎም የቴክሳስ፣ ፍሎሪዳና ሌሎች ግዛቶች ባለሥልጣናት በንግድ ተቋማት ላይ የተጣሉ ገደቦችን በድጋሚ እያጠበቁ ነው፡፡
ከበርካታ አገራት የሚወጡ መረጃዎች ጥቁሮችና እስያዊያን ከነጮች በበለጠ ለቫይረሱ የመጋለጥ እድላቸው
ከፍተኛ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡
በቫይረሱ በተያዙ
ሰዎች ቁጥር በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አገር ደግሞ ብራዚል ናት፡፡ በአገሪቷ በአጠቃላይ 1.3 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ
ሲያዙ የሟቾች ቁጥርም ከ57 ሺህ በላይ ሆኗል፡፡