በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ250 ሺህ በላይ ናሙናዎች ላይ ምርመራ ተደርጓል

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቻይናዋ ዉሃን ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ የዓለማችን ሕዝቦች 10 ሚሊየን መሻገሩን የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያሳያል። ይህ ወረርሽኝ በብዛት በአሜሪካና አውሮጳ ተስፋፍቶ ቢገኝም በአሁኑ ሰዓት ግን በአሜሪካ ከምን ግዜውም በላይ ስርጭቱ ጨምሯል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት ስድስት ቀናት ብቻ አንድ ሚሊየን ገደማ ሲሆን፣ በአፍሪካና በምዕራብ እስያ ይህ ቁጥር መጨመር እያሳየ ነው ተብሏል። በኢትዮጵያም ቢሆን የኮቪድ-19 በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በአግባቡ መከተል ራስንም ሆነ ሌሎችን ለመከላከል ሁለኛ መላ መሆኑን ባለሙያዎችና መንግሥት ዘወትር ይመክራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

  2. በኡጋንዳ የግል ትምህርት ቤቶች ለመምህራኖች የሚከፍሉት የላቸውም

    በኡጋንዳ የግል ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ላለፉት አራት ወራት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ደመወዝ አለመከፈላቸውን ተናገሩ።

    ትምህርት ቤቶቹ ለመምህራኖቻቸው የሚከፍሉትን ገንዘብ ያገኙ የነበረው ተማሪዎች ከሚከፍሉት ወርሃዊ ክፍያ ነበር።

    ነገር ግን የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለ በኋላ ትምህርት ቤቶች ከተማሪዎች ክፍያ መሰብሰብ አልቻሉም።

    በአገሪቱ ዋና ከተማ ካምፓላ ርእሰ መምህርት የሆነችው ሚሪየም ሱዛን ለቢቢሲ እንደተናገችው ለመምህሮቿ ከየካቲት ወር ጀምሮ ደመወዝ አልከፈለችም።

    ኡጋንዳ የኮሮና ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት በሚል የእንቅስቃሴ ገደብ በጣለችበት ወቅት የትኛውም ድርጅት ሠራተኞቹን እንዳያሰናብት አስጠንቅቃ ነበር።

    ነገር ግን ትምህርት ቤቶች መምህራኖቻቸውን ሳያሰናብቱ አቆይተው ያልተከፈለ ደመወዝ ማጠራቀም አልፈለጉም ነበር።

    አንዳንዶች ከመንግሥት መመሪያ ውጪ መምህራኖቹን ሲያሰናብቱ፣ ነገሮች ከተሻሻሉ ዳግም ለመቅጠር ቃል ገብተዋል።

    የግል ትምህርት ቤቶች መምህራን ማህበር እንደሚለው ከሆነ ትምህርት የሕዝብ አገልግሎት በመሆኑ መንግሥት የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንን ደመወዝ 50 በመቶ መክፈል ይኖርበታል።

    እንደ ትምህርት ሚኒስትሩ ከሆነ መንግሥት የመምህራኖችን ጩኸት ቸል አላለም። ይልቁኑስ ለንግድ ተቋማት የሚሰጠውን ድጎማ ለግል ትምህርት ቤቶችም ተግባራዊ እንደሚሆን ይናገራሉ።

    አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ግን ያላቸውን በመሸጥ ላይ ናቸው።

    በካምፓላ ብቻ ሰባት ትምህርት ቤቶች ንብረቶቻቸውን ለመሸጥ የገዢ ያለህ ሲሉ ማስታወቂያ አስነግረዋል።

    የድለላ ተቋማትም ደንበኞቻቸው ትምህርት ቤቱን ለመክፈት የተበደሩትን የባንክ ገንዘብ ለመክፈል እንደሚፈልጉ እየተናገሩ ነው

  3. አካላዊ ርቀቱን ባለመጠበቁ በኮሮና የተያዘው ግለሰብ መጸጸቱን በገለፀ ማግስት ሞተ

    አንድ በካሊፎርንያ የሚኖር ግለሰብ በኮሮናቫይረስ ከተያዘ በኋላ አካላዊ ርቀቱን ባለመጠበቁ ናለቫይረሱ በመጋለጡ መፀፀቱን በፌስቡክ ላይ በገለፀ ማግስት መሞቱ ተሰማ።

    "ይህ ቀልድ አይደለም" ሲል የጻፈው የ51 ዓመቱ ቶማስ ማሲያስ በቫይረሱ የተያዘው በሰኔ ወር 110 ኪሎ ሜትሮችን ርቆ ደቡባዊ ሎስ አንጀለስ በመሄድ ድግስ ላይ ከተሳተፈ በኋላ ነው።

    "መውጣት ካስፈለጋችሁ አካላዊ ርቀታችሁን ጠብቁ፤ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጉ" ሲል የፌስቡክ መልዕክቱ ላይ አስፍሯል።

    በዚሁ መልዕክቱ ላይ ቤተሰቡን በቫይረሱ በማስያዙ ይቅርታ ጠይቋል።

    "በእኔ ንዝህላልነት የእናቴንና የእህቶቼን እንዲሁም የቤተሰቦቼን ጤና ለአደጋ አጋልጫለሁ" ሲል ከጻፈ በኋላ "በጣም ልብ የሚሰብር አጋጣሚ ነው" ብሏል።

  4. የቦትስዋና ፕሬዝዳንት በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ራሳቸውን አገለሉ

    የቦትስዋና ፕሬዝዳንት ሞክግዌትሲ ማሲሲ አብረዋቸው የሚሰሩ ሰው በኮቪድ-19 መያዛቸውን ተከትሎ ራሳቸውን መለየታቸው ተገለፀ።

    ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው ሌሎች ለፕሬዝዳንቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በተጨማሪ ራሳቸውን አግልለው ተቀምጠዋል።

    መንግሥት ሰዎች ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራል።

    2.25 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ቦትስዋና እስካሁን ድረስ 227 ሰዎች ብቻ ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ ሲረጋገጥ አንድ ሰው ደግሞ በዚሁ ምክንያት ሞቷል።

  5. አፍሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት በሶስት ወር ውስጥ ብቻ 55 ቢሊዮን ዶላር ከቱሪዝሙ ዘርፍ አጥታለች

    የአፍሪካ ሕብረት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአፍሪካ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ከባድ ተጽዕኖ እንዳለው አስታወቀ።

    ሕብረቱ አፍሪካ በሶስት ወር ውስጥ ብቻ ከ 50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማጣቷንና የተወሰኑ አየር መንገዶችም ሊያንሰራሩ እንደማይችሉ ገልጿል።

    የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር አማኒ አቦ-ዘይድ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በነበራቸው ጉባዔ ላይ እንዳስታወቁት ቱሪዝም የአፍሪካ አንድ ቁልፍ የገቢ ዘርፍ እንደነበር ገልፀው አሁን ክን ክፉኛ መጎዳቱን ተናግረዋል።

    ". . .10 በመቶ የሆነው የአፍሪካ የነፍስ ወከፍ ገቢየሚገኘው ከቱሪዝም ነው። እንዲሁም ደግሞ ከዚያ ጋር ተያይዞ የአየር ትራንስፖርት"

    ካሉ በኋላ " 24 ሚሊየን አፍሪካውያን በቱሪዝምና በአየር ትራንስፖርት ላይ ተሰማርተዋል። እህም ማለት 24 ሚሊዮን አፍሪካውያን ቤተሰቦች በእነዚህ ዘርፍ ኣለይ ኑሯቸውን መሰረት አድርገዋል ማለት ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

    ስለዚህ አሉ ኮሚሽነሩ የኮሮናቫይረስ ተጽዕኖ ከባድ ነው ካሉ በኋላ "አንዳንዶች 55 ቢሊየን ዶላር ማጣታችንን ይገምታሉ በሶስት ወር ውስጥ ብቻ" ብለዋል።

  6. ሩዋንዳ በአውራጎዳናዎቿ ላይ ኮሮናቫይረስ መመርመር ጀመረች

    በሩዋንዳዋ ዋና ከተማ ኪጋሊ ፖሊስ መንገደኞችን እያስቆመ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ሰዎችን ፈቃድ ሲጠይቅ ተስተውሏል።

    ይህ የተጀመረው ሐሙስ ማለዳ ሲሆን በኪጋሊ የተወሰኑ አውራ ጎዳናዎችና መግቢያዎች ላይ ምርመራ ሲካሄድ ታይቷል።

    የሩዋንዳ ጤና ባለስልጣናት "በዋና ከተማዋ ስላለው የኮቪድ-19 ስርጭት ተጨባጭ መረጃ እንሰጣለን" ብለዋል።

    ሩዋንዳ ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ 140 ሺህ ናሙናዎች ላይ ምርመራ ያደረገች ሲሆን ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በኪጋሊ የሚገኙ ባለስልጣናት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰው ስራ በሚገባበት ማለዳ ላይ እና ከሥራ ወደ ቤቱ በሚመለስበት ምሽት ምርመራቸውን እያደረጉ ነው።

    አንዳንዶች ግን ተገድደው ለመመርመር ፈቃዳቸውን መስጠታቸውን እየተናገሩ ነው።

    አንድ የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው ፖሊስ ለምርመራ እንዲተባበር እንዳስገደደው የገለፀ ሲሆን ሌላ ግለሰብ ደግሞ ምርመራ በማካሄዱ ደስተኛ መሆኑንና ናሙና ሰጥቶ ወደ እለት ጉዳዩ መሰማራቱን ተናግሯል።

    ባለፈው ሳምንት የሩዋንዳ ባለስልጣናት በከተማዋ የኮሮናቫይረስ ስርጭት መጨመሩን ተከትሎ በተወሰኑ የዋና ከተማዋ ክፍሎች ዳግም የእንቅስቃሴ ገደብ መጣላቸው ይታወሳል።

  7. የኒው ዚላንድ ጤና ሚኒስትር "በፈጸሙት ስህተት" ሥራቸውን ለቀቁ

  8. ግብጽ ፒራሚዶቿን ለጎብኝዎች ክፍት አደረገች

    ግብጽ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ስትል ለሦስት ወራት ዘግታቸው የነበሩትን የጊዛ ፒራሚድን ጨምሮ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች መክፈቷን አስታወቀች፡፡

    ፒራሚዶቹ በካይሮ ታህሪር አደባባይ ቀጥሎ የሚገኘው ሙዚየም ጋር ለጉብኝት ክፍት የተደረጉ የመጀመሪያዎቹ የቱሪስት መዳረሻ ናቸው፡፡

    አገሪቷ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት የአየር ማረፊያዎቿን እና ታዋቂ የሆኑ ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን የዘጋችው መጋቢት አጋማሽ ላይ ነበር፡፡

    አሁን ዓለም አቀፍ በረራዎችን ጀምራለች፡፡

    ባለሥልጣናት የተጣሉ ገደቦች እየተነሱ በመሆናቸው በርካታ ጎብኝዎች ግብጽን መዳረሻቸው እንደሚያደርጉ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡

    በግብጽ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን ለሦስት ሚሊየን ሰዎችም የሥራ እድል የፈጠረ ነው፡፡

    በግብጽ እስካሁን ከ68 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

  9. በሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ሳቢያ 16 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙበት ሙሽራ ተቀጣ

    በሕንድ ራጃስታን ግዛት በተካሄደ ሠርግ ሳቢያ በቫይረሱ ሕይወቱ ያለፈን አንድ ግለሰብ ጨምሮ 16 ሰዎች በኮሮናቫይረስ በመያዛቸው ያልተጠበቀ ቅጣት አስከትሏል፡፡

    የሙሽራው ቤተሰቦችም ለደኅንነት ሲባል የተጣሉ ገደቦችን በመጣስ 7 ሺህ 944 ዶላር ተቀጥተዋል፡፡ በግዛቷ በሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት የሚችሉት ከፍተኛው የሰዎች ቁጥር 50 ብቻ ቢሆንም፤ በዚህ ሠርግ ላይ ግን የታደሙት ከ1 ሺህ የሚበልጡ እንግዶች እንደነበሩ ኤንዲቲቪ ዘግቧል፡፡

    ከዚህም በተጨማሪ ቤተሰቦቹ በቫይረሱ ተይዘው በሕክምና ላይ የሚገኙ 15 ሰዎችንና በለይቶ ማቆያ የሚገኙ 60 የሚጠጉ ተጋባዦችን ማሳከሚያ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡

    ይህም ምግብና በለይቶ ማቆያ የሚያስፈልጉ ሌሎች አገልግሎቶችን ሊያካትት እንደሚችል ተነግሯል፡፡

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በቢሃር ግዛት በተካሄደ ሌላ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ሳቢያ ከ100 በላይ ታዳሚዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የበሽታው ምልክት የነበረው ሙሽራም በሠርጉ ማግስት ሕይወቱ ማለፉ ተዘግቧል፡፡

  10. የዓለም ጤና ድርጅት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በአስጊ ሁኔታ እንደሚገኙ ገለጸ

    የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ተጥለው የነበሩ የእንቅስቃሴ ገደቦችን በማንሳታቸው እንዲሁም አየር ማረፊያዎችና ድንበሮች እንዲከፈቱ በመፍቀዳቸው በሽታው አስጊ ሁኔታ ላይ መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

    መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ እንዲሁም አፍጋኒስታንና ፓኪስታንን በሚያካልለው የምሥራቅ ሜደትራኒያን ቀጠና፤ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር፤ በቀጠናው በሰኔ ወር ላይ ብቻ የተመዘገበው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት አራት ወራት ከተመዘገበው የሚበልጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

    ዳይሬክተሩ ዶ/ር አል ማንድሃሪ እንዳሉት በቀጠናው ከሞቱ ሰዎች 87 በመቶ የሚሆኑት የተመዘገቡት በአምስት አገራት ሲሆን እነዚህም ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ እና ፓኪስታን ናቸው፡፡

    በፖለቲካ ቀውስ በሚታመሱት በሶሪያና በመን የተመዘገበው ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህ የሆነው በአገራቱ ምርመራ ለማካሄድ፣ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለመከታተል እንዲሁም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለማከም አዳጋች በመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

    ዶ/ር አል ማንድሃሪ "የጤና ተቋማቶቻችን ተጨናንቀዋል፤ የጤና ባለሙያዎችም ደክሟቸዋል፤ ግን አሁንም በቀጠናው ያሉ በርካታ ሰዎች ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው" በማለት፤ ተስፋ መቁረጥ ግን ምርጫ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

  11. በአሜሪካ በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ተመዘገበ

    በአሜሪካ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ አገሪቷ በአንድ ቀን ብቻ ከፍተኛ የተባለውንና 52 ሺህ 982 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች፡፡

    በአጠቃላይ በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2 ሚሊየን 682 ሺህ 270 የደረሰ ሲሆን 128 ሺህ 028 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህም በቫይረሱ በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ብራዚል ካጋጠመው ከሁለት እጥፍ በላይ ነው፡፡

    የአሜሪካ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣን ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ የወረርሽኙ ሥርጭት እየቀነሰ እንዳልሆነ በመግለጽ፤ አገሪቱ በአንድ ቀን 100 ሺህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በቅርቡ ልትመዘግብ ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

    ይህንንም ተከትሎ ምንም እንኳን በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢያስከትልም በአገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ ግዛቶች የእንቅስቀሴ ገደቦችን የማላላት እቅዳቸውን አጥፈዋል፡፡

  12. የሐሙስ ሰኔ 25/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    እንደምን አደራችሁ?

    ዕለተ ሐሙስ ሰኔ 25/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ እነሆ ከዓለም ዙሪያ ያሰባሰባቸውን የኮሮናቫይስን ወረርሽኝን የተመለከቱ ዜናና ታሪኮችን ማቅረብ ጀመረ።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ በዓለማችን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10.5 ሚሊየን አልፏል፡፡ ከ515 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወትም በቫይረሱ ተቀጥፏል፡፡

    ከአገራችንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ 6127 መድረሱን ትናንት የጤና ሚኒስተርና የህብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ከሰሞኑ ያለው ወቅታዊ ሁኔታም የቫይረሱን ሥርጭት በከፋ ሁኔታ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡

    ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ ምክሮችን በመተግበር ራሳችንንና ቤተሰባችንን ከኮሮናቫይረስ እንጠብቅ መልዕክታችን ነው፡፡

    ባገኛችሁት አጋጣሚ የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽን በመጎብኘት በቀጥታ የዘገባ ገጻችንን ላይ የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን እንድታነቡ እንጋብዛለን።

    መልካም ቀን እንዲሆንላችሁ ተመኘን!

  13. ግሪክ የቱሪስት በረራዎችን እንደገና ጀመረች

    ግሪክ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ማላላታቸውን ተከትሎ ድንበሯን ለተወሰኑ ጎብኝዎች ከፍታለች፡፡

    እስከ ሐምሌ አጋማሽ ድረስ ወደ ግሪክ መብረር ከማይችሉት ከስዊድንና ከዩናይትድ ኪንግደም በስተቀር አውሮፓዊያን ተጓዦች ላይ የተጣለ ገደብ የለም፡፡

    ከጣሊያን የሚመጡ የሰውና የእቃ ማጓጓዣ መርከቦችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎችና ወደቦችም ለቱሪስቶች እየከፈተች ነው፡፡

    አገሪቷ ይህን ውሳኔ ያሳለፈችው የአውሮፓ ሕብረት ወደ አባል አገራቱ እንዲገቡ ለተፈቀደላቸው አገራት ድንበሩን ክፍት ካደረገ በኋላ ነው፡፡

    ወደ አገራቱ መግባት ከሚችሉ አገራት ዝርዝር ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አሁንም እየተስፋፋባቸው ያሉት አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሩሲያ አልተካተቱም፡፡

    በርካታ የአውሮፓ አገራትም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ሲባል ጥለዋቸው የነበሩ ሌሎች ገደቦችን ያላላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

    ይሁን እንጅ ወረርሽኙ በአውሮፓ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ሥር አልዋለም፡፡ በጀርመን ፣ ስፔንና ፖርቱጋል ወረርሽኙ በማገርሸቱ በድጋሚ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል፡፡

    በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ በሚገኙ አገራትም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል፡፡

  14. ትምህር ቤት በተዘጋበት ወቅት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች "ተዘንግተዋል" ተባለ

    በዩናይትድ ኪንግደም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ወላጆች ትምህር ቤት በተዘጋበት ሰዓት መዘንጋታቸውን የፓርላማ አባላት ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

    በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ትምህርታዊ፣ አካላዊና እና ስሜታዊ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ልጆች የተደረገው ድጋፍም እጅግ ዝቅተኛ እንደነበር ተገልጿል፡፡

    ኮሚቴው ኮቪድ -19ን በተመለከተ በተሰራ ግምገማ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ትምህርት እንዳይከታተሉ ተደርገዋል ብሏል፡፡

    አንድ ገልተኛ የሆነ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት አሊ ፊዲይ ወላጆች ሲቸገሩ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

    "ለወላጆቹ የተደረገው ድጋፍም በቂ አልነበረም በመሆኑም አብዛኞቹ ወላጆች እንደተዘነጉ ተሰምቷቸዋል" ብለዋል፡፡

    ኃላፊዋ ምንም እንኳ በወረርሽኙ ሳቢያ ተማሪዎች በተለያየ መንገድ ትምህርታቸውን እንዲከታታሉ የማድረጉ እቅድ፤ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆችን የሚያካትት ቢሆንም፤ ልጆቹን ከትምህርት ቤት ውጭ አድርጓቸዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

    ለዚህም ልጆቹ አገልግሎት እንዳያገኙ እና ከትምህርት ውጭ እንዲሆኑ ኮሮናቫይረስ በምክንያትነት ቀርቧል ብለዋል፡፡

  15. በኢትዮጵያ 79 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ

    በኢትዮጵያ ከተደረጉ 1ሺህ 398 የላብራቶሪ ምርመራዎች 79 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቀዋል፡፡

    ይህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 6127 አድርሶታል፡፡

    በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሰዎች 47 ከአዲስ አበባ፣ 3 ከትግራይ፣ 13 ከአማራ ክልል፣ 5 ከሶማሊ ክልል እና 11 ከአፋር ክልል መሆናቸው ተገልጿል፡፡

    ተቋማቱ በዕለታዊ መግለጫቸው ከ14 አስክሬን ላይ ናሙና ተወስዶ ምርመራ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአንዱ ላይ ቫይረሱ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

    ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በሕክምና ላይ የነበረ የ45 ዓመት ጎልማሳም በበሽታው ሕይወቱ አልፏል፡፡

    59 ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል፡፡

    ዛሬ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት በእጅጉ ያነሰ ሲሆን አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ናሙናዎች የመሰብሰብ ሂደቱን አዳጋች እንዳደረገው ተቋማቱ ገልጸዋል፡፡

  16. ዚምባብዌ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የጣለችውን ገደብ አላላች

    ዚምባብዌ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ጥላው የነበረውን ገደብ በከፊል ልታላላ መሆኑን አስታውቃለች፡፡

    በአገሪቷ ለሦስት ወራት የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ተከትሎ ከተጎዱ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው፡፡

    በዚምባብዌ ከዚህ ቀደም ምግብ ቤቶች ወደ ቤት የሚወሰዱ ምግቦችን የማዘጋጀት አገልግሎት ብቻ እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸው የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን እዚያው ለመጠቀም እንደሚፈቀድ ተገልጿል፡፡

    ነገር ግን ምግብ ቤቶቹ ማስተናገድ ከተፈቀደላቸው አቅም በግማሽ መቀነስ እንዳለባቸው ተነግሯል፡፡

    ብሔራዊ ፓርኮችና የቱሪስት መዳረሻዎችም እንደገና እንዲከፈቱ ተፈቅዷል፡፡

    የዚምባብዌ ኢኮኖሚ በአብዛኛው በቱሪዝም ላይ የተመሰረተ ሲሆን በዓመት ወደ አገሪቷ ከሚገቡ ከ2 ሚሊየን የሚበልጡ ጎብኚዎች 1 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ታገኛለች፡፡

    ይሁን እንጅ በወረርሽኙ ሳቢያ ድንበሮች በመዘጋታቸው ዘርፉ ተዘግቶ ቢቆይም፤ የዘርፉ ባለሙያዎች የአገር ውስጥ ጎብኝዎችን ለመጨመር ትኩረት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

    በዚምባብዌ እስካሁን 574 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡

  17. ኡጋንዳ ለኮንጎ ስደተኞች ድንበሯን ከፈተች

    ኡጋንዳ ለሦስት ወራት ያህል ደህንነታቸው አስጊ በሆኑ ቦታዎች የቆዩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመቀበል ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ከፈተች፡፡

    ግንቦት ወር ላይ በኮንጎ ሰሜን ምስራቅ ግዛት ኢቱሪ በተከሰተ የእርስ በርስ ግጭት ቢያንስ 3ሺህ ሰዎች መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ወጥተዋል፡፡

    ይሁን እንጅ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ኡጋንዳ ድንበሯን በመዝጋቷ ወደ ጎረቤት አገር ለመጠጋትም አልቻሉም ነበር፡፡

    አሁን ላይ ግን ኡጋንዳ ለእነዚህ ስደተኞች በሯን ለመክፈት ፈቅዳለች፡፡

    ስደተኞቹ ወደ ካምፕ እንዲገቡ ከመደረጋቸው በፊትም ለ14 ቀናት ከድንበሯ በ13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አዲስ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ይቆያሉ ተብሏል፡፡

    የተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት በበኩሉ ከስደተኞቹ መካከል ኮሮናቫይረስ ያለበት ስለመኖር አለመኖሩ ለማረጋገጥም ምርመራ እንደሚደረግላቸው ገልጿል፡፡

    በመሆኑም ወደ ኡጋንዳ የሚያስገቡ ሁለት ድንበሮች በጊዜያዊነት ክፍት የተደረጉ ሲሆን ሁሉም ስደተኞች በሦስት ቀናት ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

    በኡጋንዳ ከ1.4 ሚሊየን በላይ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ ከደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ናቸው።

    30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናቸው፡፡

  18. ከንቲባው የእንቅስቃሴ ገደቡን የተላለፈ ልጃቸውን ለፖሊስ አስረከቡ

    በበርካታ አገራት የሚገኙ የመንግስት ኃላፊዎች እራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው የእንቅስቃሴ ገደቡን ሲጥሱ ዝም በማለታቸው በሚተቹበት ወቅት ኮሎምቢያ ውስጥ አንድ ያልተለመደ ነገር ተከስቷል።

    ካርሎስ ሂጊንስ ይባላሉ፤ በሰሜናዊ ሁዋን ዴ ኮስታ ከንቲባ ሲሆኑ የእንቅስቃሴ ገደቡን የተላለፉ ወንድ ልጃቸውና አንድ ሌላ የዘመድ ልጅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው አስረክበዋል።

    ከንቲባው ሲያስረዱ ከአካባቢው ነዋሪዎች በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ሲሄዱ ልጃቸውን ጨምሮ ወጣቶቹ በአንድ ቤት ተሰባስበው አልኮል እየጠጡ ነበር ብለዋል።

    "ሕግን ለማስከብ ዘመዶቼም ቢሆን ኃላፊነት አለባቸው። ሰብሰብ ብሎ አልኮል ለመጠጣት በሚል ሰበብ የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት አደጋ ውስጥ መክተት አልፈልግም’’ ሲሉ ለአንድ ሬድዮ ጣቢያ ተናግረዋል።

    ከንቲባውም ለፈጸሙት ተግባር ምስጋና እየጎረፈላቸው ነው።

    ኮሎምቢያ እስካሁን 95 ሺህ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን 3376 ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

  19. በናይጄሪያ ሌጎስ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲከታተሉ ሬዲዮ ሊሰጣቸው ነው

    በናይጄሪያ የሌጎስ ከተማ አስተዳዳሪ በቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች 10 ሺህ ሬዲዮኖችን ለማሰራጨት እቅድ እንዳለው አስታወቀ።

    የከተማዋ ትምህርት ኮሚሽነር ፎልሳዴ አዴፊሳዮ አስተዳደራቸው ከቴሌኮሙኑኬሽን ተቋማት ጋር በመተባበር ተማሪዎች በኦንላየን ትምህርታቸውን በነጻ እንዲከታተሉ ያደርጋል ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ ሰኞ እለት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ የመጨረሻ አመት ተማሪዎች ለወሳኝ ፈተናዎች እንዲዘጋጁ በሚል ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ፈቅደዋል።

    ሌሎቹ ተማሪዎች ግን ትምህርታቸውን ቤታቸው ሆነው እንዲቀጥሉ ይደረጋል ተብሏል።

    የሌጎስ ከተማ አስተዳደር ትምህርት በሬዲዮ የሚያሰራጭ ጣብያ ለማቋቋምና በዚህ የኮሮናወረርሽኝ ወቅት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እንደሚሰራ አስታውቋል።

    የትምህርት ኮሚሽነሯ አክለውም መንግሥት ተማሪዎች ከቤት ሆነው መማራቸውን ይደግፋል ብለዋል።

  20. የህንድ ባለስልጣናት አስከሬኖች ሲጣሉ የሚያሳይ ቪዲዮን ተከትሎ ይቅርታ ጠየቁ

    በኮሮናቫይረስ ህመም የሞቱ ግለሰቦች አስከሬን በደቡባዊቷ ህንድ ግዛት ሲጣል የሚያሳየው ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ በርካቶች ቁጣቸውን ገልፀዋል።

    በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተጋራው ቪዲዮ እንደሚያሳየው የመከላከያ አልባሳትን የለበሱ ሰራተኞች በጥቁር ቆሻሻ መጣያ ፕላስቲክ የተጠቀለሉ ስምንት አስከሬኖች ወደ ጉድጓድ ሲወረውሩ ያሳያል።

    የካርናታካ ግዛት ኃላፊዎች ቪዲዮው ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠው ለሟች ቤተሰቦች ይቅርታን ጠይቀዋል።

    በካርናካ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ246 በላይ ሲሆን፤ በሃገሪቱ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ህሙማን ጋር ግንኙነት እንዲሁም የታወቀ ንክኪ ያላቸውን ግለሰቦች ክትትልም በማድረግ የተዋጣላት ናት ተብሏል።