በኢትዮጵያ 91 ሰዎች ከኮቪድ-19 ሲያገግሙ 63 አዲስ ህሙማን ተገኙ

የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየገሰገሰ ባለባት ኢትዮጵያ ዛሬ 63 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በአገሪቱም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4532 አድርሶታል፤ ከእነዚህም ውስጥ 1213 አገግመዋል። ተጨማሪ ሁለት ሰዎች የሞቱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር 74 ደርሷል። እስከ ዛሬ [እሁድ] ድረስ የተከናወኑ የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራዎችም 216 ሺህ 328 ደርሷል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ኮሮናቫይረስ ዳግም እየተሰራጨ ነው

    ትናንት የወጡ አሃዞች እንዳመላከቱት በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ኮሮናቫይረስ ዳግም እየተሰራጨ ነው።

    በደቡብ እና ምዕራብ አሜሪካ በሚገኙ ግዛቶች ደግሞ ስርጭቱ አይሎ ታይቷል። ከጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው አሃዝ እንደሚያመላክተው በ16 ግዛቶች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

    አሪዞና፣ አላባማ፣ ዋሽንግተን፣ ሳውዝ ካሮላይና፣ ዩታህ፣ ቴክሳስ፣ ሚሲሲፒ፣ ፍሎሪዳ እና ጆርጂያ ቫይረሱ እየተሰራጨባቸው ይገኛል ከተባሉት ግዛቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

    በአሪዞና የሚገኙ ሆስፒታሎች እስከ አቅማቸው ጫፍ ድረስ ታማሚዎች እየተቀበሉ ነው።

    እስካሁን ድረስ በአሜሪካ 119ሺህ ገደማ ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

  2. የቻይና አየር መንገዶች የጠየቁትን ተጨማሪ በረራ አሜሪካ ውድቅ አደረገች

    የቻይና አየር መንገዶች ተጨማሪ ሳምንታዊ በረራ ወደ አሜሪካ ለማድረግ ያቀረቡትን ጥያቄ ዋሽንግተን ውድቅ አደረገች።

    የአሜሪካ የትራንስፖርት ዲፓርትመንት የአየር መንገዶቹን ጥያቄ ውድቅ ባደረገበት መግለጫ ውሳኔ በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለውን የንግድ ጦርነት ለማባባስ በማሰብ አይደለም ብሏል።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ እና ቻይና እያንዳንዳቸው በሁለቱ አገራት መካከል አራት ሳምንታዊ በረራዎች ብቻ እንፈቅዳለን ማለታቸው ይታወሳል።

    የትራንስፖርት ዲፓርትመንቱ ሰኞ ዕለት አሜሪካ እና ቻይና ባላቸው የአቪዬሽን ስምምነት መሠረት የአሜሪካ አየር መንገዶች ወደ ቻይና በሚያደርጉት በረራ ላይ የጣለችውን ገደብ ሙሉ በሙሉ ታነሳለች ብለን እናምናለን ብሏል።

    ሁለቱ የዓለማችን ግዙፍ የምጣኔ ሃብት ባለቤቶች በረራዎች ላይ ገደብ መጣል የጀመሩት ኮሮናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ እንደሆነ ይታወሳል።

  3. ትራምፕ በኦክላሆማ ደጋፊዎቻቸውን አደባባይ እንዲጠሩ ፍርድ ቤት ፈቀደ

    የኦክላሆማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቱልሳ ከተማ ደጋፊዎቻቸውን በአንድ ቦታ ማሰባሰብ ይችላሉ ሲል ፈቀደ።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ ከወራት በኋላ የድጋፍ ሰልፍ ሲያካሂዱ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

    በኦክላሆማ ግዛት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም ለትራምፕ ድጋፋቸውን ለመስጠት በርካቶች አደባባይ ቢወጡ የቫይረሱ ሰርጭት በማኅብረሰቡ ውስጥ በድጋሚ ይስፋፋል ሲሉ ስጋታቸውን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።

    የከተማዋ ጤና ቢሮ "ሰዎች ለፕሬዝደንቱ ድጋፍ ለማሳየት ብላችሁ ጤናችሁን አደጋ ላይ አትጣሉ" ሲል አስጠንቅቋል። የኦክላሆማ ግዛት አስተዳዳሪ ግን ፕሬዝደንት ትራምፕን እንኳን በደህና መጡ ሲሉ አቀባበል አድርገዋል።

    ትራምፕ አደባባይ የጠሩት ሰልፍ 19ሺህ በላይ ሰዎችን በሚይዘው ማዕከል ዛሬ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

  4. ዩኬ የለይቶ ማቆያ ደንቧን ለአንዳንድ አገራት ልታላላ ነው

    ዩናይትድ ኪንግደም ከሐምሌ ጀምሮ አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ደንቧን ለአንዳንድ አገራት የማላላት እቅድ እንዳላት አስታወቀች።

    ከፖርቹጋል፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ግሪክና ስፔን ጋርም ንግግር እየተደረገ ነው።

    ከአንድ አገር ወደ ሌላው የሚገቡ ሰዎች በሁለቱም አገራት ለይቶ ማቆያ የመግባት ግዴታ አይኖርባቸውም ማለት ነው።

    የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ደንብ በየሦስት ሳምንቱ ይከለሳል ተብሎ ነበር። የደረሱበትን ውሳኔም ሰኔ 29 ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ከዩኬ ጋር ስምምነት ካላቸው አገሮች ውጪ ያሉት ግን ዜጎቻቸው በለይቶ ማቆያ መግባት ይጠበቅባቸዋል።

  5. የአውሮፓ ሕብረት አመራሮች ከቀውስ ለማገገም በተመደበው ገንዘብ አልተስማሙም

    የአውሮፓ ሕብረት አመራሮች ኮሮናቫይረስ ካስከተለው ቀውስ ለማገገም በተመደበው 750 ቢሊዮን ዩሮ አልተስማሙም።

    ሆኖም ግን አመራሮቹ መካከል የተካሄደውን ውይይት ጀርመን “ገንቢ” ብላዋለች። መራሔተ መንግሥቷ አንግላ መርከል፤ ገና ብዙ ቢጠበቅባቸውም ውይይቱ ገንቢ እንደነበር ተናግረዋል።

    ውይይቱ የተካሄደው በቪዲዮ ኮንፍረንስ ነበር። ሐምሌ ላይ አባል አገራቱ ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመወያየት እቅድ ይዘዋል።

    የሰሜን አውሮፓ አገራት፤ የአውሮፓ ሕብረት 500 ቢሊዮን ዩሮ ይደጉም በሚለው ሐሳብ አልተስማሙም። አገራቱ መሰጠት ያለበት ብድር ነው የሚል አቋም አላቸው።

    በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱት ጣልያን እና ስፔን ከእርዳታው ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ።

    ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ኦስትሪያ እና ኔዘርላንድስ ሕብረቱ የመደበው ገንዘብ ከፍተኛ ስለሆነ ገንዘቡ በጊዜ ሂደት መመለስ አለበት ይላሉ።

    የአውሮፓ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊ ክስቲን ሌግሬስ፤ የአውሮፓ ምጣኔ ኃብት ከፍተኛ ውድቀት ይጠብቀዋል ማለታቸው ይታወሳል።

  6. ከባድ የጤና ችግር ኖሮባቸው ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ታሪክ

    'ከባድ የጤና እክል ቢኖርብኝም ከቫይረሱ አገግሜያለሁ' የሚሉ ሰዎች ታሪክን ይዘንላችሁ ቀርበናል።

    የቀደመ አሳሳቢ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዝ በጣም አስፈሪ ነገር ሊሆንባቸው ይችላል።

    ምናልባትም ብዙዎች ስለዚህ ጉዳይ ሲያስቡ በጣም ሊጨነቁ ይችላሉ። ነገር ግን አስጊ የሚባል የጤና ሁኔታ ላይ ሆነው እንኳን ከቫይረሱ እያገገሙ ያሉ ሰዎች አሉ።

    ከእነዚህም መካከል ብርዮኒ ሆፕኪንስ አንዷ ናት። ብርዮኒ ታሪኳን እንዲህ ትናገራለች።

  7. በብራዚል በኮሮናቫይረስ የተያዙ አንድ ሚሊዮን ደረሱ

    ብራዚል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 የተያዙባት ሁለተኛዋ አገር ሆነች።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ከ54,000 በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን የብራዚል የጤና ሚንስትር አስታውቋል። ይህም እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው።

    ላለፉት አራት ተከታታይ ቀናት ከ1,200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። የሟቾች ቁጥርም 49,000 ደርሷል።

    ባለሙያዎች እንደሚሉት በቂ ምርመራ ቢደረግ ከዚህም በላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ።

    የዓለም ጤና ድርጅት በሰጠው መግለጫ ቫይረሱ “አዲስና አደገኛ” ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል።

  8. እንዴት አደራችሁ?

    እንዴት አደራችሁ ውድ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች?

    የቀጥታ ዘገባ ገጻችን ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማድረስ ጀምሯል።

    አብራችሁን ቆዩ።

    መልካም ቀን!

  9. በጣልያ በኮቪድ-19 ሳቢያ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ

    በጣልያን ባለፉት 24 ሰዓታት በኮሮናቫይረስ ሳቢያ 47 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ትላንት [ሐሙስ] 66 ሰዎች ሞተው ነበር።

    ሐሙስ ዕለት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 333 ነበር። ዛሬ ደግሞ 251 ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘዋል።

    ከወራት በፊት የወረርሽኙ ማዕከል የነበረችው ጣልያን፤ አሁን በቫይረሱ ሳቢያ በርካታ ሰዎች ከሞቱባቸው አገሮች አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያሉት አሜሪካ፣ ብራዚል እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው።

    ከአገሪቱ የተገኘው መረጃ በኮሮናቫይረስ ከ34 ሺህ 561 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ያሳያል። ከ238 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

    ጣልያን ቀስ በቀስ እንቅስቃሴ ላይ ጥላ የነበረውን ገደብ እያነሳች ነው።

  10. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ አደገኛ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው፡ የዓለም ጤና ድርጅት

    የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ “ወደ አዲስና አደገኛ” ደረጃ እየተሸጋገረ ነው ሲል አስጠነቀቀ።

    ድርጅቱ ይህንን ያለው ሐሙስ ዕለት በዓለም ዙሪያ ከዚህ ቀደም ከታየው በበለጠ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በበሽታው መያዙን በተመለከተ ሪፖርት መደረጉን ተከትሎ ነው።

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም እንዳሉት በአንድ ቀን 150 ሺህ አዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል።

    ከዚህም ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከሰሜንና ደቡብ አሜሪካ አህጉራት የተገኙ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅና ደቡብ እስያ አገራት የተገኙ ናቸው ብለዋል።

    ዶክተር ቴድሮስ ጨምረውም ኮሮናቫይረስ አሁንም በፍጥነት ከመዛመቱ በተጨማሪ ወረርሽኙ እየተስፋፋ ይገኛል ብለዋል።

    ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት "ሰዎች እራሳቸውን ለይተው በመቆየት ተሰላችተው ይሆናል። አገራትም ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎችን መክፈት ይፈልጋሉ። ነገር ግን አሁን ከሌላው ጊዜ በበለጠ ጠንቃቃ መሆን የሚያስፈልግበት ነው" ሲሉ መክረዋል።

  11. የወረርሽኙን መነሻ ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ከፖሊስ የወንጀል ምርምራ ጋር ምን አገናኘው?

    አንድ ቫይረስ ከየት ተነሳ የሚለው ነገር ነፍሰ ገዳይን ለማደን ከሚደረገው ሂደት አይለይም። ፖሊስ ወንጀል የተፈጸመበት ሄዶ አካባቢውን ማጠር አለበት። የኅብረተሰብ ጤና ሰዎችም እንደዚያው ነው የሚያደርጉት።

    ፖሊስ ምስክሮችን ቶሎ ይዞ መመርመር አለበት። የጤና ባለሞያዎችን ቶሎ ታማሚዎችን ወይም የታማሚ ቤተሰቦችን መመርመር አለባቸው።

    ገዳዩን ለማግኘት ዱካውን ፍለጋ ሩጫ ያሻል። ቫይረስም እንደዚያ ነው።

    ምንም እንኳ የቫይረሱን ጭራ ለመያዝ ዓለም አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም ነፍሰ ገዳዩ ቫይረስ አሁንም ሺህዎችን እየገደለ ነው።

    አሁን ቫይረሱ የመጀመርያውን ጥቃት ካደረሰ መንፈቅ ሆኖታል። ሳይንቲስቶች እስካሁን ምን ላይ ደርሰው ይሆን? መዳኛውን ባያገኙም መነሻውን ደርሰውበት ይሆን? ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ ወንጀለኛን ከማደን ጋር የሚመሳሰለው ወረርሽኝን የመቆጣጠሪያ መንገድ

  12. በኮንጎ ስለኖቤል ተሸላሚው ዶክተር የተሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ ነው ተባለ

    ከሁለት ዓመታት በፊት የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ዶ/ር ዴኒስ ሙክዌጌ ከኮንጎ የኮቪድ-19 መከላከል ግብረ ኃይል ራሳቸውን ስላገለሉበት ምክንያት የተናፈሰው መረጃ ሐሰተኛ ነው ተባለ።

    ዶክተር ዴኒስ ከኮቪድ-19 ጋር የማይገናኙ ሞቶችን ከወረርሽኙ ጋር ይያያዛሉ እንዲሉ በመገደዳቸው ከግብረ ኃይሉ መውጣቸውን የሚገልጽ ሐሰተኛ መረጃ በፌስቡክና በዋትስአፕ እየተናፈሰ ነበር።

    “የኖቤል ሽልማቴን ለገንዘብ ስል አላቆሽሽም። ማንኛውም በሽታና ሞት ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኘ ነው እንድንል ታዘናል” ከሚል ጽሑፍ ጋር ነበር ሐሰተኛ መረጃው የተሰራጨው።

    ዶ/ር ዴኒስ ላለፉት ሁለት ወራት በኮንጎ ወረርሽኙን ለመከላከል የተቋቋሙ ሁለት ቡድኖች ውስጥ ይሠሩ ነበር።

    የኮቪድ-19 ምርመራ የሚካሄድባቸው ቤተ ሙከራዎች አለመኖራቸው ሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረ ተናግረው ሥራ ቢለቁም፤ ማንኛውም በሽታና ሞት ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኘ ነው እንድንል ታዘናል አላሉም።

    ማኅበረሰቡ አካላዊ ርቀት በአግባቡ አለመጠበቁ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከጎረቤት አገራት ወደ ኮንጎ ሲገቡ ለይቶ ማቆያ አለመግባታቸው የግብረ ኃይሉን ጥረት ማደናቀፉንም ተናግረዋል።

  13. ከአምሰት መቶ በላይ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ለይቶ ማቆያ ገቡ

    ከ500 በላይ የእስራኤል ሠራዊት አባላት የሆኑ ወታደሮች በኮሮናቫይረስ ተጠርጥረው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደረገ።

    በተጨማሪም በአገሪቱ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በድንገት በማሻቀቡ ምክንያት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መንግሥት ጥብቅ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።

    በሽታው በከፍተኛ መጠን የተገኘባቸው ሦስት በደቡባዊ እስራኤል በረሃማ አካባቢ ያሉ የመኖሪያ መንደሮች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።

    በቴል አቪቭ ከተማ በሚገኙ የተወሰኑ ክፍሎች ላይም አዲስ የቁጥጥር መመሪያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል።

    በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ውስጥ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ክልከላ ባለፈው ወር ከላላ በኋላ በበሽታው የታያዙ ሰዎች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል።

    የጤና ባለስልጣናት እንዳሉት ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ ባለፉት ሁለት ቀናት ከፍተኛው የህሙማን ቁጥር ተመዝግቧል። በዚህም ሳቢያ ሔብሮን ውስጥ ሱቆችና የንግድ ተቋማት ለጊዜው እንዲዘጉ ተደርጓል።

    በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄድን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ለጊዜው ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲከፈቱ የማድረግ ነገር አይኖርም ብለዋል።

  14. በቱርክ የበሽታው ስርጭት በመጨመሩ ሰዓት እላፊ ሊታወጅ ነው

    በቱርክ የኮቪድ-19 ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ነገና በቀጣይ በሚመጡ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በከፊል የሰዓት እላፊ ሊጣል ነው።

    ከሁለት ሳምንታት በፊት እንቅስቃሴ ላይ የተጣለው ገደብ መነሳቱን ተከትሎ የበሽታው ስርጭት ጨምሯል።

    መንግሥት አራት ሚሊዮን የሚጠጉ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ የሚፈተኑ ተማሪዎችን ከበሽታው ለመከላከል እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

    ተማሪዎች የሚፈተኑባቸው ማዕከሎች ቁጥር ተጨምሯል። ተማሪዎችም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

    አስፈላጊ መደብሮችና አንዳንድ ሱቆች አይዘጉም። ሆኖም የሰዓት እላፊው ሰዎች እንዳይሰበሰቡ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

  15. የአንድ ሐኪምን ሞት ተከትሎ የፖርቹጋሉ ፕሬዝዳንት ለጤና ዘርፉ በቂ በጀት ሊመደብ ይገባል አሉ

    የፖርቹጋሉ ፕሬዘዳንት ማርሴሎ ሮቤሎ ደ ሱዛ በአገሪቱ አንድ ዶክተር በኮቪድ-19 መሞቱን ተከትሎ፤ ለጤና ዘርፉ በቂ ደጀት ሊመደብ ይገባል አሉ።

    በአገሪቱ በበሽታው ሳቢያ የጤና ባለሙያ ሲሞት ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ይታመናል።

    ፕሬዘዳንቱ ለዶክተሩ ቤተሰቦችና ጓደኞች ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ሐኪሙ “ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል” ብለው “የጤና ዘርፉ በቂ ግብአት ሊሟላለት ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የ68 ዓመቱ ዶክተር በሽታው የያዛቸው ከሥራ ባልደረባው ነው ተብሏል። በሊዝበን በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ለ40 ዓመታት አገልግለዋል።

    ሐኪሙ ከመሞታቸው ከሰዓታት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር አንቶንዮ ኮስታ፤ ፖርቹጋል የመጨረሻውን ዙር የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ እንድታስተናግድ መመረጧ “ለጤና ባለሙያዎች የሚገባ ሽልማት” ነው ብለው ነበር።

    ብሔራዊውን የሐኪሞች ማኅበር የሚመሩት ኖኤል ቻርሊሆ ግን የጤና ባለሙያዎች እውቅና እንዲሰጣቸው የሚፈልጉት በእግር ኳስ አይደለም ብለዋል። የተሻለ የሥራ ሁኔታ ሊመቻችላቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።

  16. ኮሮናቫይረስ ልጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አባብሶታል

    በዓለም ላይ ከሚገኙ ህጻናት ገሚሱ ማለትም አንድ ቢሊዮን የሚሆኑት ወሲባዊ፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።

    በኮሮናቫይረስ ምክንያት አገራት የዜጎችን እንቅስቃሴ መግታታቸው ደግሞ ይህን የህጻናት ጥቃት ከመቼውም በላይ እንዳባባሰው የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ።

    የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት፤ እአአ 2017 ላይ 40 ሺህ ህጻናት ተገድለዋል።

    ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡ መደረጉ ልጆች እርዳታ እንዳያገኙና ይደርስባቸው የነበረው ጫና እንዲባባስም ምክንያት ሆኗል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ሁኔታውን “የኮቪድ-19 እጅግ የሚረብሽ ተጽዕኖ” ብለውታል።

    ከ80 በላይ የሚሆኑ አገራት ጥቃቶችን ለመከላከል የሚውል ድጋፍ አያገኙም። ይህም ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል።

    ልጆች በቤታቸው ከሚገጥማቸው ጥቃት በተጨማሪ በበይነ መረብ የሚሰነዘር ጥቃትም ሰለባ ሆነዋል።

  17. ኮሮናቫይረስ በይፋ ከተነገረበት ከወራት በፊት መከሰቱ ጥናቶች አመለከቱ

  18. ፖላንድ ተመልካቾች ኳስ ሜዳ እንዲገቡ ፈቀደች

    ፖላንድ ከዛሬ ጀምሮ የእግር ኳስ ተመልካቾች ስታዲየም እንዲገቡ ፈቅዳለች። በዚህም ተመሳሳይ ውሳኔን ያስተላለፉ ግንባር ቀደም የአውሮፓ አገራትንም ተቀላቅላለች።

    ተመልካቾች የአራት ወንበር ክፍተት በየመሃላቸው እየተው ጨዋታ መመልከት ይችላሉ ተብሏል። የአንድ ቤተሰብ አባላት ግን ጎን ለጎን መቀመጥ ይችላሉ። በኳስ ሜዳዎች ካሉ መቀመጫዎች 25 በመቶ ሙሉ የሚሆኑት በተመልካቾች ሊያዝ እንደሚችሉም ተገልጿል።

    ተመልካቾች ወደመቀመጫቸው ሲሄዱና ሲነሱም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም እጅ ማጽጃ (ዲስኢንፌክታንት) ይቀርብላቸዋል። ትኬት የሚሸጠው ደግሞ በድረ ገጽ ነው።

    ከምዕራብ አውሮፓ አገራት መካከል ፖላንድ ብዙም በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ያላስመዘገበች ቢሆንም፤ እግር ኳስ ተመልካቾች ስታዲየም እንዲገቡ መፍቀድ ግን አላስፈላጊ ነው ሲሉ ባለሙያዎች እርምጃውን ተችተዋል።

  19. ኮቪድ-19 ተጨማሪ የስደተኞች ስጋት ሆኗል

    በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የስደተኛ ካምፖች የሚገኙባቸው አገሮች አስቀድመው እንዲዘጋጁ የተባበሩት መንግሥታት አሳሰበ።

    በምሥራቅ አፍሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች 21 ሺህ ደርሷል። በቀጠናው ከ4 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና 8 ሚሊዮን ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ይገኛሉ።

    በስደተኞች ካምፓች በስፋት በሽታው ባይሰራጭም አካላዊ ርቀት መጠበቅ አስቸጋሪ ነው።

    ግንቦት ላይ የኬንያ መንግሥት ወደ 200 ሺህ ሰዎች ወደሚኖሩበት ደዳብና ካኩማ ካምፖች መግባትም ይሁን መውጣት ከልክሏል።

    ካምፖቹ ጥብቅ እርምጃ በመውሰዳቸው በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ችለዋል።

    እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ በሽታው የተገኘባቸው 15 ስደተኞችና የጤና ባለሙያዎች ናቸው። ሆኖም ግን ኮቪድ-19ኝን መቆጣጠር ከባድ ይሆናል።

    አሁን ላይ እንቅስቃሴ መገታቱ፤ አዲስ ስደተኞች እንዳይመዘገቡና መረጃ እንዳይገኝም እንቅፋት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ተናግሯል።

    ከደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ግጭት ሸሽተው በአሜሪካ፣ ካናዳና አውሮፓ አዲስ ሕይወት ለመመስረት ተስፋ ያደረጉ ስደተኞች በረራ ላይ እገዳ በመጣሉ ባሉበት ለመቆየት ተገደዋል።

  20. ዩኒሴፍ ለየመን 10 ሺህ መመርመሪያ መሣሪያ ሰጠ

    የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት - ዩኒሴፍ፤ ወደ የመን መዲና ሰንአ 10 ሺህ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ መሣሪያዎች ላከ።

    በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ 8,000 መሣሪያዎች ኤደን ከተማ ይደርሳሉ ተብሎም ይጠበቃል።

    የዩኒሴፍ የየመን ወኪል ሳራ በይሶሎ ኒያንቲ “መሣሪያዎቹ በአገሪቱ በስፋት ኮቪድ-19 እንዲመረመር ያግዛሉ። በበሽታው የተያዙ ሰዎችን በአፋጣኝ ማግኘት ሕይወት ይታደጋል” ብለዋል።

    ባለፈው ወር የየመን የጤና ሥርዓት መቃወሱን የተባበሩት መንግሥታት መናገሩ ይታወሳል።