ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 4 ሺህ ተጠጋ
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስር እጥፍ ጭማሬ እያሳየ ባለበት በዚህ ወር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ወደ አራት ሺህ ተጠግቷል። በዛሬው ዕለት 195 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎም ቁጥሩንም 3ሺህ 954 አድርሶታል። በዛሬው ዕለትም ሁለት በህክምና ማዕከል የነበሩ ሰዎች ህይወት ማለፉንም የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዕለታዊ መግለጫ አስታውቋል።ሃገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 65 ደርሷል።በትናንትናው ዕለትም 85 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሃገሪቱ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 934 ደርሷል።
የቀጥታ ሽፋን
ስለ ቫይረሱ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠውን መተግበሪያ 6.5 ሚሊዮን ሰዎች ጭነዋል
ኮሮናቫይረስ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ላላቸው ሰዎች ማስጠንቀቂያ የሚሰጠውን መተግበሪያ ከ6.5 ሚሊዮን በላይ ጀርመናውያን በስልካቸው ላይ ጭነዋል።
ይህም ከአጠቃላይ ሕዝቡ ሰባት በመቶው ነው።
የመተግበሪያው ዋና ኃላፊ ክርስችን ክሌን እንዳሉት፤ በስድስት ሳምንት ተሠርቶ ያለቀው መተግበሪያ ትልቅ ስኬት ነው።
የጤና ሚንስትሩ ጄንስ ስፔን ኮሮናቫይረስን ማዳከሚያ መንገድ ነው ብለዋል።
በጀርመን መተግበሪያውን የጫኑ ሰዎች ቁጥር ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ይበልጣል።
‘ኮሮና ዋርን’ የተባለው መተግበሪያ ብሉቱዝ በመጠቀም፤ ኮሮናቫይረስ ካለበት ሰው ጋር በሁለት ሜትር ሲቀርቡ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
"ከፕሪሚየር ሊጉ ይልቅ ሕይወት የበለጠ ዋጋ አለው"
የኬንያ መንግሥት ቃል አቀባይ ሴረስ ኦጉና ዛሬ ማታ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በመጠጥ ቤቶች ውስጥ ለመመልከት ተስፋ አድርገው የነበሩ ኬንያውያንን ተስፋ አጨልመዋል።
ፕሪሚየር ሊጉ ለ100 ቀናት ተቋርጦ ቆይቶ ሲጀመር የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚል ደጋፊዎች ባልተገኙበት፣ በዝግ ስታዲየም፣ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የመንግሥት ቃል አቀባዩም አገሪቱ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት ያስቀመጠችውን መመሪያ ተከትሎ መጠጥ ቤቶች ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ገልፀው "በኮሮናቫይረስ ከመሞት ጨዋታዎቹ ቢያመልጣችሁ" ይሻላል ብለዋል።
አክለውም "ከፕሪሚየር ሊጉ ይልቅ ሕይወት የበለጠ ዋጋ አለው" በማለት የእግር ኳስ አፍቃሪያን እንዲታገሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ኡጉና መንግሥት ያስቀመጠውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመከታተል የተቋቋመው ኮሚቴ መጠጥ ቤቶች የሚከፈቱበትን ሁኔታ ላይ እንደሚመክር ይታውቀዋል።
የሆንዱራስ ፕሬዝዳንት በኮሮናቫይረስ ተያዙ
የሆንዱራንስ ፕሬዝዳንት ዩዋን ኦርላንዶ ሄርናንዴዝ እርሳቸው፣ ባለቤታቸው እንዲሁም ሁለት ረዳቶቻቸው በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ገለፁ።
በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር፣ በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ ሕመም እንደተሰማቸው በመግለጽ ትናንት ባደረጉት ምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ሄርናንዴዝ አሁን ጤንነታቸው ጥሩ መሆኑንና ከቤታቸው ሆነው እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
" በፈጣሪ፣ በሆንዱራስ ሐኪሞችና መድሃኒት" አምናለሁ በማለትም ጠንክረው ቫይረሱን እንደሚዋጉ እናም እንደሚያሸንፉ ለሕዝባቸው አስታውቀዋል።
ሆንዱራስ 9 ሺህ 600 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ ከእነዚህም መካከል 330 ሰዎች ሞተዋል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለ100 ቀናት ያህል ተቋርጦ ቆይቶ ዛሬ ይጀመራል
የእግር ኳስ አድናቂዎች ዛሬ የደስታቸው እለት ይመስላል!
በርግጥ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቀድሞ በሚታወቅበት መልኩ ባይሆንም ጨዋታዎቹ ዛሬ ይጀምራሉ።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት በሚል በአጠቃላይ ጨዋታዎች በዝግ ስታዲየም የሚካሄዱ ይሆናል።
የጥቁር አሜሪካውያንን ተቃውሞ በመደገፍ ደግሞ 12 ጨዋታዎች ላይ የሁሉም ተጫዋቾች ቲሸርት ጀርባ ላይ የሚሰፍረው ስማቸው ቀርቶ "ብላክ ላይቭስ ማተር" በሚል ጽሁፍ ይተካል።
ዛሬ አስቶን ቪላ ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የውድድር ዘመኑ በፈረንጆቹ ሐምሌ 26 ከማለቁ በፊት ባሉት አርባ ቀናት ውስጥ ለመካሄድ ከተያዙት 92 የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ቀዳሚው ነው።
ከመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች በፊት በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት የሚደረግ ሲሆን፣ በስፖርት ቁሳቁሶች ላይ ደግሞ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ሰራተኞችን ለማመስገን የልብ ቅርፅ ያለው ባጅ ይቀመጣል።
የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾችና ሰራተኞች በየስምንት ውድድሮች ሁለት ጊዜ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የሚደረግላቸው ይሆናል።
እስካሁን ድረስ በተደረገው 8687 ምርመራ 16 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
ቢቢሲ አራት የሊጉን ጨዋታዎች ለማስተላለፍ ፈቃድ አግኝቷል።
ኬንያ ከ‹‹አሊባባው ጃክ ማ የተላከልኝን እርዳታ›› ተሰርቄያለሁ አለች
የኮሮናቫይረስ ጽኑ ህሙማንን ህይወት ይታደጋል የተባለውን መድኃኒት የዓለም ጤና ድርጅት ተቀበለው
በኤርትራ አስራ አንድ ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ
በኤርትራ ከሱዳን በቅርቡ ለተመለሱና በአዲባራና ጋሽ ባርካ ለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ ሰዎች በተደረገ ምርመራ አስራ አንድ ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሃገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አሳውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ወደ አስመራ የገባ አንድ ግለሰብም በቫይረሱ መያዙ ተገልጿል።
በሃገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 121 አድርሶታል። ከነዚህም ውስጥ 39ቱ አገግመዋል።
ከሌላ ሃገራት በተለያዩ መንገዶች ወደ ሃገሪቷ የሚገቡ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘትም አሳሳቢም ነው ተብሏል። ኤርትራ ወደ ሃገሯ የሚያስገቡ ድንበሮችን ብትዘጋም በህገወጥ የሚገቡ ሰዎች ግን ማቆም እንዳልተቻለ አሳውቀዋል። በባለፉትት ወራትም 7ሺህ 765 ሰዎች ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 3 ሺህ 406ቱ በሃገሪቱ በሚገኙ 47 የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።
በቤጂንግ የተነሳው አዲስ ወረርሽኝ ተከትሎ ተነስቶ የነበረው የጉዞ እገዳ ተጣለ
ፕሬዝዳንት ፑቲንን ለመጎብኘት የሚፈልጉ ሁሉ በጸረ ተህዋሲያን ጉም ውስጥ ያልፋሉ
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል በሚል ልዩ የፀረ ተህዋሲያን የሚረጭ መተላለፊያ መዘጋጀቱ ተገለፀ።
ማንኛውም ፕሬዝዳንቱን ለመጎብኘት የሚፈልግ ባለሥልጣን ከሞስኮ ውጪ በሚገኘው የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት መሄድ ይኖርበታል።
ከዚህ ቤት ውጪም የተዘጋጀ መተላለፊያ ሲኖር በዚህ መተላለፊያ ውስጥ በመግባት የለበሱትን እንዲሁም ከልብስ ውጪ ተጋልጦ የሚገኝን የአካል ክፍል በፀረ ተህዋሲያን ማስፀዳት የግድ መሆኑን ሪያ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የዜና ወኪሉ ሁኔታውን ሲገልፀው ፀረ ተህዋሲያኑ እንደዳመና ያለ ፈሳሽ መሆኑን በመግለጽ የሰዎችን ልብስና የተጋለጠ አካል በሙሉ ያለብሳል ብሏል።
ይህ የተገለፀው የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ድሚስትሪ ፔስኮቭ በሚያዚያ ወር ላይ ማንኛውም ፕሬዝዳንቱን የሚያገኝ ሰው ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ በምርመራ መረጋገጥ አለበት ካሉ በኋላ ነው።
ሩሲያ 500,000 በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ ይህም ከአሜሪካና ከብራዚል ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር የተገኘባት አገር አድረጓታል።
ለፕሬዝዳንቱ የተገጠመው መተላለፊያ እንዴት እንደሚሰራ ይመልከቱ
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት "በቫይረሱ ለሚሞቱ ሰዎች ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው" ተባለ
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ዋነኛ ተቃዋሚ ጁሊየስ ማሌማ የአገሪቱ መንግሥት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን እከፍታለሁ ማለቱን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ "በኮሮናቫይረስ ለሚሞቱ ሰዎች ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ብሏል።
ጁሊየስ ማሌማ እንዳለው ሲሪል ራማፎሳ "በግላቸው ኃላፊነቱን ይወስዳሉ" ያላቸው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የሚዘውሩት "የነጮችን የሃብት የበላይነት የሚደግፉ ናቸው" በማለት ወርፏቸዋል።
ፖለቲከኛው ይህንን ያለው በትናንትናው ዕለት የወጣቶች ቀን በሚከበርበት ክብረ በዓል ላይ ባደረገው ንግግር ነው።
ለጥቁሮች ምጣኔ ኃብት እኩልነትና ፍትሃዊነት የሚታገለው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ፓርቲ መሪ የሆነው ጁሊየስ ደቡብ አፍሪካውያን ራሳቸውንም ሆነ የሚወዷቸውን ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ ከቫይረሱ እንዲጠብቁ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ከዚህም በተጨማሪ ሃገሪቷ ጥላው የነበረውን የመጠጥ ሽያጭ እግድም እንደገና መጣሏን ደግፏል። የመጠጥ ሽያጭ እግዱ ከሁት ሳምንት በፊት ተነስቶ የነበረ ሲሆን፤ እግዱ መነሳቱን ተከትሎ የተስፋፋው ወንጀልና ጥቃት መጨመሩን ተከትሎ ነው ውሳኔው የተቀለበሰው።
ሃገሪቷ ትምህርት ቤቶችና የአምልኮ ቦታዎችን ለመክፈት መወሰኗንም ፖለቲከኛው ተቃውሟል። ምንም እንኳን ከአስር ቀናት በፊት ትምህርት ቤቶች ቢከፈቱም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸውን ተከትሎ እንዲዘጉ ተወስኗል።
ናይጄሪያ የአምልኮ ቦታዎችን ላለመክፈት ወሰነች
በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባት በናይጄሪያዋ መዲና ሌጎች የአምልኮ ቦታዎች እንዳይከፈቱ ተወስኗል።
ቤተክርስቲያኖችና መስጊዶች በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለመክፈት እቅድ ቢኖርም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ላልተወሰነ ጊዜ የአምልኮ ቦታዎቹን ያለመክፈት ውሳኔ ላይ እንዳደረሳቸው አስታውቀዋል።
በናይጄሪያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 ሺህ 600 የደረሰ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ደግሞ በሌጎስ ይገኛሉ ተብሏል።
የቫይረሱን መዛመት ለመግታት ሃገሪቷ አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔን አስተላልፋ የነበረችው መጋቢት ወር ላይ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት ግን የአምልኮ ቦታዎችና ሆቴሎች ይከፈታሉ የሚል ውሳኔ ተላልፎ ነበር።
ሃገሪቷ የምታደርገው የምርመራ ቁጥር የጨመረ ሲሆን እስካሁንም 100 ሺህ የላብራቶሪ ምርመራ አድርጋለች። ብዙዎች ግን ቁጥሩ ትንሽ ነው በማለት እየተቹ ነው። ከሌጎስ ባሉ ቦታዎች ተጥለው የነበሩ መመሪያዎች የተወሰኑት ይነሳሉ።
በለይቶ ማቆያ ያሉ የጤና ባለሙያዎች መሠረታዊ ፍላጎታችን እየተሟላ አይደለም አሉ
ወንጀለኛን ከማደን ጋር የሚመሳሰለው ወረርሽኝን የመቆጣጠሪያ መንገድ
እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች
የቢቢሲ አማርኛ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ አበይት መረጃዎችን ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ከመላው ዓለም በመሰብሰብ ወደ እናንተ ያደርሳል።
እናንተም በማንበብ መረጃ፣ ጥቆማና አስተያየት በመስጠት አብራችሁን ሁኑ!
ቤተሰብ ወዳጆቻችሁም እንዲሁም ራሳችሁ በጤና እንድትቆዩ የሕክምና ባለሙያዎችና መንግሥት የሚሰጡዋቸውን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ አትርሱ።
መልካም ቀን ከቢቢሲ አማርኛ ጋር!