በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 4 ሺህ ተጠጋ

በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስር እጥፍ ጭማሬ እያሳየ ባለበት በዚህ ወር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ወደ አራት ሺህ ተጠግቷል። በዛሬው ዕለት 195 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎም ቁጥሩንም 3ሺህ 954 አድርሶታል። በዛሬው ዕለትም ሁለት በህክምና ማዕከል የነበሩ ሰዎች ህይወት ማለፉንም የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዕለታዊ መግለጫ አስታውቋል።ሃገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 65 ደርሷል።በትናንትናው ዕለትም 85 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሃገሪቱ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 934 ደርሷል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

  2. በሺዎች የሚቆጠሩ ቱኒዝያውያን ጤና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ መቱ

    በሺዎች የሚቆጠሩ ቱኒዝያውያን ጤና ባለሙያዎች በመላው ሃገሪቱ የስራ ማቆም አድማ መትተዋል።

    መንግሥታቸውንም የሃገሪቱን የጤና ስርአቱ እንዲያሻሽልም እየጠየቁ ነው።

    ዶክተሮች፣ ነርሶች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጡ ሠራተኞች በመዲናዋ ቱኒስ በሚገኘው የጤና ሚኒስቴር ደጃፍ ላይም በመሰብሰብ በዚህ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ቀጥታ የገፈቱ ቀማሽ እነሱ እንደመሆናቸው መጠን የአሰራር ሁኔታዎች ሊሻሻል ይገባል ብለዋል።

    ቱኒዝያ በኮሮናቫይረስ ይህንን ያህል የተጠቃች ባይሆንም አምሳ ዜጎቿን አጥታለች።

    ሃገሪቷ በዚህ ሳምንትም የቫይረሱን መዛመት ለመግታት ጥላቸው የነበሩ መመሪያዎችን አላልታለች።

  3. በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ ፊልሞች ዳግም ቀረጻ ጀምረዋል

    ኮሮናቫይረስ የመዝናኛ ኢንደስትሪን ክፉኛ ጎድቶታል። ባለ ትልልቅ በጀት የተሰሩ ፊልሞች ለእይታ የመብቂያ ጊዜያቸውን አራዝመዋል።

    ሙላን፣ ፋስት ኤንድ ፉውሪየስ 9፣ ኤ ኳይት ፕሌስ 2፣ እና የጀምስ ቦንድ ፊልም ከዘገዩት መካከል ናቸው።

    በየካቲት ወር አዲሱ የሚሽን ኢምፖሲብል ቀረጻው ቆሟል።

    አሁን ግን እነዚህ ባለትልልቅ በጀት ፊልሞች ዳግም ቀረፃቸውን ጀምረዋል።

    ሁሉም የአካላዊ ርቀታቸውን በጠበቀ መልኩ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

    ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የጀምስ ካሜሮን የሳይንስ ፊክሽን ፊልም አቫተር 2 በኒውዚላንድ ቀረፃውን በዚህ ሳምንት ጀምሯል።

    ኒውዚላንድ ከኮሮናቫይረስ ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆኗን በማወጇ ቀረጻው መጀመሩ ተገልጿል።

  4. በአዲስ አበባ እስካሁን ድረስ 2887 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል

    በአዲስ አበባ እስካሁን ድረስ በተደረጉ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች 2887 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

    ባለፉት 24 ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ የኮቪድ-19 የተገኘባቸው 144 ሰዎች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል ሶስት ሰዎች የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ 40 ሰዎች በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን የተቀሩት 101 ሰዎች የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክም ሆነ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውን ጤና ቢሮ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

    ጤና ቢሮው ባወጣው እለታዊ መረጃ መሰረት ከአስሩ ክፍለ ከተሞች በኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚ የሆነው አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሲሆን፣ 666 ሰዎች በመያዝ ቀዳሚ ሆኗል።

    በመቀጠል ደግሞ ቦሌ ክፍለ ከተማ 437 ሰዎች እንዲሁም 308 ሰዎች ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በቫይረሱ ተያዘው መገኘታቸውን ቢሮው በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

  5. በአፍሪካ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እግር ተወርች የታሰረው የሆቴል ዘርፍ

    በአፍሪካ የሆቴል ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 40 በመቶ እንደሚቀንስ ተገለፀ።

    ከዚህ በፊት በዚህ የጎርጎሳውያን አመት ከፍተኛ እድገት እንደሚያሳይ ተተንብዮ የነበረው ዘርፉ አሁን ያለበት ሁኔታ ፈፅሞ ከተገመተው ውጪ ነው ተብሏል።

    በ2020 የመጀመሪያ ወራት ላይ በአፍሪካ 78 ሺህ ክፍሎች ያሏቸው 408 ሆቴሎችን ለመገንባት ያቀዱ ባለሃብቶች ነበሩ።

    ነገር ግን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እቅዱ ወደ ኋላ ተመልሶ 90 ሆቴሎች ብቻ ይገነባሉ ተብሏል።

    የመዝናኛ ኢንዱስትሪው ላይ ጥናት ያደረገው ደብሊው ሆስፒታሊቲ የተባለ ድርጅት እነዚህም ግንባታዎች ቢሆኑ ግማሽ ያህሉ ይዘገያሉ ብሏል።

    ባለፈው ዓመት ትልልቅ ስም ያላቸው ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በአፍሪካ 68 ሆቴሎችን የገነቡ ሲሆን ይህም ከጎርጎሳውያኑ 2018 ጋር ሲነጻጸር የ40 በመቶ ብልጫ ነበረው።

    ደብሊው ሆስፒታሊቲ የሆቴሎች እንቅስቃሴ በተላለፉ የእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት ተጎድቷል ያለ ሲሆን፣ የድንበሮች መዘጋት፣ የበረራዎች መቋረጥ፣ ቱሪስቶች እንዳይመጡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችም እንዳይበረታቱ አድርጓል ሲል አክሏል።

    ማሪዮት ኢንተርናሽናል በአፍሪካ በመጪዎቹ ሶስት አመታት 2 ቢሊየን ዶላር ለማፍሰስና አዳዲስ ሆቴሎችን ለመገንባት እቅድ ይዟል።

  6. የአማዞን ቀደምት ህዝቦች መሪና መብት ታጋይ በኮሮናቫይረስ ሞቱ

    በብራዚል በአማዞን አካባቢ የሚኖሩ ቀደምት ህዝቦች መሪና የመብት ታጋይ ፓውሊኖ ፓይካን በኮሮናቫይረስ ሞቱ።

    የ66 አመቱ መሪ የአማዞን ጫካ እንዳይመነጠር እንዲሁም የቀድምት ህዝቦችን ጥቅምም በማስቀደምም ብዙ ታግለዋል።

    በብራዚል የሚገኙት የካያፖ ቀደምት ህዝቦች መሪ የነበሩ ሲሆን በአለም ማህበረሰብ ዘንድም ዕውቅናን ያተረፉትም በጎርጎሳውያኑ 1980ዎቹ ላይ ሊገነባ የታሰበው የአለም ትልቁ ግድብን መቃወማቸውን ተከትሎ ነው።

    ቦሌ ሞንቴ የተባለው የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ቢሰራ በቀደምት ህዝቦች ላይ እንዲሁም ዚንጉ በተባለው ወንዝ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳትም በተመለከተም ከፍተኛ ስራን ሰርተዋል። ይህንንም ተከትሎ የግድቡ እቅድ እንደገና የተከለሰ ሲሆን የግድቡ ግንባታ የተጀመረውም በጎርጎሳውያኑ 2016 ነው።

    በአካባቢው በህገወጥ መልኩ በማዕድን ቁፋሮ የተሰማሩትንና የተፈጥሮ ሃብት የሚያወድሙትን ብዙ ታግለዋል።

    በብራዚል ዲሞክራሲ ምሰረታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት የቀደምት ህዝቦች መሪው በተለይም በአማዞን አካባቢ የቀደምት ህዝቦች ቦታዎች እንዳይነኩም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

    በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተመታችው ብራዚል በተለይም ቀደምት ህዝቦቿንም በከፍተኛ ሁኔታ አጥቅቷቸዋል።

    በሃገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 955 ሺህ ሲሆን 46 ሺህ 500 ዜጎቿም ህይወታቸውን አጥተዋል።

  7. የቤይጂንግ ነዋሪዎች ስለምን የሳልመን አሳን መመገብ ፈሩ?

    በቤጂንግ ባለፈው ሳምንት በርካታ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ሁሉም ታማሚዎች ከአንድ ትልቅ የጅምላ ምግብ መሸጫ ጋር የተያያዙ ናቸው ተብሏል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ቫይረሱ በምግብ መሸጫው ውስጥ በአንድ ከባህር ማዶ የሚመጡ ሳልመን አሳዎችን ለመቆራረጥ የሚያገለግል መቆራረጫ ላይ መገኘቱን ከዘገቡ በኋላ ፍርሃት ነግሷል።

    በቤጂንግ የሚገኙ ሱፐር ማርኬቶችና ምግብ ቤቶች ወዲያውኑ ከመደርደሪያቸውና ከምግብ ዝርዝራቸው ላይ ሳልመንን አስወግደዋል። ከአውሮፓም የሚመጣው የሳልመን ምርት እንዲቆም ተደርጓል።

    ረቡዕ እለት በቤጂንግ አቅራቢያ በበረዶ የሚቀመጡ የባህር ምግቦችን የሚያፀዳ የ22 ዓመት ልጅ በቫይረሱ መያዙ በምርመራ መረጋገጡ ተገልጿል።

    ነገር ግን የቻይና በሽታ መቆጣጠሪያ መሥሪያ ቤት ከውጪ የሚገባው የሳልመን አሳ ምርት የኮሮናቫይረስ ሊገኝበት ይችላል ማለት ፈጽሞ አዳጋች መሆኑን አስታውቋል።

  8. ማስክ ለማድረግ ፍቃደኛ ያልሆነው ተጓዥ ከአውሮፕላን እንዲወርድ ተደረገ

    በበረራ ወቅት የፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል አላደርግም ያለው ተጓዥ ከአሜሪካን ኤርላይንስ አውሮፕላን እንዲወርድ ተደርጓል።

    ይህ ግለሰብ ማስክ አላደርግም በማለቱ ከአውሮፕላን እንዲወርድ የተደረገው የመጀመሪያው ሰው ነው ተብሏል።

    ብራንደን ስታርክ የተባለው ግለሰብ አውሮፕላኑ ከኒው ዮርክ ወደ ዳላስ የሚያደርገውን በረራ ከመጀመሩ በፊት ከአውሮፕላኑ እንዲወርድ ተጠይቋል።

    በትዊተር ላይ በርካታ ተከታዮች ያሉት ወግ አጥባቂው አክቲቪስት ብራንደን ስታርክ ያጋጠመውን በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል። አጋጣሚውንም "እብደት ነው" ብሎታል።

    በዛው በረራ ላይ የነበረው የኒው ዮርክ ታይምስ ሪፖርተር፤ የብራንደን ስትርክን አቋም በመተቸት አውሮፕላኑ ውስጥ የተከሰተውን የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ሚዲያው ላይ አውጥቷል።

    ምንም እንኳ ተጓዦች ማስክ ማድረግ አለባቸው የሚል ሕግ አሜሪካ ባይኖራትም፤ አየር መንገዶች ግን ራሳቸው የሚያስፈጽሙትን ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አሜሪካን ኤርላንይንስ እና ሌሎች አምስት አየር መንገዶች ማስክ አላደርግም ያለ ተጓዥ እንደማያሳፍሩ አሳውቀዋል።

    በጤና ምክንያት ማስክ ማድረግ የማይችሉ ግን ይህ አይመለከታቸውም ተብሏል።

  9. ዴክሳሜታዞን ምን ያህል አስተማማኝ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥስ ይገኛል?

  10. ዴክሳሜታሶን ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ስለሚውልበት ሁኔታ ባለሙያዎች ሐሳብ አቀረቡ

  11. ቀባሪን ያጡትን አለሁላችሁ ያለው ብራዚላዊው አስከሬን ሰብሳቢ

  12. በኢትዮጵያ ተጨማሪ 195 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 4853 የላብራቶሪ ምርመራ 195 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 3ሺህ 954 አድርሶታል።

    በዛሬው ዕለትም ሁለት በህክምና ማዕከል የነበሩ ሰዎች ህይወት ማለፉንም የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዕለታዊ መግለጫ አስታውቋል።

    ሃገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 65 ደርሷል።

    በትናንትናው ዕለትም 85 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሃገሪቱ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 934 ደርሷል።

  13. በሩሲያ 489 የጤና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ መሞታቸው ተነገረ

    በሩሲያ 489 የጤና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ መሞታቸውን የሃገሪቱን የጤና አገልግሎት በበላይነት የሚያየው የፌደራል መቆጣጠሪያ ማዕከል ሮስድራቭናድዞር አስታውቋል።

    በባለፈው ወር 101 የጤና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ መሞታቸው ተገልፆ የነበረ ሲሆን በአንድ ወር ውስጥም ከሶስት መቶ በላይ መሞታቸው ድንጋጤን ፈጥሯል።

    የሮስድራቭናድዞር ዋና ኃላፊ አላ ሳሞይሎቫ እንዳሳወቁት ለሞቶቹ የኮሮናቫይረስ የህክምና መከላከያ ቁሳቁሶች በጊዜው አለመቅረባቸው አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።

    "እውነቱን ልናገር ካልኩ መጀመሪያ ወቅት አካባቢ ችግሮች ተከስተው ነበር" ብለዋል።

    በሃገሪቱ ከ561 ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን በባለፉት 24 ሰዓታትም 7ሺህ 790 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ይህ አሃዝም በአለም ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል። ሃገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎችም 7ሺህ 760 ነው።

  14. ደቡብ አፍሪካ ምግብ ቤቶች እና የውበት ሳሎኖች እንዲከፈቱ ፈቀደች

    የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲይረል ራማፎሳ የኮሮናቫይረስ ሰርጭትን ለመግታት ታስቦ ተጥሎ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ማላላታቸውን ቀጥለዋል።

    ምግብ ቤቶች ደንበኞቻቸው ተቀምጠው ማስተናገድ እንዲችሉ ይፈቀዳል ብለዋል። ከዚህ ቀደም ምግብ አዘው ይዘው ለሚሄዱ እንጂ ምግብ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ለሚጠቀሙት ፍቃድ አልተሰጠም ነበር።

    ከዚህ በተጨማሪም ጸጉር ቤቶች፣ ቁማር መጫወቻ ቤቶች እና ሲኒማ ቤቶች ዳግም እንደሚከፈቱ ተጠቁሟል።

    ለሥራ ተብለው የሚከናወኑ ስብሰባዎችም፣ ንክኪ የሌላቸው እንደ ሜዳ ቴኒስ እና ጎልፍ ያሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችም ፍቃድ ያገኛሉ።

    ፕሬዝደንቱ ከላይ የተጠቀሱት ገደቦች የሚነሱበት ቀን ይፋ ይደረጋል ሲሉ ለህዝባቸው በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።

    ደቡብ አፍሪካ እስካሁን ከ80 ሺህ በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ያገኘች ሲሆን፤ ከ1ሺህ 6መቶ በላይ ሞት ተመዝግቧል።

  15. ማኅበራዊ ሚዲያዎች የማኅብረሰቡን ጤና አደጋ ላይ ይጥላሉ ተባለ

    እንደ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለ ኮሮናቫይረስ ያልተረጋገጡ ሃሳቦችን ለማሰራጨት ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ለማኅበረሰቡ የጤና ስጋት መሆናቸውን አንድ ጥናት አረጋገጠ።

    የለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ ጥናት እንዳሳየው ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ዜናዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚያገኙ ሰዎች የእንቅስቃሴ ገደብን በተደጋጋሚ ሲጥሱ ታይተዋል።

    በዚህም እራሳቸውን እና ሌሎችን ለቫይረሱ ሊያጋልጡ ይችላሉ።

    ይህ ጥናት የተካሄደው በብሪታኒያ ሲሆን ለጥናቱ ግብዓት የሚሆኑት መረጃዎች የተሰበሰቡት ደግሞ በሚያዚያ እና ግንቦት ወራት ውስጥ ነው።

    በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች 'ኮቪድ-19 በሽታን የሚያስከትለው ቫይረስ ከላብራቶሪ ነው የመጣው አልያም የበሽታው ምልክት የሚባሉት በ5ጂ የሞባይል ኔትዎርክ ጨረር የሚከሰቱ ናቸው ብለው ያምናሉ ወይ?' የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

    ኮሮናቫይረስ ከላብራቶሪ መውጣቱ ወይም የበሽታው ምልክት የሚከሰተው ለ5ጂ ኔትዎርክ ጨረር በመጋለጣችን ነው ብለው የሚያምኑ በርካቶች አሉ።

    ጥናቱ እንዳረጋገጠው ይህ አይነት እምነት ያላቸው ሰዎች ዜናዎችን በዋናነት የሚያገኙት ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ነው።

    ዩቲዩብ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከገጹ ላይ ሲያነሳ ቆይቷል።

  16. የወባ መድኃኒት ለኮሮናቫይረስ ህክምና ለማዋል ሲደረግ የነበረው ጥናት ተቋረጠ

    የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን ለማከም ይረዳል በተባለለት ሃይድሮክሎሮኪን ላይ ያደርግ የነበረውን ጥናት ማቋረጡን አስታወቀ።

    ጸረ-ወባ የሆነው መድኃኒት በሽታውን ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ የታመሙትን ለማከም ሊውል ይችላል የሚል ሰፊ ቅድመ ግምት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ በጥናት ሳይረጋገጥ ቆይቷል።

    ፕሬዝደንት ትራምፕን በተደጋጋሚ መድኃኒቱ ፈዋሽ ስለመሆኑ እና እርሳቸው ይወስዱት እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል።

    የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለ ከሆነ በመድኃኒቱ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደጠቆሙት ሃይድሮክሎሮኪን የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን አልታደገም።

    "ሃይድሮክሎሮኪን በሆስፒታል የሚገኙ የኮቪድ-19 ታማሚዎችን የሞት መጠን መቀነስ አልቻለም" ብሏል ጅርጅቱ ባወጣው መግለጫ።

    ዘ ላንሴት የተሰኘው እውቅ የህክምና መጽሔት ሃይድሮክሎሮኪን የኮቪድ-19 ታማሚዎችን ከመፈወስ ይልቅ የሞት መጠንን ይጨምራል የሚል የጥናት ውጤትን ይፋ ካደረገ በኋላ የዓለም ጤና ድርጅት በሙከራ ደረጃ ለታማሚዎች መድኃኒቱ እንዳይሰጥ ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

    ከዚያም የላንሴት የጥናት ውጤት ጉድለት አለበት መባሉን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት በሃይድሮክሎሮኪን ላይ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቷል።

  17. ዴክሳሜታሶን በተባለው መድኃኒት ኅብረተሰቡ መዘናጋት የለበትም ተባለ

    ዴክሳሜታሶን ስለተባለውና ብዙ ስለተነገረለት መድኃኒት ዝርዝር ሁኔታና በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ስለሚውልበት መንገድ ምርመራ በማድረግ ሃሳብ እንዲያቀርቡ የተጠየቁት ባለሙያዎች፤ የደረሱበትን ውጤት ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማቅረባቸው ተሰማ።

    በጤና ሚኒስቴር የህክምና ግልጋሎት ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ ያዕቆብ ሰማን ለቢቢሲ እንደገለጹት የጤና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ መድኃኒቱ እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ጥናት አቅርበዋል ይሁን እንጂ በመድኃኒቱ ምክንያት ኅብረተሰቡ መዘናጋት የለበትም ብለዋል።

    "በማኅበረሰቡ ዘንድ መዘናጋትን እንዳይፈጠር እና አሁንም ዋነኛው መተኮር ያለበት መንገድ ባለሞያዎች የሚሰጧቸውን የመከላከያ እርምጃዎች መተግበር ነው ሲሉ" ገልጸዋል አቶ ያዕቆን።

    የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ዴክሳሜታሶን በኮቪድ-19 ተይዘው በጽኑ የታመሙ ሰዎችን ለማከም ሊውል ይችላል ማለታቸውን ይታሳል።

    በአሜሪካ አገር የድንገተኛ ክፍል እና የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት እና የጤና ጥበቃ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ጽዮን ፍሬው እንደሚሉት ይህ የምርመር ውጤተ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ገና ቁንጽል የጥናት ውጤት በመሆኑ ሕብረተሰቡ በዚህ ሊዘናጋ አይገባም በማለት ይመክራሉ።

    ስለዚህም ከበሽታው ሊጠብቁን የሚችሉት "በቤት መሆን፣ የአፍና የአፍንጫ መሰፈኛ ጭምብል ማድረግ፣ የእጅ ንጽህናን መጠበቅ . . . እነዚህ ነገሮች እንደሚሰሩ እናውቅለን። ለአሁኑ የሚሰሩት ነገሮች ላይ ብናተኩር ጥሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

  18. በወረርሽኙ የሞቱ ሰዎች አሃዝ እስካሁን ከተነገረው በላይ ነው ተባለ

    በይፋ ከተነገረው 440 ሺህ ሟቾች በተጨማሪ 130 ሺህ ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ መሞታቸውን የቢቢሲ ጥናት አረጋገጠ።

    ከ27 አገራት የተገኘ የሞት መጠንን የተመለከተው ጥናቱ፤ በቫይረሱ ምክንያት በይፋ ህይወታቸውን አጥተዋል የተባሉት ሰዎች ቁጥር በላይ ሰዎች መሞታቸውን ጥናቱ ደርሼበታለሁ ብሏል።

    ይህ ማለት መንግሥታት ከሚሉት በላይ በቫይረሱ ሳቢያ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

    ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎችን አሃዝ ለማወቅ፤ ምን ያህሉ ተመርምረው እንደነበረ ቀድሞ ማወቅ ግድ ይላል ተብሏል።

    ከዚህ በተጨማሪም መንግሥታት በቫይረሱ ምክንያት ከጤና ተቋማት ውጪ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር የማካተታቸው አጋጣሚ አነስተኛ ስለሆነ በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በትክክል ማወቅ ከባድ ያደርገዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በቢቢሲ በይፋ ከተነገረው በተጨማሪ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያ 130 ሺህ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጧል።

    የቫይረሱ ስርጭት በላቲን አሜሪካ፣ ሕንድ እና አፍሪካ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በመንግሥታት ሪፖርት የማይደረጉ የሟቾች ቁጥር መጨምሩን እንደሚቀጥል ተገምቷል።

  19. በአውስትራሊያ ቫይረሱ በማኅብረሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ ነው ተባለ

    አውስትራሊያን ውጤታማ በሆነ መልኩ የቫይረሱን ስርጭት መግታቷን በተደጋጋሚ ተነግሯል።

    ይሁን እንጂ ቪክቶሪያ ተብሎ በሚጠራው የአውስትራሊያ ግዛት ቫይረሱ አሁንም በማኅብረሰቡ ውስጥ እየተስፋፋ ይገኛል ተብሏል።

    በአገሪቱ ሁለተኛዋ በርካታ ነዋሪዎች ያሉቷ የቪክቶሪያ ግዛት አስተዳዳሪዎች ግን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው ቢሉም ከዕለት ወደ ዕለት በኮሮናቫይረስ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት 12 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

    አውስትራሊያ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ ተይዘው የሚገኙ 500 ሰዎች ብቻ ይገኙባታል። አብዛኛዎቹም ከሌሎች አገራት የተመለሱ እና በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎች ናቸው ተብሏል።

  20. ሕንድ በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ ከፍተኛ የሰዎች ቁጥር መዘገበች

    በሕንድ እና በላቲን አሜሪካ አገራት የቫይረሱ ስርጭት በስፋት እየተሰራጨ ነው። በሕንድ ባለፉት 24 ሰዓታት እስካሁን ድረስ ያልታየ በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

    በአንድ ቀን 12 ሺህ 881 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን የሕንድ የጤና ተቋማት ከአቅማቸው በላይ በታማሚዎች ብዛት ተጨናንቀዋል።

    በደልሂ እና ሙምባይ የሚገኙ ሆስፒታሎች ታማሚዎችን አንቀበልም እያሉ ስለመሆኑ በስፋት ተዘግቧል።

    ሕንድ የቫይረሱ ስርጭት በጀመረበት ወቅት ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ ነበር። የእንቅስቃሴ ገደቡም ምጣኔ ሃብቷን ክፉኛ ጎድቶታል።

    በዚህም የሕንድ መንግሥት የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ተጥለው የነበሩ ገደቦች እንዲላሉ ለማድረግ ተገዷል። ይህንንም ተከትሎ ቫይረሱ እንደተስፋፋ ይነገራል።