በኢትዮጵያ 150 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው የአንድ ሰው ህይወት አለፈ

በኢትዮጵያ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁትር ከዕለት ዕለት በፍጥነት እየጨመረ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የቫይረሱ መስፋፋት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ በየዕለቱ የሚወጣው መረጃ ያመለክታል። በዚህም በአገሪቱ እስካሁን ከተመዘገበው 1637 የህሙማን ቁጥር ውስጥ ከአንድ ሺህ የሚበልጡት ከአዲስ አበባ የተገኙ ናቸው። አሁንም የቫይረሱ ስርጭት ባለበት እንዲቆም እጅን በሚገባ መታጠብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በባለሙያዎችና በመንግሥት የሚመከሩ መከላከያዎች ናቸው። ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የቀጥታ ዘገባዎቻችንን እዚህ ገጽ ላይ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በምስራቅ አፍሪካዋ አገር ታንዛንያ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ቀንሷል ተባለ

    የታንዛንያ ጤና ሚኒስትር በአገሪቱ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት መቀነሱን ጠቅሰው የንግድ ከተማ በሆነችው ዳሬ ሰላም አራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ብቻ መኖራቸውን ገለፁ።

    ኡሚ ምዋሊሙ አክለውም በታንጋ እና ምዋንዛ ግዛቶች ምንም በቫይረሱ የተያዘ ሰው አለመኖሩን ተናግረዋል።

    የታንዛንያ መንግሥት ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ባለስልጣናት ቁጥር ያጋንናሉ ብለው ከተናገሩ በኋላ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ የአገሪቱን የኮሮናቨይረስ እለታዊ መረጃ ይፋ ማድረግ አቁሟል።

    ባለፈው ወር የአሜሪካ አምባሳደር በዳሬ ሰላም የሚገኙ ሆስፒታሎች በህሙማን ተጥለቅለቀዋል በማለት በከተማዋ በኮሮናቫይረስ የመያዝ እድል ሰፊ መሆኑን ተናግረው ነበር።

    የጤና ሚኒስትሩ ምዋሊሙ ሰኞ እለት ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ፈጣሪ ታንዛንያን ታድጓል ሲሉ ተናግረዋል።

    የታንዛንያ መንግሥት ከሰኞ ዕለት ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ካስታወቀ በኋላ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል።

  2. የፌስቡክ ሠራተኞች በመሥሪያ ቤታቸው ድርጊት ተበሳጩ

  3. የጆርጅ ፍሎይድ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ

  4. ተቃውሞው የቫይረሱን ሥርጭት ሊጨምረው ይችላል ተባለ

    የአሜሪካው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ሰልፈኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ቢያደርጉም፤ በርካታ ሰዎች አንድ ላይ መሰባሰባቸው ቫይረሱን ሊያስፋፋው እንደሚችል ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

    የተለያዩ የአሜርካ ግዛቶች እንቅስቃሴ ላይ ጥለው የነበረውን ገደብ እያነሱ ነው። ወረርሽኙን መቆጣጠር ግን አልተቻለም።

    6.2 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን፤ 375,513 ሞተዋል።

    በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ በበሽታው እየሞቱ ያሉት ጥቁሮች ናቸው። ሥራ አጥ እየሆኑ ያሉትም ጥቁሮች ናቸው።

  5. ኡጋንዳ ተማሪዎች በመንደራቸው ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ቴሌቪዥን ልታድል ነው

    የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበትን ወቅት በአንድ ወር አራዘሙ።

    ፕሬዝዳንቱ ትምህርት ቤቶችን በአሁን ሰዓት መክፈት አደገኛ መሆኑን ገልፀው አገሪቱ ተማሪዎቹን በየሁለት ሳምንቱ ለመመርመር የሚያስችል መመርመሪያ እንደሌላት ገልፀዋል።

    ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ለእያንዳንዱ መንደር ሁለት ሁለት ቴሌቪዥን እንደሚሰጥ ገልፀው ይህም ተማሪዎች በመንደራቸው ሆነው እንዲያጠኑ እንደሚረዳቸው አስታውቀዋል።

    "በየመንደሩ ሁለት ቴሌቪዥን ማለት ለመላው አገሪቱ 140 000 ቴሌቪዥን ማለት ነው" ሲሉ ተናግረዋል በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር።

    የሕዝብ ማመላለሻዎች የመጫን አቅማቸውን በግማሽ ቀንሰው እንዲሰሩ ሲፈቀድ ሞተር ክብስክሌቶች ግን አሁንም ቢሆን ከእቃ ውጪ ሰዎችን እንዲጭኑ አልተፈቀደም።

    ቤተ እምነቶች፣ መስጂዶች እንዲሁም መጠጥ ቤቶች ለተጨማሪ ሀያ ቀናት ተዘግተው ይቆያሉ።

    ኡጋንዳ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን ለዜጎቿ በዚህ ወር ማከፋፈል የምትጀምር ሲሆን ማንኛውም መሸፈኛውን ያላደረገ ሰው በቤቱ እንዲቆይ ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

    ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ የእንቅስቃሴ ገደቡን ጥሰው በቁጥጥር ስር የዋሉ 4000 ሰዎች ጉዳይ ዳግም እንዲታይ የጠየቁ ሲሆን ጉዳያቸው ቀላል የሆነ ደግሞ እንዲለቀቁ አዝዘዋል።

    በተጨማሪም መንግሥት የምግብ እደላ ፕሮግራሙን እንደሚቀጥልበት አስታውቀዋል።

  6. “ዜጎች ከቫይረሱ ጋር መኖርን መማር አለባቸው” የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር

    የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ካሃን፤ በአገራቸው የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት እንቅስቃሴ ማቆም መፍትሔ እንደማይሆን ተናገሩ።

    በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም፤ ትላንት በሰጡት መግለጫ “ፓኪስታናውያን ከቫይረሱ ጋር መኖርን መማር አለባቸው” ብለዋል።

    ድሃ የአገሪቱ ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች እንቅስቃሴ መግታት የማይታሰብ ነገር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

    በፓኪስታን እስካሁን በወረርሽኙ የተያዙት 75,000 ሰዎች ሲሆኑ፤ 1,500 ሞተዋል።

    በሽታው መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንቅስቃሴ መግታትን ሲቃወሙ ነበር። የካቲት ላይ ተጥሎ የነበረ ገደብ አሁን ተነስቷል።

    የህክምና ባለሙያዎች፤ የጤና ዘርፉ ከሚችለው በላይ ሰዎች ሊታመሙ ይችላሉ ቢሉም፤ ጎዳናዎችና ገበያዎች በሰው ተጨናንቀዋል።

    ኢምራን ካሀን፤ የገበያ መደብሮች መከፈታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረው፤ ማኅበረሰቡ አካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

    በላሆሬ ከተማ የተደረገ ድንገቴ ምረመራ አምስት በመቶ ነዋሪዎች ለበሽታው ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁሟል። ይህም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያካትታል። በመላው አገሪቱ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ቁጥር በላይም ነው።

  7. ሲንጋፖር የእንቅስቃሴ ገደቡን የተላለፉ የውጪ አገራት ዜጎችን ከሰሰች

    የሲንጋፖር ባለስልጣናት አገሪቱ ያስተላለፈችውን የእንቅስቃሴ ገደብ ተላልፈው የተገኙ የውጪ አገር ዜጎችን ፍርድ ቤት አቆሙ።

    ይህ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ይረዳል የተባለ የእንቅስቃሴ ገደብ የትኛውንም መሰባሰብ ይከለክላል።

    በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ በብዛት የውጪ አገር ዜጎችና ዲፕሎማቶች በሚኖሩበት አካባቢ እነዚህ ሰዎች በአንድ የገበያ ስፍራ ተቀምጠው ሲጠጡ ፎቶግራፍ ተነስተው ነበር።

    ይህ ምስል በፌስቡክ በሰፊው ከተሰራጨ በኋላ የሲንጋፖር ዜጎች መንግሥታቸው የውጪ አገር ዜጎችን እንደማይጫን እና የተላለፈው መመሪያ የአገሪቱን ዜጎች ብቻ የሚመለከት መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ አሰምተዋል።

    የሲንጋፖር ባለስልጣናት በፎቶው ላይ የሚታዩትን ሰባት የውጪ አገር ዜጎች አፈላልገው ካገኙ በኋላ የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመከላከል የተላለፈውን መመሪያ በመተላለፍ በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት ቆመዋል።

    እነዚህ ተከሳሾች እስከ ስድስት ወር ድረስ ዘብጥያ ሊወርዱ ይችላሉ የተባለ ሲሆን በገንዘብም እስከ 7000 ዶላር ሊቀጡ እንደሚችሉ ተገልጿል።

    የሲንጋፖር ባለስልጣናት የእነዚህን የውጪ አገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ መሰረዝና ዳግም ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ እስከመከልከል ድረስ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ገልፀዋል።

  8. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች

    ቢቢሲ አማርኛ ሠላምና ጤና ይመኝላችኋል!

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያደገ ቢሆንም ባለፉት አስራ አምስት ቀናት ግን በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

    ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ጎልቶ ይታያል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከጋምቤላ ክልል ውጪ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በአጠቃለይ በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ተገኝቷል።

    በእድሜም ካየነው ከአንድ ወር ጨቅላ ጀምሮ በሰማንያዎቹ ውስጥ እስከሚገኙ አዛውንት ድረስ በቫይረሱ ተይዘዋል። ይህ እድሜን እና ጸታን እንዲሁም የመኖሪያ ስፍራን የማይለየውን ቫይረስ ለመከላከል በየጊዜው እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ወሳኝ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

    እናንተም አስፈላጊውነ ጥንቃቄ እያደረጋችሁ የቢቢሲ አማርኛ ቀጥታ ዘገባን ተከታተሉ።

    መልካም ቀን!