በአሜሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1 ሚሊዮን ደረሰ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከዓለማችን ላይ የሚጠፋ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል። እስካሁን ባለው መረጃ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲያዙ በሺዎች የሚቆጠሩም ህይወታቸውን አጥተዋል። አንዳንድ አገራት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ እያነሱ ቢሆንም አሁንም ግን ዜጎቻቸው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው እየተናገሩ ነው። በእኛም አገር አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ሊዘነጉ የሚገባቸው አይደሉም። እናንተም ጤና ወዳጆቻችሁም ደህና እንዲሆኑ ምኞታችን ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. 'ቱፓክ ሻኩር' ስራ ፈትቻለሁ ሲል አመለከተ

    የአሜሪካዋ ኬንታኪ ግዛት አስተዳዳሪ ቱፓክ ሻኩር ስራ ፈትቻለሁ ሲል ያስገባውን ማመልከቻ በቅርቡ ቀልድ ነው በሚል በማሰባቸው ይቅርታ ጠየቁ።

    " በቱፓክ ሻኩር ስም ሥራ መፍታቱን ያመለከተ ሰው አለን። ምናልባት ለጨዋታ ብሎ ይሆናል" ብለው ነበር አንዲ ቤሼይር በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት።

    ነገር ግን ስሙን በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1996 ከሞተው ከዝነኛው የአሜሪካ ራፐር ጋር የሚጋራው ግለሰብ በትክክል ስሜ ቱፓክ ማሊክ ሻኩር ነው ሲል አቤት ብሏል።

    " በጣም ነው ያፈርኩት፤ ይህ ስሜ ነው" ሲል በአካባቢው ለሚታተም ጋዜጣ ተናግሯል። ግለሰቡ ለጋዜጣው አክሎ እንደተናገረው ስራ መፍታቱን ያመለከተው ከ1 ቀን በፊት ነው።

    በአሜሪካ የኮሮናወረርሽኝን ተከትሎ ሚሊየኖች ስራ መፍታታቸው ይታወቃል።

    ሻኩር አክሎም "ባለፈው ወር ያሉብኝን ወጪዎች እንዴት አድርጌ መሸፈን እንዳለብኝ መላ ጠፍቶኝ ነው ያለሁት" ብሏል።

  2. ቬትናም ለተከታታይ 13 ቀናት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አለማግኘቷን ገለፀች

    ቬትናም አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ካገኘች 13 ተከታታይ ቀን እንዳለፋት አስታወቀች።

    95 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ቬትናም እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ 270 ሰዎች ብቻ ስታገኝ ምንም የሞተ ሰው የለም።

    የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተናገሩት አገራቸው ውጤታማ በሆነ መልኩ ቫይረሱን እያስወገደች ነው። አሁንም ግን ዜጎች ጥንቁቅ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

    ቬትናም እነ ደቡብ ኮሪያና ጀርመን እንዳደረጉት በሰፊው ምርመራ ባታደርግም ወረርሽኙ በቻይና እንደተከሰተ በረራ በማቆምና ድንበሯን በመዝጋት የመከላከል እርምጃ ወስዳለች።

    በአንድ የኮሚኒስት ፓርቲ ስር የምትተዳደረው ቬትናም በሁሉም ግዛቶቿ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ ቆይታለች።

    ባለፈው ሳምንት ጀምሮ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳት ጀምሯል።

  3. ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ለናይጄሪያ ቬንትሌተር ለመላክ ቃል ገቡ

    የናይጄሪያ ባለሥልጣናት እንዳሉት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት ለምዕራብ አፍሪካ አገራት ቬንቲሌተሮች ለመላክ ቃል ገቡ፡፡

    ከፕሬዚደንት ሙሃመዱ ቡሃሪ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ትራምፕ በወረርሽኙ ወቅት አሜሪካ ለናይጄሪያ የምታደርገውን ትብብርና ድጋፍ ማረጋገጣቸውን የናይጄሪያ ባለሥልጣናት በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡ የፕሬዚደንቱ ረዳትም የውይይታቸውን ሃሳብ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

    ፕሬዚደንት ትራምፕ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ተመሳሳይ ቃል መግባታቸው ይታወቃል፡፡

    አሜሪካ በዓለማችን በቫይረሱ ሳቢያ በርካታ ሰዎች የሞቱባት ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡ በቫይረሱ ከ56 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

    ኮቪድ -19 የመተንፈሻ አካል በሽታ በመሆኑ ሕክምናው አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎች ያስፈልጉታል፡፡ ይሁን እንጅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቬንቲሌተሮች አቅርቦት እጥረት አለ፡፡

  4. ስደተኞች የኮቪድ-19 ምርመራን በነፃ እንዲያገኙ የሚተጋው ኢትዮጵያዊ

  5. ሞተዋል የተባሉት ሴት "አልሞትኩም እህቴ ጋር ደውሉልኝ" አሉ

  6. አውስትራሊያውያን 'ንክኪ' የሚለየውን መተግበሪያ በስልካቸው ላይ እንዲጭኑ እየተጠየቁ ነው

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ሚሊዮኖች አውስትራሊያውያን ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ያላቸውን 'ንክኪ' የሚለየውን መተግበሪያ በስልካቸው ላይ እንዲጭኑ ጠየቁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ መተግበሪያውን በሰፊው መጠቀም መጀመራችን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ “ትኬታችን” ነው ብለዋል።

    አውስትራሊያ በአሁኑ ሰዓት የቫይረሱን ስርጭት የተቆጣጠረችው ሲሆን በትናንትናው ዕለት ብቻ አንድ ሰው መያዙ ተመዝግቧል።

    በአውስትራሊያ እስካሁን ድረስ 6700 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲመዘገብ ከእነዚህም መካከል 88 ሰዎች ሞተዋል።

    ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሪሰን የአገራቸው ትክክለኛ ስኬት የሚመሰረተው ዜጎች መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ ሲተገብሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

    እስካሁን ድረስ 'ንክኪ' የሚለየውን መተግበሪያ በስልካቸው ላይ የጫኑ አውስትራሊያውያን ቁጥር 2.8 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር እስካሁን ወደ ስልካቸው መተግበሪያውን የጫኑትን አመስግነው “ሚሊየኖች፣ ተጨማሪ ሚሊየኖች ተመሳሳዩን እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

    መተግበሪያውን በበጎ ያላዩ ተቺዎች ግን ይህ የግለሰብን ደህንነት ይጋፋል፤ የግል መረጃውም በአንድ ቋት በማዕከል ስለሚቀመጥና በሕክምና ባለሙያዎች ስለሚፈተሽ የግል ደህንነት አደጋ ነው ይላሉ።

    በርካታ የአውስትራሊያ ግዛቶች ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ እያላሉ ነው።

  7. በቻይና አንድም ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘ ሞት ሳይመዘገብ ዋለ

    ቻይና በትናንትናው ዕለት ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ አንድም ሞት አለማስመዝገቧን አስታወቀች።

    የአገሪቱ የጤና ኮሚሽን እንዳለው በትናንትናው ዕለት ብቻ 22 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መገኘታቸውን ጠቅሶ ከእነዚህ መካከል 21 ከሌላ አገር የመጡ መሆናቸውን አስታውቋል።

    በቻይና በኮሮና ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 4ሺህ 633 ሲሆን በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ደግሞ 82,858 ነው።

  8. አሜሪካ በአንድ ቀን ከአምስት ሚሊየን በላይ ሰዎችን ለመመርመር አቅዳለች

    በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በቬትናም ጦርነት ከሞቱት እንደሚልቅ ተገለፀ።

    በአሁኑ ሰዓት 58,220 አሜሪካውያን በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸው ታውቋል። የዋይት ሐውስ ከፍተኛ የሕክምና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ወረርሽኙ ገና ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    አክለውም ተመራማሪዎች ሁነኛ መድሃኒት ወይም መፍትሄ ካላገኙ በስተቀር እስከ ታህሳስ ወር ድረስ አስጊ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

    ዶ/ር ፋውቺ ቫይረሱ ተመልሶ እንደሚመጣ ገልፀው በፈረንጆቹ የበጋ ወርም ድራሹ ይጠፋል ብላችሁ አታስቡ ሲሉ አሜሪካውያንን አስጠንቅቀዋል።

    በተያያዘ ዜና በአሜሪካ በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ይህም ሊሆን ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ የአሜሪካ ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ (ወደ 330 ሚሊየን) በመሆኑ ነው ተብሏል።

    ሌላኛው ምክንያት ደግሞ አሜሪካ በሁለት ወር ውስጥ ድረስ 5.7 ሚሊየን ሰዎችን በመመርመሯ እንደሆነ ተገልጿል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት በቅርቡ በቀን ከአምስት ሚሊየን በላይ ምርመራዎችን አገራቸው ታካሂዳለች።

    ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ በቀን መመርመር የቻለችው 200 000 ሰዎችን ብቻ ነው።

    በአሜሪካ የኮሮናቫይረስ ለመመርመር ከግዛት ግዛት መስፈርቶቹ የሚለያዩ ሲሆን በሁሉም ግዛቶች ግን በሆስፒታል ተኝተው የሚታከሙ፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ በእስር ቤትና በእንክብካቤ ማዕከላት የሚኖሩ ቅድሚያ ያገኛሉ ተብሏል።

  9. በአማራ ክልል “ህጋዊ አሰራርን ያልተከተሉ” 7ሺህ የሚሆኑ ንግድ ቤቶች ታሸጉ

  10. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ወዳጆች

    ቢቢሲ አማርኛ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ አበይት የዓለማችንን ዜናዎች ከዚህ ሰዓት ጀምሮ በፌስቡክ ገፃችንም ሆነ በድረ ገፃችን ወደ እናንተ በቀጥታ ያደርሳል። እናንተም ራሳችሁን ከቫይረሱ እየጠበቃችሁ፣ መረጃዎቻችንን ትጋሩ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።

    ከአበይት ዜናዎቻችን መካከል፡

    • በአሜሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1,012,399 መድረሱን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሁናዊ መረጃ ያሳያል። በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 3,114,659 መሆኑ ይታወቃል።
    • ፈረንሳይ በሕዝብ ትራንስፖርትና በትምህርት ቤቶች ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ልታስገድድ ነው
    • የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኮሮናቫይረስን ለሚያክሙ ለሕክምና ባለሙያዎች የሚሆን የሰውነት መከላከያ እጥረት መኖሩን አመኑ