"በር ዘግተናል ኳረንቲን ጠቅሞናል" ያለው ኮሜዲያን ቶማስ ነው
በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ኅብረተሰቡን ለማንቃት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ አርቲስቶች የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።
ኮሜዲያን ቶማስም "በር ዘግተናል ኳረንቲን ጠቅሞናል" በማለት የበኩሉ አበርክቷል።
ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዚህ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም ከ720 ሺህ በላይ ሰዎችን ይዟል። 34 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በዚህ መካከል ደግሞ ጥቂትም ቢሆን ተስፋ የሚሰጡ ዜናዎች አይጠፉም። ይህ በእንዲህ እያለ ማንኛውም ሰው ራሱን ሌሎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የተረጋገጠው መከላከያ መንገድ እጅን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና በሚያስሉና በሚያስነጥሱበት ወቅት አፍን መሸፈን ናቸው። እናንተ ራሳችሁን ከቫይረሱ እየጠበቃችሁ በጤና ኑሩልን። ስለበሽታው ጠቃሚ ዘገባዎችን በቀጥታ ከዚህ ገጽ ታገኛላችሁ።
በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ኅብረተሰቡን ለማንቃት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ አርቲስቶች የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።
ኮሜዲያን ቶማስም "በር ዘግተናል ኳረንቲን ጠቅሞናል" በማለት የበኩሉ አበርክቷል።
በኤርትራ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች መገኘታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 15 አድርሶታል።
ዛሬ በኮቪድ-19 መያዛቸው ከተረጋገጠው ግለሰቦች መካከል ሁለቱ እድሜያቸው ከ48 እስከ 60 የሚሆኑ ወንዶች ሲሆኑ በረራ ከመታገዱ በፊት ወደ አገሪቷ የገቡ መንገደኞች መሆናቸው ተገልጿል።
ኤርትራ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች። ማንኛውንም የሕዝብ የትራንስፖርት አግልግሎትን አግዳለች። ከዚህም በተጨማሪ ከ10 ሰዎች በላይ በአንድ ላይ መሰብሰብን ከልክላለች።
የጣሊያን መንግሥት በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ ማለፉን አሳውቋል።
ይህ አሃዝ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ፣ የሞቱ እና ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን ይጨምራል።
ሲቪል ፕሮቴክሽን ኤጀንሲ የተባለው የመንግሥት አካል እንዳስታወቀው ባለፉት 24 ሰዓት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1,648 ነው።
ይህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ከ75 ሺህ እንዲሻገር አድርጎታል።
ከዚህ በተጫማሪም ኤጅንሲው ባለፉት 24 ሰዓታት 1,590 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል ብሏል።
አርብ ዕለት የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባት ሪፖርት የተደረገችው የ24 ዓመት ኢትዮጵያዊት በተደጋጋሚ በተደረገላት ምርመራ በሽታው እንደሌለባት መረጋገጡን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህች ወጣት ምንም አይነት የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላት እንዲሁም በበሽታው መያዙ ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር ንክኪ ያልነበራት በመሆኑ በድጋሚ ሦስት ጊዜ በተደረገላት የላብራቶሪ ምርመራ ሁሉም ውጤት ኔጌቲቭ በመሆኑ በቫይረሱ አለመያዝዋን ማረጋገጥ እንደተቻለ ተገልጿል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ወጣቷ የተገኘችው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮናቫይረስ በሽታ ቅኝትን ለማጠናከር በተለያዩ ሆስፒታሎች በተኝቶ ማከሚያ ውስጥ በሚያደርገው ምርመራ ወቅት መሆኑን አመልክቷል።
በዚህም መርመራው ከተደረገላቸው በህክምና ላይ ያሉ የከፍተኛ አጣዳፊ የመተንፈሻ አካል በሽታ ካለባቸው ሰዎች ላይ ናሙና በመውሰድ የኮሮናቫይረስ ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ እንደሆነም ገልጿል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ከቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ከተወሰደ ናሙና ውስጥ አንዲት ታካሚ ላይ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባት በመጀመሪያ የላብራቶሪ ምርመራ በመታወቁ ለኅብረተሰቡ መጋቢት 18/2012 ዓ.ም በተሰጠው መግለጫ የተገለጸው ውጤት በተደጋጋሚ ምረመራን የሚቀይር እንደሆነም አመልክቷል።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ታማሚዋ የቆየ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባት በመሆኑ የህክምና ክትትል እየተደረገላት እንደሚገኝ ተገልጸወል።
በዚህ ምክንያት ለጥንቃቄ ሲባል የህክምና ክትትል ሲያደርጉላት የነበሩ የሆስፒታሉ ሠራተኞችና ሌሎች ከእነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በድምሩ 24 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ሥራ ገበታቸውና ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱ ይሆናል።
በዚህም እስካሁን ባለው መረጃ በኢትዮጵያ የተመዘገበው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች አሃዝ በአንድ ቀንሶ 22 ይሆናል ማለት ነው።
በአሜሪካ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑን ተከትሎ በቅርቡ ምርመራዎች በፍጥነት እንደሚካሄዱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።
ይህንም ማድረግ የሚያስችል ፈጣን መመርመሪያ እየተዘጋጀ እንደሆነ ፕሬዝደንት ትራምፕ አስታውቀዋል።
“አሁን ላይ ያለው መመርመሪያ አስቸጋሪ ነው፤ አዲሱ ግን በጣም ቀላል እና ፈጣን ነው” ሲሉ ፕሬዝደንት ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ ዝርዝሩን ባይገልጹም አቦት የተሰኘ ቤተ ሙከራ ግን የምርመራ ውጤትን ከአምስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ የሚያሳውቅ አዲስ መመርመሪያ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ትራምፕ መመርመሪያው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ይወጣል ያሉ ሲሆን ስለመመርመሪያውም ሆነ ስለ ምርቱ ያሉት ዝርዝር ነገር የለም።
የኮቪድ -19 መመርመሪያ መሳሪያ ለአሜሪካም ችግር ሆኖ ቆይቷል። ምንም እንኳን የግል ተቋማት አቅማቸውን በማጠናከራቸው ላለፉት ጥቂት ሳምንታት የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም፤ አሁንም ቢሆን ተጠርጣሪዎች ውጤታቸውን ለማወቅ ቀናት መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።
ትራምፕ አክለውም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በአገሪቷ የተላለፉ ውሳኔዎች ቢያንስ ለቀጣዮቹ 30 ቀናት ይዘልቃል ብለዋል።
በአሜሪካዋ ዋሽንግተን ግዛት ውስጥ የአንድ ቤተ ክርስቲያን የሕብረ ዝማሬ ቡድን አባላት፤ በአገልግሎት ላይ ሳሉ በኮሮናቫይረሱ መያዛቸው ተነገረ።
ዘማሪያኑ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ዘልቀው ከመግባታቸው በፊት እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያጸዱና ተራርቀው እንዲቆሙ ተደርጎ ነበር ተብሏል።
ይሁን እንጂ በርካታ ዘማሪያን በቫይረሱ መያዛቸውን እንዲሁም ሁለቱ ህይወታቸውን ማጣታቸው ተነግሯል።
በዕለቱ በቤተ-ክርስቲያኑ ከተገኙት 60 ሰዎች መካከል 45ቱ በቫይረሱ ተይዘዋል።
ሎስ አንጀለስ ታይምስ እንደዘገበው ህይወታቸው ካለፈው በተጨመሪ ሦስቱ ደግሞ በሆስፒታል ይገኛሉ።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል በኩል አዲስ አበባ ውስጥ በተመለከቷቸው ነገሮች ሃሳብ እንደገባቸው ገልጸው የነበሩት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፤ በአገሪቱ ውስጥ ለሚደረገው ጥረት ማገዣ ይሆን ዘንድ ከእራሳቸውና ከጽህፈት ቤታቸው የገንዘብ ድጋፍ አበርክተዋል።
በዚህም መሰረት የፕሬዝዳንቷ ጽ/ቤት የሚያስፈልገውን ወጪ በማብቃቃትና በመቆጠብ ከበጀቱ የሚቀነስ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከማበርከቱ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ሰጥተዋል።
ከዚህም ባሻገር ፕሬዝዳንቷ ወረርሽኙ ሊያስከትል ስለሚችለው ጉዳትና ሕዝቡ እራሱን ለመጠበቅ መውሰድ ስላለበት እርምጃ የቪዲዮ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
የእንግሊዙ ርካሹ አየር መንገድ ኢዚጀት፤ ሁሉንም አውሮፕላኖቹን ከበረራ ማገዱን አስታወቀ።
አየር መንገዱ መቼ በረራ እንደሚጀምር ያለው ነገር የለም።
አየር መንገዱ እንዳለው ውሳኔውን ያስተላለፈው በቫይረሱ ምክንያት መንግሥታት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የበረራ እገዳዎች በመጣላቸው ነው።
በርካታ አገልግሎቱቹን እንዳቋረጠ የገለጸው አየር መንገዱ፤ ከአገር ውጭ እንቅስቃሴቸው ተገድቦ የሚገኙ እንግሊዛዊያንን ወደ አገራቸው ለማምጣት ግን ሲበር እንደነበር ገልጿል።
"አሁንም ዜጎችን ለመታደግ ተጨማሪ በረራዎችን ማድረግ ካስፈለገ ከመንግሥት ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለን" ብሏል።
ኢዚ ጀት ዜጎችን ለመታደግ እስካሁን 650 የሚሆኑ በረራዎችን ያደረገ ሲሆን 45 ሺህ ዜጎችን ወደ አገራቸው አስገብቷል።
ወደሚቀጥለው ዓመት የተዘዋወረው ኦሊምፒክ የሚካሄድበት ቀን ይፋ ሆነ።
በዚህም መሠረት የቶኪዮ ኦሊምፒክ በእኛ አቆጣጠር ከሐምሌ 16 እሰከ ነሐሴ 2 2013 ዓ.ም. ይካሄዳል።
ዘንድሮ ሐምሌ ወር ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ወደ ቀጣይ ዓመት እንዲሸጋገር መደረጉ ይታወሳል።
ምንም እንኳ ውድድሩ የሚካሄደው እአአ 2021 ቢሆንም ውድድሩ ቶኪዮ 2020 የሚለውን ስያሜ ይዞ ይቀጥላል ተብሏል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር አዲስ የዲጂታል መሳሪያ ሥራ ላይ መዋሉን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
መተግበሪያው በኢትዮጵያ የኮቪድ- 19ን ወረርሽኝ በተመለከተ የማህበረሰብ ጤና ኃላፊዎች እና ፖሊሲ አርቃቂዎች ትክክለኛውን መረጃ በፍጥነት እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።
እነዚህ ወደ ሥራ የገቡት ዲጂታል ማስተግበሪያዎች የቅንጅትና ክትትል ሥራዎችን ለማቀላጠፍ፣ መረጃዎችን መዝግበው ለመያዝ፣ የተለዩ ተጠርጣሪዎችን ክትትል በማድረግ የጤና ሁኔታቸውን መዝግቦ ለመከታታል ይረዳሉ ብለዋል የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ።
ከዚህም በተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራዎችን ለመላክና ውጤቱንም ለመቀበል፣ ውጤታቸው የታወቀ ታማሚዎችንና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች በቀላሉ ለመለየት እንዲሁም የተሰበሰበውን መረጃ ሁሉ አጠናቅሮ በመተንተን በማስረጃ ላይ የተደገፈ ውሳኔ ለመስጠት ያስችላል።
ማስተግበሪያው በጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ከአጋሮች ጋር በመተባበር የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል።
ግራ ዘመሙ የኮሎምቢያ ብሔራዊ ነጻነት ጦር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ለአገሪቱ መንግሥት ጥያቄውን አቀረበ።
የተኩስ አቁሙ ስምምነት ከሁለት ቀናት በኋላ ተፈጻሚ እንዲሆን ጨምሮ ጠይቋል።
የሽምቅ ተዋጊው የተኩስ አቁሙ ጥሪውን ለመግሥት ያስተላለፈው "ሰብዓዊነት የተሞላበት ተግባር" በመሆኑ ነው ብሏል።
በኮሎምቢያ እስከ አሁን 700 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 10 ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ተነግሯል።
ሽምቅ ተዋጊዎቹ ከዚህ ውሳኔ ለመድረስ ያነሳሳቸው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒቶ ጉተሬዝ ከቀናት በፊት የሚመለከታቸው ሁሉ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ይድረሱ ሲሉ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ መሆኑ ተነግሯል።
በምሥራቅ አፍሪካ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ሩዋንዳ
ትናንት በሩዋንዳ 10 ሰዎች በቨይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 70 አድርሶታል።
ይህም በቀጠናው ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ትናንት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል 6ቱ ከዱባይ፣ ሁለቱ ከደቡብ አፍሪካ፣ አንድ ከናይጀሪያ እና ሌላኛው በምስራቅ አፍሪካ ካሉ አገራት በቅርቡ ወደ አገሪቷ የገቡ መሆናቸውን የአገሪቷ የጤና ሚኒስትር አስታውቋል።
ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎችን እየተከታተሉ መሆኑን ጠቅሰው ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ሩዋንዳ ለ14 ቀን በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ሁለተኛ ሳምንቷን ይዛለች።
ኤርትራ
ኤርትራ ትናነት 6 ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ማግኘቷን አስታውቃለች።
ይህም ቁጥሩን 12 አድርሶታል።
ስድስቱ ሰዎች አገሪቷ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ከማገዷ አስቀድሞ ወደ አገሪቷ የገቡ መሆናቸውን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ከእነዚህ መካካል 5ቱ እድሜያቸው ከ32- 60 የሚሆኑ ሴቶች ሲሆኑ ሁሉም ሕሙማን የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተነግሯል።
አገሪቷ ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች ማንኛውንም የሕዝብ የትራንስፖርት አግልግሎትን አግዳለች።
ከዚህም በተጨማሪ ከ10 ሰዎች በላይ በአንድ ላይ መሰብሰብን ከልክላለች።
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ትናንት አምስት ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን አስታውቃለች፤ ዛሬም ሁለት ሰዎች መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህም ቁጥሩን 23 አድርሶታል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ነው።
ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጇል። ተግባራዊነቱን ለማስፈጸም ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አንድ ሰው መገደሉ ይታወሳል።
የአማራ፣ ኦሮሚያ እና የደቡብ ክልል መንግሥታትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ወሳኔዎችን አሳልፈዋል።
ኬንያ
ኬንያ ትናንት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ38 ወደ 42 ከፍ ብሏል፤ ዛሬም ተጨማሪ 8 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች፡። በዚህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 50 ደርሷል።
ትንናት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሰዎች የኬንያ፣ አሜሪካ፣፣ ካሜሩን እና ቡርኪናፋሶ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።
ኡጋንዳ
ኡጋንዳ 33 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቃለች።
ታንዛኒያ
በታንዛኒያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 14 ደርሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አለመኖራቸው ተገልጿል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ወደ ለይቶ ማቆያ ሊገቡ መሆኑ ተዘገበ።
አንድ የእስራኤል ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ የጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ አማካሪ የሆኑ ግለሰብ በኮቪድ-19 መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ለይቶ ማቆያ ይገባሉ ተብሏል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት እንደዘገበው ኔታኒያሁን ጨምሮ ከሌሎች ቅርብ አማካሪዎቻቸው ጋር ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ይደረጋል።
ጀርመን በደቡብ አፍሪካ እንቅስቀሴያቸው ተገድቦ የሚገኙ 7 ሺህ በላይ የሚሆኑ ጎብኚ ዜጎቿን ልታወጣ መሆኑን በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ አስታውቋል።
አምባሳደር ማርቲን ስቻፈር እንደገለጹት ከ7 እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ ጀርመናዊያን በደቡብ አፍሪካ እንቅስቃሴቸው ተገድቦ ይገኛሉ።
በደቡብ አፍሪካ አንድ ጎብኝ በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ 47 ጀርመናዊያን ጎብኝዎች በለይቶ ማቆያ እንደሚገኙ የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ካሉ አገራት ከፍተኛውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስመዝግባለች።
እስካሁን 1280 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አገሪቷ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴን ገድባለች።
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
ከእነዚህም መካከል ክልል አቋራጭ የሆኑ የሕዝብ የትራንስፖርት አግልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጡ ተወስኗል።
በተጨማሪም በከተሞች ውስጥ የታክሲ፣ የባጃጅ እና የሞተር ሳይክል የትራንስፖርት አግልግሎቶች በተመሳሳይ መልኩ ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጡ ተደርጓል።
የክልሉ መንግሥት በክልሉ ውስጥ ከአንድ ወረዳ ወደ ሌላ በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ተሽከርካሪዎች በግማሽ የመጫን አቅማቸው ብቻ እንዲሠሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከዚህ በተጫማሪም የትኛውንም ዓይነት ስብሰባ ማካሄድ እንደማይቻል ተነግሯል።
መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት ጭፈራ ቤቶች፣ ጫት እና ሺሻ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ ተወስኗል።
በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት ትልልቅ ከተሞች መግቢያ እና መውጫ ላይ የሙቀት ልኬት ማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ይጀመራልም ተብሏል።
ሕዝቡ በተቻለው መጠን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲገታና ወደ እምነት ቦታዎች ከመሄድ እራሱን እንዲቆጥብ ጥሪ ቀርቧል።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎችን ለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ ተወስኗል።
በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችም በተቻለ መጠን ከቤት ሆነው እንዲሰሩ የሚል ትዕዛዝ የተላለፈ ሲሆን፤ የሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ የክልሉ መንግሥት ገልጿል።
ጀርመን ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ጋር ሲነጻጸር ያስመዘገበችው የሞት ቁጥር ዝቅተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመልከታሉ።
በቫይረሱ የተያዙ 62 ሺህ ሰዎች ቢኖሩም የሟቾች ቁጥር ግን 541 ብቻ ነው።
ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት ሰፊ ምርመራ ማድረጓ ነው። ጀርመን ምርመራ ማድረግ የጀመረችው ቀደም ብላ በመሆኑ አብዛኞቹ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቀለል ያለ ምልክት የሚያሳዩ ነበሩ።
በሌሎች አገራት የተረጋገጡት ኬዞች ቁጥር ከተጠረጠሩት የተወሰኑት ያህሉ ብቻ የሚያሳይ ነው። በጀርመን ግን በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ በቫይረሱ ከተጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር ጋር ተቀራራቢ ነው።
በመሆኑም ጣሊያን፣ ስፔን አሊያም ዩናይትድ ኪንግደም በምርመራ ያልተረጋገጡና ቀለል ያሉ ኬዞችን ቀደም ብለው ቢያካትቱ የሞት ቁጥራቸው ከጀርመን ያን ያህል እንደማይርቅ ይነገራል። በሌላ በኩል የጤና ተቋማት አቅም እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። ጀርመን ከፈረንሳይ፣ ጣሊያን ወይም ዩኬ የተሟላና የተጠናከረ የህክምና ተቋማት አላት።
በአገሪቷ ያለው ሕክምና ስርዓት ጽኑ ሕሙማንን ለመከታተል የሚያስችል አቅም ስላላትም ታማሚዎች ከጣሊያን እና ፈረንሳይ ለህክምና ወደ ጀርመን እየተወሰዱ ነው።
በአገሪቷ ያሉ ጽኑ ታማሚዎች ቁጥር ከጨመረም የሕክምና ስርዓቱን እንደምታሰፋ ይጠበቃል።
ምንም እንኳ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለም እያስጨነቀ ቢገኝም ሰሜን ኮሪያን ግን የሚሳኤል ሙከራ ከማድረግ አላገዳትም።
ትናንት እሁድ ሰሜን ኮሪያ ሁለት የአጭር-ርቀት ሙከራ ለማድረግ ሁለት ሚሳኤሎችን ለሙከራ መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ መንግሥት አስታውቋል።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ይህን የሰሜን ኮሪያ መንግሥት የሚሳኤል ሙከራን አጥብቆ ኮንኗል።
"የዓለም አገራት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጠበው እያለ የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ተግባር ተቀባይነት የሌላው እና በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል" ብሏል የደቡብ ኮሪያ መንግሥት።
ይህ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ጥሪ ከተሰማ በኋላ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት የሙከራውን ስኬት ጠቅሶ የእራሱን ተግባር አወድሶታል።
የሰሜን ኮሪያ መንግሥት እስካሁን በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ስለመኖሩ ሪፖርት አላደረገም።
ይሁን እንጂ ባለሙያዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይኖራሉ ብለው ይገምታሉ። ተጨማሪ ለማንበብ፡ ዓለም በወረርሽኝ በተጨነቀበት ጊዜ ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዋን ቀጥላለች
የስፔን መንግሥት ባለፉት 24 ሰዓታት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 812 መሆኑን አስታውቋል።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ ከሆነ እስካሁን በስፔን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 85ሺህን የተሻገረ ሲሆን 7,340 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሞተዋል።
በዓለማችን ላይ በአጠቃላይ 732,153 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 34,686 ደግሞ መሞታቸው ተነግሯል።
በሱዳን የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የተጣለውን ሰዓት እላፊ አፈጸዓጸም ስትቃኝ የነበረች ሰው አልባ አውሮፕላን በፕሬዝዳንቱ ጠባቂዎች ተመትታ ወደቀች።
አልሳህያ የተባለው ጋዜጣ እንዳለው ሰው አልባ አውሮፕላኗ ሰዓት እላፊውን ለመቆጣጠር ቅኝት እያደረገች ነበር፤ ነገር ግን የሱዳን የፕሬዝዳንቱ የጥበቃ አባላት በጥይት መትተዋታል።
ጥበቃዎቹ አውሮፕላኗን የመቷት በሉዓላዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሌ/ጄኔራል አብደልፈታህ አልቡሃሪ ቤት አቅራቢያ እያንዣበበች በነበረችበት ወቅት ነው።
ምንጮች እንዳረጋገጡት ሰው አልባ አውሮፕላኗ የጸጥታ አካላት ንብረት ስትሆን የሰዓት እላፊውን ሁኔታ አፈጻጸም ለመቃኘት የተላከች ነበረች።
በዓለም ላይ ድህነትን ለመቀነስ የሚሰራው እና የበርካታ የበጎ አድራጊ ድርጅቶች ስብስብ የሆነው ኦክስፋም ኮቪድ-19ን ለመዋጋት 160 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል አለ።
ኦክስፋም ኮቪድ-19ን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ እና ለአሰችኳይ የብድር እፎይታ የሚውል ገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል።
ኦክስፋምን ጨምሮም የገንዘቡ እርዳታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የደሃ አገራት ዜጎች በቫይረሱ እንዳይያዙ እና የአገራት የጤና ስርዓትን ለማጠናከር ያስፈልጋል ብሏል።