የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 አገራት የሚያደረገውን በረራ ያቆማል

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 250,000 የደረሰ ሲሆን የሞቱት ደግሞ 9,900 መሆናቸው ተነግሯል። በአፍሪካ እስካሁን ድረስ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች ቫይረሱ ቢገኝባቸውም የዓለም ጤና ድርጅት ግን "ለክፉ ቀን ተዘጋጁ" ሲል ማስጠንቀቅያ አዘል ምክሩን ለግሷል። እስካሁን ድረስ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ታማሚ ያገኙ ቢሆንም ሌሎች አገራቶችም አዳዲስ ታማሚዎችን ማግኘታቸውን እያሳወቁ ነው። ዛሬ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያና በቀሪው ዓለም ያለውን ውሎ በቀጥታ ዘገባችን እናስነብባችኋለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ማንኛውም ሰው ማድረግ ያለበት - እነዚህን መመሪያዎች መተግበር አይርሱ

    በተደጋጋሚ የሰሙት መልዕክት ሊሆን ይችላል። ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስም ተደጋግሞ ይሰሙታል።

    ነገር ግን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እርስዎ ማድረግ ከሚችሉት ነገር መካከል አንዱ ይህ ነው።

    እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብን አይርሱ!

  2. በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ ሆነ

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ከሆነ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ አልፏል።

    ከቫይረሱ መጀመሪያ ጀምሮ ዳታዎችን ሲያሰባስብ የነበረው የአሜሪካው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 250 ሺህ እየተጠጋ ነው ብሏል።

  3. "እጅ አንስጥ እጅ እንንሳ " በሚል የተሰራ አጭር ቪዲዮ

    ይህ ስለ ኮሮናቫይረስ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተሰራ አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል ነው። መልዕክቱ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን "እጅ አንስጥ እጅ እንንሳ ይላል።

    የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ያስችላሉ በሚል ካስቀመጧቸው መንገዶች መካከል አለመጨባበጥ አንዱ ነው።

    በዚህ አጭር ተንቀሳቃሽ ቪዲዮ ላይ የጃኖ ባንድ አባሉ ድምጻዊ ሐይሉ መርጋ የተሳተፈ ሲሆን፣ ተዋናይት ማህደር አሰፋም በሌላ መልዕክት ላይ ተሳትፋለች።

  4. በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እምነቶች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፉ

    በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ቤተ እምነቶች ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ለምዕመኖቻቸው ማድረግ ያለባቸውን የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፉ።

    የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ለሁለት ሳምንታት የእሁድ አምልኮ እንደማይኖር አስታውቀዋል።

    የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ የእሁድ አምልኮ ጉባኤዎች፣ ኮንፍራንሶች፣ ሥልጠናዎችና ሌሎች ተመሳሳይ ፕሮግራሞች እስከ መጋቢት 21 ድረስ እንዳይካሄዱ አዛለች።

    መካነ ኢየሱስ በበኩሏ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሚያዚያ ወር ልታካሂደው አቅዳው የነበረውንም 60ኛው የቤተክርስትያን ብሔራዊ ክብረ በዓል ለሌላ ጊዜ ማስተላለፏን አስታውቃለች።

    የኢትዮጵያ ካቶሊክዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በበኩሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ መጸለይ ለሚፈልጉ ሰዎች ዘወትር ክፍት እንደምትሆኑ ገልፀው የቅዳሴ አገልግሎት ውስን ቁጥር ባላቸው ምዕመናን ይካሄዳል ብለዋል።

    ቤተ አምነቶቹ ምዕመኖችና ካህናት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ይረዳሉ የተባሉ ዝርዝር እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉም መክረዋል።

  5. በናይጄሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች 12 ደረሱ

    ናይጄሪያ አዲስ አራት ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ በመገኘቱ በአጠቃላይ በአገሪቱ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 12 ደረሰ።

    የናይጄሪያ ጤና ሚኒስትር የሆኑት ኦሳጌ ኢሃኒር፣ ትናንት እንዳሉት አራቱ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በሌጎስ ከተማ የሚኖሩ ናቸው።

    ሁለቱ ግለሰቦች ከዩናይትድ ኪንግደምና ከፈረንሳይ የመጡ ሰዎች ሲሆኑ አንዱ ግን ቫይረሱ ካለባቸው ጋር ንክኪ የነበረው መሆኑ ተገልጿል።

    ይህ በነበረው ንክኪ ምክንያት ቫይረሱ የያዘው ግለሰብ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ እንደሌለው ሚኒስተሩ በትዊተራቸው ላይ አስፍረዋል።

  6. ሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ በረራ አገደች, ሳዑዲ አረቢያ ሁሉንም የአገር ውስጥ በረራዎች አግዳለች

    ሳዑዲ አረቢያ ሁሉንም የአገር ውስጥ በረራዎች ያገደች ሲሆን፣ አውቶቡሶች፣ ታክሲዎች እንዲሁም የባቡር ትራንስፖርት ለሁለት ሳምንት እንዲቋረጥ ተደርጓል።

    ይህ ውሳኔ ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የሚጀምር ይሆናል።

    ውሳኔው አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ከሰብዓዊ ድጋፍ፣ ከሕክምና ጋር የተያያዙ በረራዎችና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን አለመከልከሉ ታውቋል።

    እስካሁን ድረስ በሳዑዲ አረቢያ 270 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀ ሲሆን ሞት ግን አልተመዘገበም።

  7. ደቡብ አፍሪካ ከዚምባብዌ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በአጥር ልትዘጋ ነው, ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ከዚምቧቤ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በአጥር ለመዝጋት ወስናለች

    ደቡብ አፍሪካ በቀጣዩ አንድ ወር ውስጥ ከዚምባብዌ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በማጠር ህገወጥ ስደተኞችንና የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል መወሰኗን የሕዝብ አገልግሎት ሚኒስትር አስታወቁ።

    ይህ ውሳኔ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እሁድ እለት ቫይረሱን ብሔራዊ ቀውስ ነው ብለው ካወጁ በኋላ የተወሰነ የአስቸኴይ ጊዜ እርምጃ ነው ተብሏል።

    ሚኒስትሩ ሲናገሩ ይህ ውሳኔ ፕሬዝዳንቱ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚገቡ የውጪ ዜጎችን ማገዳቸውን ተከትሎ የተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል።

    ዚምባብዌና ደቡብ አፍሪካ በሚዋሰኑበት ድንበር 2 ሜትር ያህል ቁመት ያለው 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን አጥር እናጥራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

    በደቡብ አፍሪካ ከሁለት ሳምንት በፊት የመጀመሪያው ቫይረሱ ያለበት ሰው የተገኘ ሲሆን ከዚያ በኋላ 150 ተጨማሪ ሰው ተገኝቶበታል።

    በዚምባብዌ እስካሁን ድረስ አንድም ቫይረሱ የተገኘበት ሰው አልተገኘም።

  8. ካሊፎርኒያ ነዋሪዎቿ ከቤት እንዳይወጡ አገደች

    ካሊፎርኒያ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት በማሰብ የግዛቷን ነዋሪዎች"ቤት ተቀመጡ" ስትል አዛለች።

    የካሊፎርኒያ አገረ ገዢ ጋቪን ኒውሶም ለግዛቲቱ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ከቤት መውጣት የሚቻለው እጅግ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል።

    የአገረ ገዢው ውሳኔ ዜጎች ከቤታቸው እንዲወጡ የሚፈቅደው መድሃኒትና የፍጆታ እቃዎችን ለመግዛት፣ ውሻን ለማናፈስ ወይንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሆን ከሰዎች ጋር የሚኖር ግንኙትን ግን ከልክሏል።

    በአሜሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ 205 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 14ሺህ ደግሞ መያዛቸው ተመዝግቧል።

    በዓለም አቀፍ ደረጃ 250ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀ ሲሆን 10ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

  9. የጉዞ ክልከላዎች በአፍሪካ

    በአፍሪካ እስካሁን ድረስ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች ቫይረሱ ቢገኝባቸውም የዓለም ጤና ድርጅት ግን "ለክፉ ቀን ተዘጋጁ" ሲል ማስጠንቀቅያ አዘል ምክሩን ለግሷል።

    እስካሁን ድረስ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ታማሚ ያገኙ ቢሆንም ሌሎች አገራትም አዳዲስ ታማሚዎችን ማግኘታቸውን እያሳወቁ ነው። ለመሆኑ የትኞቹ የአፍሪካ አገራት ወደ ግዛቶቻቸው የሚገቡም ሆነ የሚወጡ በረራዎችን አገዱ?

  10. በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ ደረሰ

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በሦስት ጨምሮ ዘጠኝ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሜኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቁ።

    በአገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው የመጀመሪያው ግለሰብ ጃፓናዊው የዛሬ ሳምንት መጋቢት 04/2012 ዓ.ም ይፋ ከተደረገ በኋላ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር አሁን ዘጠኝ ደርሷል።

    በሽታው ከተገኘባቸው ከአዲሶቹ ሦስት ሰዎች መካከል አንደኛው የ44 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ጃፓናዊ፣ ሌላው የ39 ዓመት ኦስትሪያዊ፣ እንዲሁም ሦስተኛዋ የ85 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ኢትዮጵያዊት መሆናቸው ተገልጿል።

    አዲስ በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡት ሦስት ሰዎች ውስጥ ጃፓናዊው ግለሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠው ጃፓናዊ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲኾኑ፣ የ85 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ደግሞ ከሁለት ሳምንት በፊት ከውጪ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው።

    ተጨማሪ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ