የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 አገራት የሚያደረገውን በረራ ያቆማል

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 250,000 የደረሰ ሲሆን የሞቱት ደግሞ 9,900 መሆናቸው ተነግሯል። በአፍሪካ እስካሁን ድረስ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች ቫይረሱ ቢገኝባቸውም የዓለም ጤና ድርጅት ግን "ለክፉ ቀን ተዘጋጁ" ሲል ማስጠንቀቅያ አዘል ምክሩን ለግሷል። እስካሁን ድረስ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ታማሚ ያገኙ ቢሆንም ሌሎች አገራቶችም አዳዲስ ታማሚዎችን ማግኘታቸውን እያሳወቁ ነው። ዛሬ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያና በቀሪው ዓለም ያለውን ውሎ በቀጥታ ዘገባችን እናስነብባችኋለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ከዛሬ ሌሊት ስድስት ሠዓት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ይገባሉ

    መንግሥት አርብ ዕለት ይፋ ባደረገው ውሳኔ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ማናቸውም መንገደኞች ለ14 ቀናት ወደ በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የሚደረገው ከዛሬ ዕከለሌሊት ጀምሮ ነው።

    በዚህም መሰረት ከማናቸውም ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በሆቴል ውስጥ ተለይተው ለ14 ቀናት እንዲያቆዩ የሚያስገድደው ውሳኔ ተግባረዊ መሆን ይጀምራል።

    በመሆኑም ከዕሁድ እኩለሌሊት ጀምሮ የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች በስካይ ላይት ወይም በጊዮን ሆቴል ለ14 ቀናት በራሳቸው ወጪ ተለይተው ይቆያሉ ተብሏል።

    እንዲሁም ዲፕሎማቶች አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ በየአገራቸው ኤምባሲዎች እራሳቸውን ለ14 ቀናት ለይተው ይቆያሉ።

    የትራንዚት በረራ መንገደኞችም የትራንዚት በረራቸውን እስኪያገኙ ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በሆነው በስካይላይት ሆቴል ተለይተው ይቆያሉ።

  2. የዛሬውን አጠናቀናል፤ ነገ እንመለሳለን

    ውድ የቢቢሲ አማርኛ ተከታታዮች፤ የዛሬውን የቀጥታ ስርጭታችንን በዚህ አጠናቀናል።

    ነገ ጠዋት በሌላ የቀጥታ ስርጭት እንመለሳለን።

    መልካም ምሽት

  3. ዩናይትድ ኪንግደም ካፌ እና መጠጥ ቤቶችን ልትዘጋ ነው

    ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ካፍቴሪያዎች፣ መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚዘጉ ተናገሩ።

    "ካፌዎች፣ መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ምሽት ጀምሮ በፍጥነት እንዲዘጉና ነገ መልሰው መክፈት እንደማይችሉ ጨምረን መልዕክት አስተላልፈናል" ብለዋል።

    የምሽት መዝናኛ ስፍራዎች፣ ሲኒማ ቤቶች እና ጂምናዚየሞችም ዝግ ይሆናሉ ተብሏል።

  4. ሰበር, ጣሊያን በአንድ ቀን ከተመዘገበው ሞት ከፍተኛውን አስመዘገበች

    ጣሊያን በአንድ ቀን ውስጥ ከተመዘገበው ሞት ከፍተኛውን ቁጥር አስመዝግባለች።

    አውሮፓዊቷ አገር በአንድ ቀን የ 627 ሰዎች ሞት በመመዝገብ በአንድ ቀን ከተመዘገበው ሞት ከፍተኛውን አስተናግዳለች። እስካሁን በአጠቃላይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርም ወደ 4032 ከፍ ብሏል።

    5129 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን 2655 ግን ከፍተኛ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

  5. ቱኒዚያ ሁሉንም እንቅስቃሴዎች አገደች

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ቱኒዚያ ዜጎቿ የሚያደርጓቸውን ሁሉንም እንቅስቃሴዎች አገደች።

    የአገሪቱ ፕሬዝደንት እጅግ አንገብጋቢ ለሆነ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከቤት መውጣት አይፈቀድም ብለዋል።

    ይሁን እንጂ ፕሬዝደንቱ ይህ አዋጅ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አላሳወቁም።

    ሱፐርማርኬቶች እና መድሃኒት ቤቶች ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ እና ዜጎች ከቤት መውጣት የሚችሉት ምግብ እና የህክምና እርዳታን ሲሹ ብቻ ነው ተብሏል።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በቱኒዚያ የሰዓት እላፊ ታውጆ እንደነበረ ይታወሳል።

    በኮሮናቫይረስ የሞተ የመጀመሪያ ሰው ዛሬ በቱኒዚያ ተመዝግቧል።

  6. ኮሮናቫይርስ በምርጫ ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ ውይይት ተደረገ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮናቫይረስ ስጋት ለምርጫ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ላይ ስለሚኖረው ተጽህኖና ስለሚኖሩ አማራጮች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አደረገ።

    ምርጫ ቦርድ ከአርባ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አደረግሁት ባለው ውይይት ላይ በአሁኑ ወቅት ያለው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ለጥቂት ሳምንታት ከቀጠለ መፈጸም በሚገባቸው ተግባራት ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ ለፓርቲዎቹ አቅርቧል።

    ቦርዱ ከዚህ በተጨማሪ ወረርሽኙ በምርጫው ዝርዝር አፈጻጸምና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተጽህኖና ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለመገምገም ከፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በተከታታይ ውይይት እንደሚያደርግ አሳውቋል።

    የፖለቲካ ፓርቲቹም በበኩላቸው ይህ ችግር በምርጫ ሂደት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽህኖ እንደሚገነዘቡ እንደገለጹና ቦርዱም ሁኔታዎች እያገናዘበ ውይይት ተደረገባቸው ውሳኔዎችን እንዲወስን አስተያየት እንደሰጡ ተገልጿል።

  7. ሰበር, ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ በሙሉ በራሳቸው ወጪ ወደ ለይቶ ማቆያ ይገባሉ ተባለ

    ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ዛሬ አመሻሽ ላይ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው የኢኮኖሚ፣ የጸጥታ፣ የጤና እና የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ ተቋቁሞ የኮሮናቫይረስ እድገት በኢትዮጵያ ሲከታተል መቆየቱን ተናግረዋል።

    በዚህም መሠረት አዳዲስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተወስኗል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ። ውሳኔዎቹም የሚከተሉት ናቸው።

    1.ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሰው ወደ ለይቶ ማቆያ ይወሰዳል

    ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሰው ለ14 ቀናት ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስታውቀዋል።

    ወጪዉም በግለሰቡ ይሸፈናል በለዋል።

    2. በረራ ይደረግባቸው የነበሩ ከ30 በላይ አገራት በረራ እንዲቋረጥ ተደርጓል

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ከ 30 በላይ አገራት የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ መወሰኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

    ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አየር መንገዱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ተናግረዋል።

    "አየር መንገዱ 190 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሞታል። በዚህም ወደፊት ከፍተኛ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል” ብለዋል።

    3.የዕምነት ተቋማት

    የአምልኮ ስርዓቱ እና ልምዱ ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

    በዚህም "በእነሱ [ኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶች] በኩል መልዕክት እንደሚተላለፍ ይጠበቃል” ያሉ ሲሆን፤ የኦርቶዶክስ አባቶች መግለጫ ዛሬ እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

    የፕሮቴስታንት መሪዎችም ቴክኖሎጂን በመታገዝ አገልግሎት እንዲሰጡ አማራጭ መቀመጡን ተናግረዋል።

    በእስልምናም የሚደረጉ ሰላቶች ንክኪ ስለሚኖራቸው፤ የሃይማኖት መሪዎች እርምጃ እንደሚወስዱ እና መግለጫ እንዲሰጡ መንግሥት ጥሪ አስተላልፏል ብለዋል።

    4.በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች

    በማረሚያ ቤቶች በሽታው ከገባ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ታራሚዎችን ወደ ሌሎች ቦታዎች ወስዶ ዘርዘር ለማድረግ ተጨማሪ ቦታዎች ተዘጋጅቷል ብለዋል።

    አዳዲስ ታራሚዎች ምረመራ ሳይደረግላቸው ወደ ማረሚያ ቤት አይገቡም ብለዋል።

    አክለውም የቤተሰብ ጥየቃ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም መደረጉን ጠቅሰዋል።

    ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ፤ ህጻናትን የያዙ፣ የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰ እና ቀለል ያለ ክስ ያለባቸው እንዲለቀቁ መወሰኑን ተናግረዋል።

    5. በውጪ አገር ዜጎች ላይ ስለደረሰው ጥቃት

    ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከሰሞኑ የወረርሽኙን ስርጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ በውጪ አገር ዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት ‘‘ኢትዮጵያዊ ባህሪ የሌለው ነው’’ በማለት ጥቃቱን አውግዘዋል።

    6. የበጎ አድራጎት ሥራዎች

    ከሰሞኑ በርካታ ወጣቶች ሰዎችን እጅ ማስታጠብ ጨምሮ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲያከናውኑ ነበር። መንግሥት የበጎ አድራጎት ሥራዎቹን በአክብሮት የሚመለከተው ነው ካሉ በኋላ፤ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ሲሰሩ ተገቢውን ጥንቃቄ መውሰድ ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል።

    7. የሕክምና ባለሙያዎች ጥረት

    ጠቅላይ ሚንስትሩ የእስካሁኑን የሕክምና ባለሙያዎችን ጥረት አድንቀዋል። የቫይረሱ ስርጭት የሚስፋፋ ከሆነም በሽታውን ለማሸነፍ ብዙ ጥረት ይጠበቅባችኋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    8. ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚገኙ ድጋፎች

    ከጃክ ማ፣ ከቢል ጊቴስ እና ከዓለም ባንክ በተገኙ ድጋፎች የዜጎች ሕይወት እንዳያልፍ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

    9. የምሽት መዝናኛ ቤቶች ይዘጋሉ

    ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመሽት መዝናኛ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ ይሆናሉ ብለዋል።

    በጠባብ ቦታ ላይ በርካታ ሰዎች ስለሚያስተናግዱ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ዝግ ይደረጋሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

    “በሽታውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠራችንን እስክናረጋግጥ ድረስ የምሽት መዝናኛዎች እንዲዘጉ ተወስኗል” ብለዋል።

    10. ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች

    ጠቅላይ ሚንስትሩ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት በሞከሩ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰው አሁንም ሕጋዊ የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰድ ይቀጥላል ብለዋል።

    11. ለክልሎች የሚደረገው ድጋፍ

    በክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና ሆስፒታሎች ምረመራ የማድረግ አቅማቸውን ለማሳደግ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበረ አስታወሰዋል።

    ለዚህም የሚረዳ የምረመራ እና የማዳን ሥራ እንዲሰራ ተግባብተናል ብለዋል።

    12. ምርጫ

    ወረርሽኙ ከወራት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ስለሚኖረው ጫና ሲያስረዱ፤ "ምርጫ ቦርድ የራሱን ግምገማ እያካሄደ ነው፤ ግምገማውን መሰረት በማድረግ የመጨረሻው ውጤት ይፋ ይደረጋል” ብለዋል።

    13. የመጠጥ ውሃ እጥረት

    የመጠጥ ውሃ እጥረት ባለባቸው ቦታዎች በቦቴ የማቅረብ ሠራዎች እየተካሄደ እንደሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

    በተለይ በከተማ አከባቢ ከፍተኛ የውሃ እጥረት መኖሩን አንስተዋል።

    14. የኮሮናቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ

    ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ተናግረዋል።

    እንደ ምሳሌም አየር መንገዱ ብቻ 190 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሞታል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህም “አየር መንገዱ ከፍተኛ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል” ብለዋል።

    የአበባ እና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎችም ከፍተኛ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።

    “ይቅርታ”

    ጠቅላይ ሚንሰትሩ በመግለጫቸው መጨረሻ ላይ “የብልጽግና ፓርቲ የገንዘብ መዋጮ ላይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን እና የፖለቲካ ምሁሮችን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር በርካቶች ማዘናቸውን ሰምቻለሁ” ብለዋል።

    “ጉዳዩ የማይመለከታችሁ እና በንግግሬ እንድትታቀፉ የሆናችሁ፣ የተማራችሁ እና በተማራችሁበት ዘርፍ አገራችሁን በቅንንተ የምታገለግሉ ውጤትም ያመጣችሁ ሰዎች ጉዳዩ እናንተን የማይመለከት ቢሆንም ጉዳዩ እናንተን የማይመለከት መሆኑን በግልጽ ባለማስቀመጤ እናንተን ይቅርታ ጠይቃለሁ” በለዋል።

  8. በአንድ ሠርግ ላይ የታደሙ 35 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተነገረ

    በአውስትራሊያ በአንድ ሠርግ ላይ የታደሙ 35 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተነገረ።

    የሠርጉ ስነ-ስርዓት ከሁለት ሳምንት በፊት በአውስትራሊያ ኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት እንደተከናወነ ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።

    ለ 35ቱ ሰዎች በቫይረሱ እንዲያዙ ምክንያት የሆነው ግለሰብ ከአሜሪካ ወደ አውስትራሊያ የተጓዘ መሆኑም ተነግሯል።

    የአከባቢው ባለስልጣናት በሠርጉ ላይ ተሳትፈው ምረመራ ያላደረጉ ተጨማሪ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ግለሰቦቹን ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

    በተመሳሳይ መልኩ ከአውሮፓ ወደ ኡራጋይ ተጉዛ ሠርግ ላይ የታደመች ሴት 44 ሰዎች በኮሮና እንዲያዙ ምክንያት መሆኗም ተነግሯል።

    የካቲት 28 በተካሄደው የሠርግ ስነ-ስርዓት ላይ ከ 500 በላይ ጥሪው የደረሳቸው ሰዎች ተሳትፈው ነበር።

    44 ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንዲያዙ ምክንያት ሆናለች የተባለችው የ56 ዓመት ሴት ከሰፔን ወደ ኡራጋይ የተጓዘች መሆኑ ተዘግቧል።

    መንግሥታት እና የኃይማኖት ተቋማት የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ሰዎች እንዳይስበሰቡ ውሳኔ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

    በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ቸርች ኦፍ ኢንግላንድ ጥንዶች የሠርግ ስነ-ስርዓታቸውን ወደ ሌላ ቀን እንዲያዘዋወሩ ወስኗል።

    የቀን ለውጥ ማድረግ የማይችሉ ከሆነ በስነ-ስርዓታቸው ላይ መገኘት የሚችሉት ሰዎች ቁጥር አምስት ብቻ እንደሚሆን ተነግሯል። እነዚህም ሰዎች ሁለቱ ጥንዶች፣ ሁለት ምስክሮች እና የሚያጋቡት የኃይማኖት መሪ ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ወረርሽኙን ተከትሎ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ጥንዶች ሊያካሂዱት የነበረውን የሠርግ ስነ-ስርዓት ላልተወሰ ጊዜ አራዝመዋል።

    ከእነዚህም መካከል እንግሊዛዊያኑ ጆዲ እና ፊሊፕ ይገኙበታል። ጥንዶቹም “በሠርጋችን ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ አንጥልም” ብለዋል።

  9. በቀጣይ ወራትም ማኅበራዊ እርቀትን ጠብቆ መቆየት የግድ ነው ተባለ

    የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት በቀጣይ ወራትም ማኅበራዊ እርቀታችንን ጠብቀን እንቆያለን ተባለ።

    በአደጋ ጊዜ ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳብ የሚያቀርበው የእንግሊዝ አጥኚዎች ቡደን እንዳለው በመጪዎቹ ወራትም ሰዎች ማኅበራዊ እርቀታቸውን ጠብቀው መቆየት ይኖርባቸዋል።

    ቡድኑ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ጠንከር እና ላላ የሉ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ብሏል።

    ጠንካራ ከሚባሉ እርምጃዎች መካከል ለቀጣይ ወራት ትምህርት ቤቶችን ዘግቶ ማቆየት እና ሰዎች ማኅበራዊ እርቀታቸውን እንዲጠብቁ ማስገደድ የሚለው ይገኝበታል።

  10. ኬንያ የምሽት መዝናኛ ስፍራዎች የሠዓት ገደብ ተጣለባቸው

    የኬንያ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት መጠጥ ቤቶችና የምሽት መዝናኛ ስፍራዎች መስራት የሚችሉት እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ ብቻ ነው አለ።

    ከዚህ ቀደም የምሽት መዝናኛ ስፍራዎች እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ እንዲሰሩ ተፈቅዶ ነበር።

    ከዚህ በተጨማሪ በመገበያያ ስፍራዎች በአንድ ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ላይ ገደብ እንዲደረግ ውሳኔ አስተላልፏል።

    እስካሁን በኬንያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 7 ደርሷል።

    የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ቀጣዮች ሁለት ሳምንታት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

  11. ቱኒዚያና ኒጀር የመጀመሪያ በኮሮና የሞተ እና የተያዘ ሰው ይፋ አደረጉ

    ቱኒዚያ በኮሮናቫይረስ የመጀመሪያውን የሞተ ሰው ይፋ ስታደርግ፤ ኒጀር በበኩሏ በአገሪቱ የመጀመሪያውን በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘቱን አስታውቃለች።

    በቱኒዚያ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው ያለፈው ከአራት ቀናት በፊት ከቱርክ ወደ ቱኒዚያ የተጓዙ የ72 ዓመት ሴት ናቸው ተብሏል።

    ኒጀር በበኩሏ ከቶጎ የመጣ የ36 ዓመት ጎልማሳ በኮሮናቫይረስ መያዙን አረጋግጫለሁ ብላለች።

    ይህ ግለሰብ ወደ ኒጀር ከመግባቱ በፊት ባለፉት ጥቂት ቀናት ወደ ቶጎ፣ ጋና፣ አይቮሪኮስትና ቡርኪናፋሶ ተጉዞ ነበር ተብሏል።

    ቱኒዚያ የመጀመሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መኖሩን ይፋ ያደረገችው ከ18 ቀናት በፊት ሲሆን ዛሬ ላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 39 ደርሷል።

    እስካሁን አፍሪካ ውስጥ 7 ሰዎች በግብጽ፣ 9 በአልጄሪያ፣ 2 በሞሮኮ እንዲሁም ሱዳን እና ቡርኪናፋሶ እያንዳንዳቸው አንድ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን አስመዝግበዋል።

  12. አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ ቦታ ተሰብስበው የነበሩ 150 ሰዎች በፖሊስ ተያዙ

    በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ሺሻ ሲያጨሱ አገኘኋቸው ያላቸውን አንድ መቶ ሀምሳ ሰዎችን መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

    ፖሊስ እንዳለው “ይህ ተግባር ከሕገ ወጥነትም ባለፈ የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር እየተደረገ ላለው ጥረት እንቅፋት ይሆናል” ሲሉ ኮማንደር ከበደ አስፋው የአዲስ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ መናገራቸውን የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን አመልክቷል።

    ፖሊስ ከደንብ ማስከበር ሰራተኞች ጋር በመሆን ጎማ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ጠባብ ቤት ውስጥ አንድ መቶ ሀምሳ ሰዎች ተሰብስበው ሺሻ ሲያጨሱና ጫት ሲቅሙ አግኝቶ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አመልክቷል።

    ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ መንግሥት የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በከፍተኛ ቁጥር በአንድ ቦታ ላይ ተሰብስቦ አለመገኘት መሆኑ ይታወሳል።

  13. የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር ከ30 ሚሊየን ሕዝብ በላይ በኮሮና ሊጠቁ ይችላሉ ሲሉ አስጠነቀቁ

    የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር ከ30 ሚሊየን ሕዝብ በላይ በኮሮናቫይረስ ሊጠቃ ይችላል ሲሉ ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ደቡብ አፍሪካ 205 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

    ይህ ቁጥር ሐሙስ ዕለት ከነበረው በ55 ከፍ ብሏል።

    ጤና ሚኒስትሩ ዝዌል ማክሄዚ ቁጥሩ ከዚህም ከፍ እንደሚል ተናግረው የአገሪቱ 60 በመቶ ሕዝብ ሊጠቃ ይችላል ብለዋል።

    ከእነዚህም መካከል 20 በመቶው የሚሆኑት ክፉኛ ይጠቃሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የኮሮናቫይረስ ወርሽኝን ተከትሎ ብሔራዊ ቀውስ ሲሉ ማወጃቸው ይታወሳል።

    ደቡብ አፍሪካ በቀጣዩ አንድ ወር ውስጥ ከዚምባብዌ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በማጠር ህገወጥ ስደተኞችንና የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል መወሰኗን የሕዝብ አገልግሎት ሚኒስትር አስታወቁ።

  14. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ኪነጥበብ ባለሙያዎች መልዕክት

    ኢትዮጵያዊያን የኪነጥበብ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን ስለ ኮሮናቫይረስ ግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች በተንቀሳቃሽ ምስሎች በመስራት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን እየለቀቁ መሆኑን የቡድኑ አባል የሆነው የፊልም ባለሙያ ክብረዓለም ፋንታ ለቢቢሲ ገለጸ።

    እነዚህ "እጅ አንስጥ እጅ እንንሳ" እና "አብረን እንጂ ብቻችንን አንድንም" የሚሉ መልዕክቶች የያዙ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ናቸው።

    አቶ ክብረዓለም ከእርሱ ባሻገር ሚካኤል ሚሊዮን፣ አክሊሉ ገብረመድኅን፣ ሰው መሆን ይስማው መኖራቸውን በመግለጽ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መልዕክቱን በማስተላለፍም መሳተፋቸውን ይናገራል። ዝርዝሩን ለማንበብና ተንቀሳቃሽ ምስሎቹን ለመመልከት ቀጣዩን ማስፈንጠሪያ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ባለሙያዎች መልዕክት ስለ ኮሮናቫይረስ

  15. የአዛውንቶች ጥሪ ስለኮሮናቫይረስ

    በዓለማችን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 250ሺህ የደረሰ ሲሆን ከ10ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

    ቫይረሱ በእድሜ የገፉና የተለያዩ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ላይ እነደሚበረታ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

    ስለቫይረሱ የተለያዩ ሰዎች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን እነዚህ አዛውንቶች ይህንን ብለዋል!

  16. ኬኒያዊው ኃይማኖት ሰባኪ ኮሮናቫይረስን የፈጠራ ወሬ በማለቱ ከአገልግሎት ታገደ

    ኬኒያዊው የኃይማኖት ሰባኪ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የፈጠራ ወሬ በማለቱና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረግን እጅ መታጠብ በማጣጣሉ ከሚያገለግልበት ቤተ እምነት ታገደ።

    አገልጋዩ ቫይረሱን ክርስትያኖችን ለመፈተን የመጣ "ወሬ" ነው ያለ ሲሆን የቤተክርስትያኑ አባላት ወደ ቤተእምነቱ በመምጣት አምልኮ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።

    የቤተክርስትያኑ አስተዳደር አገልጋዩን ያወገዘ ሲሆን ወረርሽኙንም እውነት እንደሆነ በመጥቀስ በቤተክርስትያኒቱ የሚካሄዱ የአምልኮ መርሃግብሮችን አግዷል።

    የቤተክርስትያኑ አገልጋዮች መንግሥት ያስቀመጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

    በኬንያ ከኮረናቫይረስ ጋር በተያያዘ በርካታ ቤተ እምነቶች የአምልኮ መርሃ ግብራቸውን ሰርዘዋል።

  17. በስፔን በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ1ሺህ በላይ ሆነ

    በስፔን በኮሮና ቫይረስ ምከንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1002 መድረሱን ባለስልጣናት ተናገሩ።

    20ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 1588 ሰዎች ደግሞ ከሕመማቸው አገግመዋል ተብሏል።

  18. ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ማለት ምን ማለት ነው?

    ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሰዎች እንዲወሰዱ ካስቀመጣቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው።

    ድርጅቱ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች አንድ ሜትር ወይም ሶስት ጫማ እንዲርቁ ያሳስባል።

    ይህ ሰዎች ሲስሉ ወይም ሲያስነጥሱ ከአፍ ወይም ከአንጫቸው የሚወጡ እንጥብጣቢዎች ወደ ሌሎች እንዳይሄድ እንደሚያስችልና ይህም የቫይረሱን መተላለፍ እንደሚያስቀር ተገልጿል።

    እርስዎስ ማህበራዊ ርቀትዎን እጠበቁ ነው?

  19. በኮሮናቫይረስ በየደቂቃው በዓለም ዙሪያ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር

    ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ተነስቶ ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲክ ውጪ ሁሉንም የዓለማችንን አህጉራትን ያዳረሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት የምድራችን ዋነኛ የጤና ስጋት ሆኗል።

    ኮቪድ-19 በመባል የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ሲሆን፤ መጀመሪያ ትኩሳት ቀጥሎም ደረቅ ሳል ከሳምንት በኋላ ደግሞ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል።

    እስካሁን በቫይረሱ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። ዝርዝሩን ለማየት ማስፈንጠሪያውን ይከተሉ በየደቂቃው በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ስንት ደረሰ

  20. የአሜሪካ እስር ቤቶች በኮሮናቫይረስ ምክንያት እስረኛ መልቀቅ ጀመሩ

    በአሜሪካ እስር ቤቶች ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ታራሚዎች እንዳሉ መሰማቱን ተከትሎ እስር ቤቶች እስረኛ መልቀቅ መጀመራቸው ተገለፀ።

    የሎስ አንጀለስ እና ክሌቭላንድ እስር ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች መልቀቃቸውን ተክትሎ ረቡዕ የኒው ዮርክ እስር ቤት ለወረርሽኙ ተጋላጭ ያላቸውን እስረኞች መልቀቅ መጀመሩ ተሰምቷል።

    የእስርኛ አያያዝ ወትዋቾች ታራሚዎች በቫይረሱ ለመያዝም ለማስተላለፍም የተጋለጡ መሆናቸውን እየገለፁ ነው።

    የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ቢል ዲ ብላዚዮ ረቡዕ እለት እስር ቤቶች በጥቃቅን ወንጀሎች የታሰሩ ታራሚዎችን እንዲሁም ሌሎች በሽታዎች ያሉባቸውና ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ የሆኑትን የመለየት ሥራ እንደሚሰሩ አስታውቋል። ሙሉ ዜናውን ለማንበብ ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይከተሉ፡ የአሜሪካ እስር ቤቶች በኮሮናቫይረስ ምክንያት እስረኛ መልቀቅ ጀመሩ