ጣሊያን ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ተሰማ

በደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ እና በአውሮፓ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል። ቢቢሲ አማርኛ በኢትዮጵያ እና በተቀረው ዓለም ከቫይረሱ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን እና መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እያደረጉ ስለሚገኙት ጥረት መረጃዎችን በፍጥነት እናደርሳችኋላን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሕንድ በስልክ ጥሪ ስለኮሮናቫይረስ መረጃ እየሰጠች ነው

    በሕንድ የሚገኙ በርካታ የሞባይል ኔትወርክ አቅራቢዎች ደንበኞቻቸው ማንኛውንም ጥሪ ከማድረጋቸው በፊት ለ30 ሰከንድ የኮሮናቫይረስ መረጃ እንዲያገኙ እያደረጉ ነው።

    ጂሎ፣ ቢኤስኤንኤል እና ቮዳፎን የተባሉት ኩባንያዎች መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ተግባራዊ ካደረጉት መካከል ይገኙበታል።

    መልዕክቱ በእንግሊዘኛ የሚሰራጭ ሲሆን ማንኛውም ሰው ሲደውል ከጥሪው በፊት የሚያስል ሰውና የጤና መልዕክቱን ይሰማሉ።

    ነገር ግን አንዳንድ ደንበኞች በመልዕክቱ መበሳጨታቸውን ደጋግመው በመግለጻቸው የተነሳ በርካታ ድረ-ገጾች መልዕክቱን እንዴት ማስቆም እንደሚቻል የሚገልፅ መረጃ እያሰራጩ ይገኛሉ።

  2. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች መከሰቱ ተሰማ, በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች ኮሮና ወረርሽን ተከስቷል

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች መስፋፋቱ ተሰማ።

    የዌስት ቨርጂኒያ አገረ ገዢ በትናንትናው ዕለት በግዛታቸው ስለተገኘ አንድ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መግለጫ ሲሰጡ “እንደሚመጣ እናውቀው ነበር” ብለዋል።

    ኒውዮር ልክ እንደ ሳንፍራንሲስኮዋ ቤይ ኤሪያ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴዎችን ለማቆም እያሰበች መሆኑም ተነግሯል።

    በአሜሪካ እስካሁን ድረስ 108 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሲሆን 6300 ሰዎች ደግሞ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ 200ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 8ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    በተያያዘ ዜና ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ዓለማችን ውድ ከተሞች በጎብኚ ድርቅ ተመትተዋል።

    ሆንግ ኮንግ፣ ሲንጋፖር እና ኦሳካ የዓለማችን ውድ ከተሞች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

    ይህ ግን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የሚቀጥል አልሆነም።

    ከፍተኛ ገቢያቸውን ከቱሪዝም ያገኙ የነበሩ እነዚህ ከተሞች ከወረርሽኙ በኋላ ርካሽ እየሆኑ መጥተዋል ይላል።

    በአንድ ወቅት የማታንቀላፋዋ የተባለችው ኒው ዩርክ የሚንቀሳቀስ አንድም ሰው የማይታይባት እየሆነች ነው ተብሏል።

  3. በኢትዮጵያ ኮረናቫይረስ ያለበት ስድስተኛ ሰው ተገኘ

    በኢትዮጵያ ኮረናቫይረስ ያለበት ስድስተኛ ሰው ተገኘ የጤና ጥበቃ ሚንስትሯ ሊያ ታደሰ ቫይረሱ የተገኘባት የ59 ዓመት ኢንግሊዛዊት ሴት ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች መሆኗን አሳውቀዋል።

    እንግሊዛቷ ዲፕሎማት በነበረችበት ሆቴል እራሷን አግልላ መቆየቷን የጤና ሚንስትሯ አሳውቀዋል።

    የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከግለሰቧ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየትና የክትትል ስራ አጠናክሮ መቀጠሉም ተነግሯል።

    በአሁኑ ሰዓት ግለሰቧ በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላት እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም በሁኔታዎች ሳይደናገጥ በተረጋጋ መንፈስ የበሽታውን ስርጭት በመግታት የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ተጠይቋል።