በኢትዮጵያ ኮረናቫይረስ ያለበት ስድስተኛ ሰው ተገኘ

ዓለማችን በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ከታመሰች ወዲህ ከተለያዩ አገራት የሚሰሙ ዜናዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያመለክቱ ናቸው። ይህንን ተከትሎም አገራት ድንበራቸውንና ትምህርት ቤቶችን እየዘጉ ሲሆን፣ ሰዎች በርከት ብለው እንዳይሰበሰቡ እያገዱ ነው። ዛሬስ በአገራችንና በዓለማችን ኮሮናን በተመለከተ ምን እየተካሄደ ነው? ቢቢሲ አማርኛ በቀጥታ ዘገባው ያደርሳችኋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተባለ, በአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተባለ

    በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ አራት ቴአትር ቤቶች እና የመንግሥት ሲኒማ ቤቶች ከትናንት ጀምሮ ለ15 ቀናት ለሕዝብ አገልግሎት ዝግ መሆናቸው ተነገረ።

    ትዕዛዙ የተላለፈው ትናንት ሲሆን ይህንን ተከትሎም ሁሉም ትያትር ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች ዝግ መሆናቸው ይታወቃል።

    በትናንትናው እለት ሴንቸሪ ሲኒማ ለተጠቃሚዎቹ በቴሌግራም ገፁ ላይ ባስተላለፈው መልዕክትም ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ለቀጣይ 15 ቀናት ዝግ እንደሚሆን አስታውቋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትናንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትልልቅ ስብሰባዎች ለቀጣዮቹ 15 ቀናት እንደሚዘጉ አስታውቀዋል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ አምስት ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።

  2. የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አለብን?, የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አለብን?

    የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው የኮሮናቫይረስን ለመካላከል በሚል ሁሉም ሰው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አያስፈልገውም።

    ጭንብሉን ማድረግ ያለባቸው የሚያስነጥሱና የሚያስሉ ከሆነ እንዲሁም በበሽታው የተጠረጠረ ወይም የተያዘን ሰው የሚቀርቡና የሚንከባከቡ ሰዎች ብቻ ነው።

    ለእነዚህ ሰዎች ጭንብሉን ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም፤ በውጤታማ ሁኔታ በሽታውን ለመከላከልም በመደበኛነት እጃቸውን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ወይም አልኮል ነክ በሆኑ ፈሳሾች እጃቸውን ማጽዳት ይጠበቅባቸዋል።

    በተጨማሪም ጭንብሉን መጠቀም ያለባቸው ሰዎች እንዴት መጠቀምና በተገቢው ሁኔታ እንዴት መወገድ እንዳለበትም ማወቅ ይገባቸዋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል።

    የማስነጠስና የማሳል ምልክት የሚታይባቸውን ወይም በኮሮናቫይረስ ከሚጠረጠሩ ሰዎች ጋር የግድ መቅረብ ያለባቸው ሰዎች የሚጠቀሙባቸው የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች በቀላሉ በላብ ስለሚባላሹ ወዲያው ወዲያው መቀየር አለባቸው።

    ስለዚህ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚመክሩት የተጠቀሱት ምልክቶች እስካልታዩ ድረስ ሁሉም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አያስፈልገውም።

    ከዚያ ይልቅ ግን የበሽታው ስጋት ለማስወገድ ከሚያስሉ፣ ከሚያስነጥሱ ወይም ትኩሳት ካለባቸው ሰዎች ጋር የሚኖርን

    ንክኪ ማስወገድ፣ እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ካልሆንም ተህዋሲያንን በሚያስወዱ ማጽጃዎች እጅን ማጽዳት ከሁሉ በበለጠ ጠቃሚ ነው።

    በተጨማሪም እጅን ሳይታጠቡ ዓይንን፣ አፍንጫንና አፍን አለመንካት እንዲሁም መጨባበጥን ማስወገድ የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት መወሰድ ካለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

  3. ሞሮኮ እንደ ፍልውሃ ያሉ የጋራ መታጠቢያ አገልግሎቶችን አገደች, ሞሮኮ እንደ ፍልውሃ ያሉ የጋራ መታጠቢያ አገልግሎቶችን አገደች

    ሞሮኮ ሃማምስ የተሰኙትን እንደ ፍል ውሃ ያሉ የህዝብ ገላ እጥበት አገልግሎት መስጫዎችን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል አገደች። የህዝብ መታጠቢያ ቦታዎቹን እገዳ ይፋ ያደረገው የሞሮኮ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ነው።

    ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጨማሪ እገዳዎችንም የጣለ ሲሆን ካፍቴሪያዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሲኒማዎችና መስጂዶችም ጭምር ዝግ እንዲሆኑ ተደርጓል።

    አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶች የሚገኙባቸው ገበያዎች ወይም የሚሸጡ ሱቆች እንዲሁም ወደ ቤት የሚወሰድ ምግብ የሚያቀርቡ ሬስቶራንቶች ግን ከእገዳው ውጭ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

    እስካሁን በሞሮኮ 29 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ተረጋግጧል። ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን እያገኙ መሆናቸውን ተከትሎ የጉዞን ጨምሮ የተለያየ እገዳ እየጣሉ ነው።

  4. አሜሪካ በበጎ ፈቃደኞች ላይ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ ጀመረች, አሜሪካ በበጎ ፈቃደኞች ላይ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ ጀመረች

    አሜሪካ ኮቪድ-19ን መከላከል የሚያስችል ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ላይ ሞከረች።

    አራት በኮሮናቫይረስ የተያዙ አሜሪካውያን ሲያትል በሚገኝ የምርምር ማዕከል ክትባቱን ወስደዋል። ክትባቱ ኮቪድ-19 ከሚያሲዘው ቫይረስ ጎጂ ያልሆነ የጄኔቲክ ኮድ ኮፒ ተደርጎ የተወሰደ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ይገልጻሉ።

    ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ክትባቱ መስራት አለመስራቱን ለማወቅ በርካታ ወራት ይጠይቃል።