በኢትዮጵያ ኮረናቫይረስ ያለበት ስድስተኛ ሰው ተገኘ

ዓለማችን በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ከታመሰች ወዲህ ከተለያዩ አገራት የሚሰሙ ዜናዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያመለክቱ ናቸው። ይህንን ተከትሎም አገራት ድንበራቸውንና ትምህርት ቤቶችን እየዘጉ ሲሆን፣ ሰዎች በርከት ብለው እንዳይሰበሰቡ እያገዱ ነው። ዛሬስ በአገራችንና በዓለማችን ኮሮናን በተመለከተ ምን እየተካሄደ ነው? ቢቢሲ አማርኛ በቀጥታ ዘገባው ያደርሳችኋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአሜሪካ እና በእንግሊዝ በኮረና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

    በአሜሪካ እና በእንግሊዝ በኮረናቫይረስ የሚሞቱ እና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

    አሜሪካ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ከ4200 በላይ ሰዎች ያላት ሲሆን የ75 ሰዎች ሞት ተመዝግቧል።

    ቫይረሱ በስፋት ከተሰራጨባቸው መካከል ኒው ዮርክ እና የዋንሽንግተን ግዛቶች ይገኙበታል።

    በእንግሊዝ ደግሞ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 67 ደርሷል።

  2. ሳዑዲ በመስጅድ የሚደረጉ ጸሎቶችን አገደች

    ሳዑዲ አረቢያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በመካ እና በመዲና ከሚገኙ ሁለት መስጅዶች ውጪ በመላው አገሪቱ በመስጅዶች የሚደረጉ ጸሎቶችን አገዳለች።

    የመካከለኛው ምሥራቅ ትልቋ ነዳጅ አምራችና የእስልምና ቅዱስ ቦታዎች መገኛ አገር ሳዑዲ ከዚህ ቀደም ሃይማኖታዊ ጉዞዎችን ማገዷ ይታወሳል።

    ሳዑዲ አረቢያ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ 133 ሰዎች ይገኙባታል።

  3. ሰበር, ሰበር, በኢትዮጵያ ኮረናቫይረስ ያለበት ስድስተኛ ሰው ተገኘ

    በኢትዮጵያ ኮረናቫይረስ ያለበት ስድስተኛ ሰው ተገኘ

    የጤና ጥበቃ ሚንስትሯ ሊያ ታደሰ ቫይረሱ የተገኘባት የ59 ዓመት ኢንግሊዛዊት ሴት ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች መሆኗን አሳውቀዋል።

    እንግሊዛቷ ዲፕሎማት በነበረችበት ሆቴል እራሷን አግልላ መቆየቷን የጤና ሚንስትሯ አሳውቀዋል።

    የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከግለሰቧ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየትና የክትትል ስራ አጠናክሮ መቀጠሉም ተነግሯል።

    በአሁኑ ሰዓት ግለሰቧ በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላት እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም በሁኔታዎች ሳይደናገጥ በተረጋጋ መንፈስ የበሽታውን ስርጭት በመግታት የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ተጠይቋል።

  4. የጀርመን ሌቦች 50ሺህ የፊት ማስኮችን ሰረቁ

    በጀርመን 50ሺህ የፊት ማስኮች መሰረቃቸውን የጀርመኑ ዲፒኤ ዘግቧል።

    የፊት ማስኮቹ አንድ ሆስፒታል ለክሊኒኮች ለማከፋፈል ያዘጋጃቸው ነበሩ ተብሏል።

    በኮሎኝ ከተማ የሚገኘው የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ በፊት ማስኮቹ ስርቆጥ ብስጭታቸውን ገልጸዋል።

    “በሳንቲም ደረጃ ይሸጡ የነበሩ ቁሶች ስለመዘረፋቸው ነው እያወራን ያለነው። አሁን ላይ ብዙ ሊጠየቅባቸው እንደሚችል ግልጽ ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

    የማስኮቹ ስርቆት ከተሰማ በኋላ የከተማዋ አስተዳደር ኃላፊዎች ወደ የፊት ማስክ ቆጠራ እና ጥንከር ወዳለ ጥበቃ ተሸጋግረዋል።

  5. ማኔ ሴኔጋል የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለምታደርገው ጥረት የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

    የሊቨርፑል እና የሴኔጋል የፊት መስመር ተጫዋቹ ሳዲዮ ማኔ አገሩ ሴኔጋል የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለምታደርገው ጥረት የ45 ሺህ ዩሮ ድጋፍ አደረገ።

    የማኔ ወኪል ተጫዋቹ የገንዘብ ድጋፉን ማድረግ የወሰነው በሴኔጋል የኮሮናቫይረስ በፍጥነት የመሰራጨቱ ዜና ከተሰማ በኋላ መሆኑን ተናግሯል።

    ከዚህ በተጨማሪ ማኔ ዜጎች እራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ በማህበራዊ ሚዲያ መልዕክት አስተላልፏል።

    እስካሁን በሴኔጋል በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 27 ደርሷል።

  6. ግብጽ በአፍሪካ በርካታ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ያሉባት አገር ሆናለች

    ግብጽ በአፍሪካ በርካታ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ያሉባት አገር ስትሆን ደቡብ አፍሪካና አልጄሪያ ደግሞ በሁለተኛና በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

    በግብጽ 166፣ በደቡብ አፍሪካ 62 እንዲሁም በአልጄሪያ 60 በኮረናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ይገኛሉ።

    እስካሁን 30 የአፍሪካ አገራት ቫይረሱን በግዛታቸው ውስጥ መገኘቱን ሪፖርት አድርገዋል።

    ይህ ካርታ እስካሁን ድረስ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ የተረጋገጠባቸው አገራት ሲሆኑ የተያዙና በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል።

  7. የአውሮፓ ዋንጫ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት በአንድ ዓመት ተራዘመ

    የዘንድሮው [2020] የአውሮፓ ዋንጫ በሚቀጥለው ዓመት እንዲካሄድ መወሰኑ ተነገረ።

    የአውሮፓ የእግር ኳስ ማህበር ባካሄደው አስቸኳይ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ውድድሩ በቀጣይ ዓመት እንዲካሄድ ወስኗል።

    የዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ከሰኔ 12 እስከ ሐምሌ 5 ከአስር በላይ በሚሆኑ የአውሮፓ ከተሞች እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር።

    የአውሮፓ ዋንጫ እንዲራዘም መደረጉ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተቋርጠው የሚገኙት የአውሮፓ ሊጎች እንዲጠናቀቁ ጊዜ ይሰጣል ተብሏል።

  8. እነዚህ ጥንዶች የኮሮናቫይረስ በተከሰተባት ቻይና፤ ዉሃን ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።

    ሴቷ ነርስ ስትሆን ከወራት በፊት በኮሮናቫይረስ ትያዛለች።

    ባለቤቷም ተንከባክቦ ከቫይረሱ እንድትድን አድርጓታል።

    የፊልም ባለሙያ የሆነው ባል አጠቃላይ ሂደቱን ቀርጾ በሚከተለው መልኩ ለዓለም አጋርቷል።

  9. የጀርመን ‘ቢግ ብራዘር’ ተሳታፊዎች ስለኮሮና ስርጭት ሊነገራቸው ነው

    የጀርመኑ ‘‘የቢግ ብራዘር’’ ተሳታፊዎች ስለኮሮናቫይረስ ስርጭት መረጃ ሊሰጣቸው ነው።

    ከ6 ሳምንታት በፊት ነበር የጀርመን ቢግ ብራዘር ተሳታፊዎች ወደ ሚቆዩበት ቤት የገቡት።

    ተሳታፊዎቹ ወደ ሚቆዩበት ቤት ሲገቡ ኮሮናቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻይናዋ ዉሃን ከተማ ውጪ ተገኘ እየተባለ የሚዘገብበት ወቅት ነበር።

    ዛሬ ላይ በጀርመን ብቻ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ7 ሺህ በላይ ሆኗል፤ 14 ደግሞ ሰዎች ሞተዋል።

    14 ወንድና ሴት ተሳታፊዎች ስለቫይረሱ ስርጭት ዛሬ ምሽት ይነገራቸዋል ተብሏል።

    ይህን ፕሮግራም የሚስተላልፈው ሳት1 የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ለተሳታፊዎቹ ስለቫይረሱ ስርጭት ለማሳወቅ የወሰነው ከተሳታፊ ቤተሰቦች ጋር ከተመካከር በኋላ መሆኑ ተነግሯል።

  10. 15 የፖላንድ ሚኒስትሮች ወደ ለይቶ ማቆያ ተወሰዱ

    ኮሮናቫይረስ ከተገኘበት አንድ ሚኒስትር ጋር ስበሰባ ተቀመጠው የነበሩ 15 የፖላንድ መንግሥት ሚንስትሮች ወደ ለይቶ ማቆያ ተወሰዱ።

    የ29 ዓመቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሚካል ዎስ ትናንት ምሽት ነበር በኮሮናቫይረስ መያዙን ይፋ ያደረገው።

    ከሚኒስትሩ ጋር ስበሰባ ለማድረግ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ 24 ሚኒስትሮች ቀጠሮ ይዘው ነበር።

    ይሁን እንጂ ከ24ቱ ሚኒስትሮች ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ዘጠኝ ሚኒስትሮች በአጋጣሚ በስበሰባው ሳይሳታፉ ቀርተዋል።

    በዚያ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የተቀሩት 15 ሚኒስትሮች ወደ ለይቶ ማቆያ ተወስደዋል።

    በፖላንድ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 177 ሲሆን እስካሁን 4 ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸው ተረጋግጧል።

  11. በኮሮናቫይረስ ስጋት ኢራን 85 ሺህ እስረኞችን ‘በጊዜያዊነት’ ለቀቀች

    ኢራን በእስር ቤቶች ውስጥ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በማሰብ 85 ሺህ እስረኞችን መልቀቋን አስታወቀች።

    የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ “እስከ አሁን 85 ሺህ የሚሆኑ እስረኞችን በጊዜያዊነት ለቀናል። በእስር ቤቶች ውስጥ ጠንከር ያለ የበሽታው ቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችንም እያከናወንን እንገኛለን” ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ በጊዜያዊነት የተለቀቁት እስረኞች መቼ ወደ እስር ቤት እንደሚመለሱ አላሳወቁም።

    ከእስር ከተለቀቁት መካከል የፖለቲካ እስረኞችም ይገኙበታል ተብሏል።

    በኢራን እስካሁን ድረስ በኮረናቫይረስ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 853 የደረሰ ሲሆን 15 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  12. ተመራማሪዎች ሰውነታችን የኮሮናቫይረስን ሊከላከል የሚችልበትን መንገድ ለዩ

    የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች የሰውነታችን በሽታን የመከላከል ሥርዓት እንዴት አድርጎ ኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስን] ሊዋጋው እንደሚችል ለመለየት ችለዋል።

    'ኔቸር' በተሰኘው የህክምና መጽሔት ላይ ዛሬ በወጣው የምርምር ግኝት መሰረት፤ ሰዎች ከኮሮናቫይረስ እየዳኑ ያለው ከጉንፋን በሚድኑበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አረጋግጠዋል።

    ባለሙያዎቹ እንዳሉት በዚህ ወቅት የትኞቹ የሰውነት በሽታን መከላከያ ህዋሳት እንደሚታዩ መለየት በቀጣይ ክትባት ለመስራት ያግዛል።

    በዓለም ዙሪያ እስካሁን ከ160 ሺህ በላይ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ሲኖሩ ከ6500 በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን በወረርሽኙ አጥተዋል። ተጨማሪ ለማንበብ፡ ተመራማሪዎች ሰውነታችን የኮሮናቫይረስን የሚከላከልበትን መንገድ መለየት ቻሉ

  13. የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ከኮሮናቫይረስ ነፃ ሆነው ተገኙ, ኃላፊው ራሳቸውን ለይተው የተቀመጡት ቫይረሱ ከተገኘበት ጃፓናዊ ጋር የቅርብ ንክኪ ስለነበራቸው ነው

    የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ከኮሮናቫይረስ ነፃ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

    ኃላፊው ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘበት ጃፓናዊ ጋር የቅርብ ንክኪ አንደነበራቸው ከታወቀ በኋላ ላለፉት 12 ቀናት ራሳቸውን ለይተው ተቀምጠው ነበር።

    አሁን ግን በተደረገላቸው ምርመራ ነፃ መሆናቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

    ጃፓናዊው ከዶክትር ቶላ ጋር በተገናኘበት በዚያን ጊዜ "ገና ከውጪ አገር መምጣቱ ስለነበር ምንም አይነት የበሽታው ምልክት አይታይበትም ነበር" በማለት ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

    ይህ ጃፓናዊ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በአርሲ ዞን ሁለት ትምርት ቤቶችን ጎብኝቶ እንደነበረ የተናገሩት ኃላፊው እሱ በሄደባቸው ቦታዎች አብረውት የነበሩ ሰዎች ራሳቸውን ለብቻ ለይተው ክትትል እተደረገላቸው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ይህ ጃፓናዊ የኮሮናቫይረስ በሽታው እንዳለበት ተረጋግጦ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘ የኮሮናቫይረስ ታማሚ መሆኑ የተገለጸው ግን አርብ ዕለት ነበር።

  14. የኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] ወረርሽኝን ለመከላከል ማድረግ ያሉብን ነገሮች፡

    የኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] ወረርሽኝን ለመከላከል ማድረግ ያሉብን ነገሮች፡

    ● ሳል ወይም ትኩሳት ካለው ግለሰብ ቢያንስ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት ያህል መራቅ

    ● እጅዎን በአግባቡ ሳይታጠቡ አይንና አፍንጫዎን አይንኩ

    ● ከሰዎችጋር አይጨባበጡ

    ● እጅን በንጹህ ውሃና ሳሙና አዘውትረው ይታጠቡ

    ● በተለይም የህመም ስሜት ካልዎ ሰዎች ወደሚበዙባቸው ቦታዎች አይሂዱ

    ● በሚያነጥሱና በሚያስሉ ጊዜ አፍና አፍንጫዎን በሶፍት ወይም በክርንዎይሸፍኑ

    ●የተጠቀሙበትን ሶፍትና ተመሳሳይ ነገሮች ክዳን ባለው የቆሻሻማጠራቀሚያ ያስወግዱ

    ● በሥራ ቦታ፣የመጓጓዣና የመኖሪያ ወይም የመኝታ ክፍል መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር ያድርጉ

    ● መረጃን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ ያግኙ

    ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796

    (ምንጭ፡ የጤባ ጥበቃ ሚኒስቴር)

  15. በኮሮናቫይረስ ስጋት በርካታ ቻይናዊያን በኢትዮጵያ ለመቆየት እየጠየቁ ነው, የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋትን በመፍራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት ጠይቀዋል የተባሉ ጣሊያናውያን ቱሪስቶች ጉዳይ "ሐሰተኛ ወሬ" ነው ተባለ

    በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ቻይናዊያን ወደ አገራቸው ላለመመለስ በኢትዮጵያ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ቪዛ እያራዘሙ መሆኑ ተገለጸ።

    ቻይናዊያኑ ለተለያዩ ሥራዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ቆይተው በአሁኑ ወቅት የተሰጣቸው የመቆያ ቪዛ ሲያበቃ ነው ወረርሽኙን በመፍራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ፈቃድ እየጠየቁ ያሉት ተብሏል።

    በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ የኢሚግሬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ አይክፋው ጎሳዬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቂት የማይባሉ ቻይናዊያን በኢትዮጵያ ለመቆየት የሚያስችላቸውን የቪዛ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እያገኙ ነው።

    ከዚህ ባሻገርም በአንዳንድ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በርካታ ጣሊያናዊያን ቱሪስቶች በኢትዮጵያ መቆየት የሚያስችላቸው ቪዛ ቢያበቃም በአገራቸው ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋትን በመፍራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት ጠይቀዋል ለሚለው ወሬ ማረጋጫ አልተገኘም።

    ቢቢሲ ይህንኑ ለማጣርት አዲስ አበባ የሚገኘውን የጣሊያን ኤምባሲን የጠየቀ ሲሆን በተሰጠው ምላሽ መሰረት እንዲህ አይነት ጥያቄ አለመቅረቡንና የተባለው ነገር "ሐሰተኛ ወሬ" መሆኑን ተነግሮታል።

  16. "ኮቪድ-19ን በቁጥጥር ስር ለማዋል እያንዳንዱን ተጠርጣሪ መርምሩ", ኮሮናቫይረስ፡"ኮቪድ-19ን በቁጥጥር ስር ለማዋል እያንዳንዱን ተጠርጣሪ መርምሩ"

    የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19ን በቁጥጥር ስር ለማዋል አገራት በበሽታው የሚጠረጥሯቸውን ግለሰቦች በሙሉ እንዲመረምሩ አሳሰበ።

    በአሁኑ ወቅት ሁሉም የአፍሪካ አገራት ቫይረሱን የማይመረምሩ ሲሆን ይህ ደግሞ በአህጉሪቱ የህሙማንን ቁጥር ከፍ ያደርጋል ተብሎ ተሰግቷል።

    እስካሁን 30 ያህል የአፍሪካ አገራት በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ማግኘታቸውን የገለፁ ሲሆን አብዛኞቹ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሕሙማንን ብቻ ነው የመዘገቡት።

    ይህ ቢሆንም እንኳ እንደ ጉዞ እገዳ ያሉ እርምጃዎችን የወሰዱ አገራት አሉ።

    አሁንም ቢሆን ግን በርካታ አፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስን ለመመርመር የሚያስችል አቅሙ የላቸውም ተብሏል።

    ሶማሊያ በሽታውን ለመቆጣጠር ዓለም አቀፍ በረራዎችን ማገዷን በትናንትናው ዕለት አስታውቃለች።

    ሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች ሲሆን አገር አቀፍ የመንቀሳቀስ እገዳ አስቀምጣለች።

    ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በአፍሪካ ያለውን ሁኔታ ለመከታተል የተቋቋመው አፍሪካ ሲዲሲ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በፍጥነት ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይመክራል።

    ቻይናዊው ቢሊየነር ጃክማ ከአንድ ሚሊየን በላይ መመርመሪያዎችን፣ ስድስት ሚሊየን አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችንና የመከላከያ አልባሳት ለመለገስ ቃል መግባቱ ይታወሳል።

  17. ኢትዮጵያ ውስጥ ኮቪድ-19 ከተገኘበት ጃፓናዊ ጋር ንክኪ የነበራቸው 74 ሰዎች ነፃ መሆናቸው ታወቀ

    በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ከተገኘበት ጃፓናዊ ጋር ንክኪ ነበራቸው ከተባሉት 113 ግለሰቦች መካከል 74ቱ ነፃ መሆናቸውን ታወቀ።

    ይህንን ያለው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ሲሆን ቀሪዎቹ አሁንም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው ውጤታቸውን እየተጠባበቁ ነው ተብሏል።

    በኢትዮጵያ አስካሁን ድረስ አምስት ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው መረጋገጡ ይታወሳል። ህሙማኑ በአሁኑ ጊዜ በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ኢንስቲቲዩቱ ገልጿል።

    በበሽታው ከተያዙት አምስት ሰዎች መካከል ሶስቱ የጃፓን ዜግነት ያላቸው ሲሆን አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው።

    ከእነዚህ አምስት ሰዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተለዩ 992 ሰዎች ለ14 ቀን ራሳቸውን ለይተው እንደሚያቆዩ ለማወቅ ተችሏል።

  18. አውሮፓ ድንበሯን ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት አቅዳለች, እገዳው ለቀጣዮቹ 30 ቀናት የሚቆይ መሆኑ ታውቋል

    የአውሮፓ ኮሚሽን በአገራት መካከል አላስፈላጊ ያላቸውን ጉዞዎች ሊከለክል ነው። ይህ የአውሮፓ ኮሚሽን እቅድ የተሰማው በርካታ የአውሮፓ አገራት ድንበራቸውን መዝጋት በመጀመራቸው ነው።

    የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን ከዛሬ ጀምሮ የአገራቱ መሪዎች እርምጃ መውሰድ እንዲጀምሩ እንደመሚጠይቁ ተናግረዋል።

    “ ጉዞ በቀነስን ቁጥር፣ ቫይረሱን የመገደብ እድላችን ይሰፋል” ሲሉም ተናግረዋል።

    የፈረንሳዩ ፕረዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአውሮፓ የውጪ ድንበሮች ለተጓዦች ዝግ ይሆናል ብለው ተናግረው ነበር።

    “ በተጨባጭ አውሮፓ ህብረት አባል አገራት እና በአውሮፓ አገራት መካከል የሚደረገው ጉዞ ይቋረጣል” ነበር ያሉት ማርኮን።

    ረዥም ጊዜ በአውሮፓ አገራት ውስጥ የኖሩ፣ የአውሮፓ አገራት ውስት ቤተሰቦቻቸው ያሉ፣ ዲፕሎማቶች በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች፣ ድንበር ተሻጋሪ ሰራተኞች፣ እንዲሁም እቃ የሚያጓጉዙ መኪኖች ይህ እገዳ አመለከታቸውም ብለውዋል። ይህ እገዳ ለቀጣዮቹ 30 ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

    የሸንገን ስምምነት ሰዎች በአውሮፓ አገራት መካከል በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ይፈቅዳል።

  19. የኮሮናቫይረስ ምልክት ለሚታይባቸውና በቫይረሱ ለሚያዙ ታራሚዎች ለይቶ ማከሚያ ተዘጋጅቷል ተባለ, የኮሮናቫይረስ ምልክት ለሚታይባቸውና በቫይረሱ ለሚያዙ ታራሚዎች ለይቶ ማከሚያ ተዘጋጅቷል ተባለ

    የኮሮናቫይረስ ምልክት ለሚታይባቸው እንዲሁም በቫይረሱ ለሚያዙ ታራሚዎች ለይቶ ማከሚያ መዘጋጀቱን በፌደራል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ገረመው አያሌው ለቢቢሲ ገለፁ።

    አቶ ገረመው እንደገለፁት ለይቶ ማከሚያ ሆኖ የተዘጋጀው በተለምዶ አባሳሙኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያለ አዲስ ማረሚያ ቤት ነው።

    ማረሚያ ቤቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራቱን በማረሚያ ቤቶች ያለውን ሁኔታ የሚከታተል አካልም በጤና ሚኒስቴር መመደቡንም ገልፀዋል አቶ ገረመው።

    እሳቸው እንደሚሉት ተደራጅቶ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በማረሚያ ቤት ያለውን ሁኔታ የሚከታተል በከፍተኛ ሃላፊዎች የሚመራ ቡድን ተቋቁሟል። የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦት እንዲጨምርም ስራዎች እየተሰሩ ነው።

  20. ተመራማሪዎች ሰውነታችን የኮሮናቫይረስን የሚከላከልበትን መንገድ መለየት ቻሉ, የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች ሰውነታችን ራሱን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል አራት ዓይነት የመከላከያ ሕዋሶች እንደሚጠቀም መለየታቸውን ገለፁ።

    የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች የሰውነታችን በሽታን የመከላከል ሥርዓት እንዴት አድርጎ ኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስን] ሊዋጋው እንደሚችል ለመለየት ችለዋል።

    'ኔቸር' በተሰኘው የህክምና መጽሔት ላይ ዛሬ በወጣው የምርምር ግኝት መሰረት፤ ሰዎች ከኮሮናቫይረስ እየዳኑ ያለው ከጉንፋን በሚድኑበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አረጋግጠዋል። ባለሙያዎቹ እንዳሉት በዚህ ወቅት የትኞቹ የሰውነት በሽታን መከላከያ ህዋሳት እንደሚታዩ መለየት በቀጣይ ክትባት ለመስራት ያግዛል።

    "በምርምር ለማወቅ የተቻለው ጠቃሚ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ይህ የሰውነት የመከላከያ ሥርዓታትን በምን መልኩ የኮሮናቫይረስን እንደሚዋጋ በመረዳት በኩል የመጀመሪያው በመሆኑ ነው" ሲሉ የምርምሩ አካል የሆኑት ካትሪን ኬደዜርስካ ተናግረዋል። ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አንጻር ተመራማሪዎች የደረሱበት ይህ ግኝት "ፈር ቀዳጅ" እንደሆነ ተነግሮለታል።

    አስካሁን በርካታ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች የዳኑ ሲሆን፤ ይህም የሰው ልጅ በሽታን የመከላከል ሥርዓት በተሳካ ሁኔታ ቫይረሱን ተቋቁሞ ማሸነፍ ይችላል ማለት ነውም ተብሏል።