የቀራጺ ማይክል አንጀሎን ዝነኛ የራቁት ሐውልት ለተማሪዎች ያሳየችው አስተማሪ ተባረረች

የማይክል አንጀሎ 'ዴቪድ' የተሰኘው ሥራው የወንድ ብልት በግላጭ የሚታይበት ነው
የምስሉ መግለጫ, የማይክል አንጀሎ 'ዴቪድ' የተሰኘው ሥራው የወንድ መራቢያ አካል በግላጭ የሚታይበት ነው
ታትሟል

በአሜሪካ ፍሎሪዳ አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ለተማሪዎች የዝነኛውን ሠዓሊና ቀራጺ ማይክል አንጀሎን ሥራ ለተማሪዎች አሳይተሻል በሚል ተባረረች።

የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲመለከቱት ተደርገዋል የተባለው የሐውልት ቅርጽ ሥራ ‘ዳዊት’ የተሰኘው የማይክል አንጀሎ ዝነኛ የጥበብ ሥራው ነው።

ይህ ታላቅ የጥበብ ሥራ በምዕራቡ ዓለም ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውና የዘመነ ሕዳሴን ጥበብ ማንሰራራት ከሚያወሱ ሥራዎች አንዱ ነው።

ሠዓሊ፣ ገጣሚና ቀራጺ ማይክል አንጀሎ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ታላቅ የጥበብ ሰው ሲሆን ይህን ‘ዳዊት’ የተሰኘውን ሥራ የቀረጸው እንደ ጎረጎሮሲያዊያኑ ከ1501-1504 ዓ/ም ባለው ጊዜ ነበር።

ይህ ‘ዳዊት’ የተሰኘው የሐውልት ቅርጽ ሥራው ታዲያ የወንድ ብልት ተጋልጦ የሚታይበት በመሆኑ ነው ወላጆች ቅሬታ ያቀረቡት።

‘ለልጆቻችን ልቅ ወሲብ (ፖርኖግራፊ) እንዲመለከቱ ሆነዋል’ በሚል ከአንድም ሁለት ሦስት ወላጆች ቅሬታ የቀረበባት ርዕሰ መምህርት መልቀቂያ እንድታስገባ ተገዳለች።

ተማሪዎቹ ይህን ሥራ እንዲመለከቱ የተደረጉት እየተማሩ የነበሩት የትምህርት ዓይነት “የሕዳሴ ዘመን ሥነ ሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ” ስለነበረ ነው።

ይሁንና አንድ ወላጅ ሐውልቱ ‘ልቅ ወሲብ’ ነው በማለታቸውና ሌሎች ሁለት ወላጆች ደግሞ ተማሪዎች የሚማሩትን አወዛጋቢ ርዕሰ ጉዳይ ቀድሞ ሊነገረን ይገባል ብለው ቅሬታ በማቅረባቸው ነው መምህርቷ የተሰናበተችው።

ርዕሰ መምህርት ሆፕ ካራሳኪላ በፍሎሪዳ በሚገኘው ቴላሃሲ ክላሲካል ትምህርት ቤት ነበር የምትሠራው።

ይህ ያልተጠበቀ ቅሬታ ከወላጅ መቅረቡን ተከትሎ የትምህርት ቤቱ ቦርድ ሁለት ምርጫ ሰጥቷታል። በገዛ ፈቃድ መልቀቅ አልያም መልቀቂያ ካላስገባች እንደሚያባርሯት።

ባለፈው ሐሙስ ሪፐብሊካኑ የፍሎሪዳ ገዥ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ሥነ ጾታ ትምህርቶችን ለልጆች እንዳያስተምሩ የሚለውን መመሪያ ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም እንደሚያስፋፉት ጠቁመው ነበር።

በአሜሪካ የጾታ ትምህርት ጉዳይ በሪፐብሊካኖችና በዲሞክራቶች መሀል ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል።

ልጆች በየትኛው ዕድሜ ምን መማር አለባቸው? የሚለውም የአሜሪካንን ማኅብረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ እያከራከረ ያለ ጉዳይ ነው።

በተለይ በ2024 ዓ/ም ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ይሆናሉ፣ ምናልባትም ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ሰፊ ግምት የተሰጣቸው የፍሎሪዳ ገዥ ዴ ሳንቶስ በግዛታቸው ሁለት ቁልፍ የሥርዓተ ትምህርት ረቂቆች እንዲጸድቁ አድርገዋል።

ከነዚህም አንዱ ልጆች የሥነ ጾታና የጾታ ማንነት ትምህርቶችን በዚያ ዕድሜያቸው እንዳይሰጣቸው የሚደነግግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የአሜሪካንን የጥቁሮች ታሪክ ተማሪዎች ጨርሶውኑ እንዳይማሩ የሚያደርግ ነው።