ባይደን አሜሪካ በፑቲን ኃላፊነት የጎደለው ዛቻ አትሸበርም አሉ

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው በቭላድሚር ፑቲን ኃላፊነት በጎደላቸው ዛቻዎች እንደማትደናገጥ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቁጥጥራቸው ስር ያሉ አራት የዩክሬን ግዛቶችን መጠቅለላቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

ፑቲን ወደ ሩሲያ የተቀላቀሉትን አዳዲሶቹን የዩክሬን ግዛቶች ለመጠበቅ ኒውክሊየር ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል የዛቱ ሲሆን፣ ግዛቶቹ “ለዘላለሙ” የሩሲያ አካል ሆነዋል ብለዋል።

የኔቶ ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ የግዛቶቹን መጠቅለል “ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የታየ እጅግ አሳሳቢው ክስተት” ነው ብለዋል።

በኼርሶን፣ ዛፖሪዢያ፣ ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ የተባሉት አካባቢዎች ላይ በቅርቡ በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ ነዋሪዎቹ “ከሕዝባቸው እና ከእናት አገራቸው” ጋር ለመቀላቀል ወስነዋል ሲሉ ፑቲን ተናግረዋል።

ሆኖም ዩክሬን እና ምዕራውያን ድርጊቱን አሳፋሪ ሲሉ አውግዘውታል።

የፑቲን ንግግር በአመዛኑ ያነጣጠረው ምዕራባውያን ላይ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ አሜሪካ ጃፓን ላይ ኒውክሊየር መጠቀሟን አስታውሰዋል።

ፑቲን ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር አገራቸው “በርካታ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን መታጠቋን” ገልጸው፣ አስፈላጊ ሲሆን ያለንን አማራጭ ሁሉ እንጠቀማለን ብለዋል። ይህንን የምለው ለማስፈራራት አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።

በአዳዲሶቹ ግዛቶች ላይ የሚቃጣ ማንኛው አይነት ጥቃት በሩሲያ ላይ እንደተቃጣ ይቆጣራል ሲል፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ያስጠነቀቀ ሲሆን ይህም ውዝግቡን እንዳያባብሰው ተስግቷል።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለፑቲን በሰጡት ምላሽ የግድየለሽ ንግግሮች እና ማስፈራሪያዎች አያሸብረንም ብለዋል።

“አሜሪካ እና አጋሮቿ አይሸበሩም” ብለዋል ባይደን በዋይት ሐውስ ባደረጉት ንግግር።

ወደ ካሜራ እጃቸውን እየጠቆሙ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት በቀጥታ ባደረጉት ንግግር “አሜሪካ የኔቶ ግዛትን እያንዳንዷን ኢንች ለመጠበቅ ከአጋሮቿ ጋር ዝግጁ ናት። ፑቲን! በተሳሳተ መንግድ እንዳትረዳኝ ያልኳት እያንዳንዷን ኢንች ነው” ብለዋል።

ከዚህ ንግግር በኋላ የባይደን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሞስኮ ኒውክሊየር የምትችልበት ዕድል እንዳለ ከገለጹ በኋላ ከባድ ስጋት እንደለሌ ተናግረዋል።  

ግዛቶቿ ወደ ሩሲያ የተጣቀለሉባት ዩክሬን በአስቸኳይ የኔቶ አባል እንድትሆን ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ የሩሲያን እርምጃ የተቃወሙት የኔቶ አባላት ምን እንደሚወስኑ በቀጣይ ሳምንታት ይሚታወቅ ይሆናል።

የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያ የተያዙባቸውን ግዛቶቻቸው ለማስመለስ ወታደራዊ ዘመቻዎችን እያካሄዱ ሲሆን፣ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አርብ ዕለት እንዳሳወቀው ኃይሎቹ አንዳንድ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪም ኃይሎቻቸው ሁሉንም ግዛቶቻቸውን ከሩሲያ ወረራ እስከሚያስለቅቁ ድረስ ፍልሚያቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን መጠቅለሏን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ሩሲያ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣኗን ተጠቅማ ውድቅ አድርጋዋለች።

የውሳኔ ሐሳቡ ቀድሞውኑም በሩሲያ ውድቅ እንደሚሆን የተጠበቀ ሲሆን፣ ቻይና እና ሕንድ ደግሞ ድምጸ ታዕቅቦ አድርገዋል።

ሩሲያ አራቱን የዩክሬን ግዛቶችን በይፋ የግዛቷ አካል መሆናቸውን ማወጇን ተከትሎ ከተለያዩ አገራት ተቃውሞና ውግዘት የቀረበባት ሲሆን፣ ምዕራባውያውን አገራት ተጨማሪ ዕቀባዎችን በሞስኮ ላይ እንደሚጥሉ አሳውቀዋል።