ታዋቂው አሜሪካዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ኳታር ውስጥ በድንገት ሞተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ዋንጫን ለመዘገብ ኳታር የነበረው ታዋቂው አሜሪካዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ግራንት ዋህል በድንገት መሞቱ ተገለጸ።
ኳታር ሳለ የሞተው የ48 ዓመቱ ጋዜጠኛ ትላንት አርብ የአርጀንቲ እና እና የኔዘርላንድስን ጨዋታ እያየ ሳለ በድንገት ራሱን መሳቱ ተነግሯል።
እስካሁን የወጡ ሪፖርቶች የልብ ድካም ገጥሞት ሊሆን እንደሚችል ቢጠቁሙም፣ በይፋ የተረጋገጠ ነገር የለም።
ባለፈው ወር ጋዜጠኛው የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን ለመደገፍ የቀስተ ደመና ምሥል ያለበት ቲሸርት ለብሶ ወደ ስታዲየም ሊገባ ሲል በኳታር ለአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
የጋዜጠኛውን ሞት ተከትሎ የአሜሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽን “ልብ የሚሰብር ዜና” ሲል መግለጫ አውጥቷል።
“የእግር ኳስ እና ጋዜጠኛነት ወዳጆች ሁሌም ቢሆን ግራንት በሚሠራው ዜና ይተማመናሉ። ስለ እግር ኳስ ጨዋታዎች አዝናኝ እና ዝርዝር መረጃ የያዙ ዘገባዎች እየሠራ ነበር” ብሏል መግለጫው።
የግራንት ባለቤት ሴሊን ጎውደር “ከባድ ድንጋጤ ውስጥ ነኝ። በዚህ ጊዜ የደገፋችሁኝ ጓደኞቼ አመሰግናችኋለሁ” ስትል ትዊት አድርጋለች።
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ “ጋዜጠኛው ለእግር ኳስ ጥልቅ ፍቅር ነበረው። በመላው የእግር ኳሱ ዓለም ይናፈቃል” ብለዋል።
በኳታር የዓለም ዋንጫን የሚያዘጋጀው ኮሚቴ ቃል አቀባይ በበኩሉ “አሜሪካዊው ጋዜጠኛ በመሞቱ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል። ግራንት ለእግር ኳስ ባለው ፍቅር ነው የሚታወሰው። ኳታር የመጣው ስምንተኛ የዓለም ዋንጫ ዘገባውን ለመሥራት ነበር” ብለዋል።
ጋዜጠኛው የአርጀንቲና እና የኔዘርላንድስን ጨዋታ ለመዘገብ በሉሴይል ስታድየም የጋዜጠኞች ክፍል ውስጥ ሳለ እንደታመመ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
“ወዲያው ድንገተኛ ሕክምና ተደርጎለታል። ከዚያም ወደ ሐማድ አጠቃላይ ሆስፒታል ተወስዷል። የቤተሰቡን ፍቃድ ተከትሎ አስክሬኑን ወደ አሜሪካ ለመመለስ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር እየተነጋገርን ነው” ሲሉ አክለዋል።
ጋዜጠኛው እአአ በ1994 በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ከዘገበ በኋላ ለተከታታይ ስምንት ጊዜ የዓለም ዋንጫን ውድድርን ዘግቧል።
በአረቡ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለውን የዓለም እግር ኳስ ውድደርን ለመዘገብ በርካታ ጋዜጠኞች እዚያው ይገኛሉ።
በተጨማሪም በቢሊዮኖች የሚቆጠር የዓለም ሕዝብ በተለያዩ አገራት ውስጥ ሆኖ የእግር ኳስ ውድድሩን በቀጥታ የሚከታተል ሲሆን፣ እንዲሁም ከስፍራው የተለያዩ ዘገባዎችን በቀጥታ ከጋዜጠኞች ያገኛል።












