ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ የአማጺ ቡድን መሪውን ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች
አሜሪካ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰው አማጺ ቡድን መሪን ለመያዝ የሚያስችል መረጃ ለሰጠ 5 ሚሊዮን ዶላር ሸልማለሁ አለች።
በአሜሪካ የሚፈለገው ሴካ ሙሳ ባሉኩ የተባለው ግለሰብ በምስራቅ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በስፋት የሚንቀሳቀሰውን አላይድ ዴሞክራቲክ ፎርስ (ኤዲኤፍ) የተባለ ጽንፈኛ ቡድንን ይመራል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ይህ ከእስላሚክ ስቴት ቡድን ጋር ቁርኝነት ያለው ቡድን በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል፤ የሰውነት አካልን ቆርጧል፣ አስገድዶ ደፍሯል እንዲሁም ሕጻናትን ጨምሮ በርካቶችን ጠልፎ ወስዷል ይላል።
በፈረንጆቹ 2021 ላይ አሜሪካ አላይድ ዴሞክራቲክ ፎርስ አሸባሪ ድርጅት ነው ስትል ፈርጃዋለች።
የኤዲኤፍ መሪው ሴካ ሙሳ ባሉኩ ትውልዱ ኡጋንዳ ሲሆን እአአ 1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በትውልድ አገሩ ጥቃት ይሰነዝር ነበር።
የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ሙስሊሞችን ይበድላሉ በማለት መንግሥት ላይ አንጃ አነስቶ የነበረው ቡድን ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ከተሻገረ በኋላ ጂሃዲስት በመሆን ሌላ ገጽታን ተላብሷል።
ቡድኑ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በኡጋንዳ ጦር ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተሻግሮ ሰሜን ኪቩ ግዛት መሽጎ ይገኛል።
እአአ 2015 ላይ የቀድሞ የቡድኑ መሪ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ አሁን በአሜሪካ የሚፈለገው ግለሰብ ጽንፈኛ ቡድኑን ላለፉት 8 ዓመታት ሲመራ ቆይቷል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አሃዝ ከሆነ ሴካ ሙሳ ባሉኩ የሚመራው ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት በለተይ የክርስትና እምነት ተከታዮችን ዒላማ በማድረግ ከ200 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከ40ሺህ የማያንሱትን ደግሞ ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል።