ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኤርዶዋን ድል ቱርካውያን ደስታቸውን በአደባባይ እየገለጹ ነው
በቱርክ ጣይብ ኤርዶዋን ለሌላ አምስት ዓመት ለመምራት የሚያስችላችውን ድምጽ ማግኘታቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው ምሽቱን ደስታቸውን ሲገልጹ አምሽተዋል።
“85 ሚሊዮን ሕዝብ ነው ያሸነፈው ዛሬ” ብለዋል ኤርዶዋን ከግዙፉ ቤተ መንግሥት ደጅ ለተሰበሰበው ደጋፊያቸው።
ይሁንና የኤርዶዋን ለአንድነት ያቀረቡት ጥሪ ከልብ የመሆኑ ነገር ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ይህም በተቀናቃኛቸው ከማል ክሎችዳሮሉ ማፌዛቸው፣ እንዲሁም በተሳሪው የኩርድ መሪ ላይ የሰነዘሩት ዛቻ እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን በሚደግፉ ፖሊሲዎች ዙርያ የሰላ ትችት መሰንዘራቸው ኤርዶዋን እንዴት አንድነት ሊያመጡ ይችላሉ የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
የኤርዶዋን ተቀናቃኝ ከማል ክሎችዳሮሉ እስከአሁን በይፋ መሸነፋቸውን ይፋ አላደረጉም።
የኤርዶዋን ድል በምርጫ ቦርድ ካውንስልም በይፋ አልተገለጸም።
ክሎችዳሮሉ “በቅርብ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ኢ-ፍትሐዊ ምርጫ” ሲሉ ተችተውታል።
ከማል ክሎችዳሮሉ ተቀናቃኛቸው ኤርዶዋንና ፓርቲያቸው የመንግሥትን ሃብት በሙሉ ለምርጫ ቅስቀሳ አውለውታል ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል።
ኤርዶዋን በድጋሚው ምርጫ ያገኙት ድምጽ 52 ከመቶ ሲሆን ይህም ገና በምርጫ ቦርድ ይፋ ያልተደረገ ነው።
ወደ ግማሽ የሚጠጋው ሕዝብ የኤርዶዋንን ‘ወደ አምባገነንነት የቀረበውን የኤርዶዋን አገዛዝ’ የሚቃወም መሆኑን አሳይቷል።
ኤርዶዋን ለመጀመርያ ጊዜ ድል ማድረጋቸውን ይፋ ያደረጉት ሌሊት ላይ አውቶቡስ ጣሪያ ላይ ወጥተው ወደ 320ሺህ ለሚጠጉ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ነው።
“እኛ ብቻ አይደለንም ያሸነፍነው፤ ቱርኪዬ ናት ያሸነፈችው” ብለዋል።
ምርጫውንም በቱርክ ታሪክ እጅግ ወሳኙ ምርጫ ሲሊ ጠርተውታል።
ባላንጣቸው የነበሩትን ከማል ክሎችዳሮሉን ‘ደህና ሰንብት ከማል! ደህና ሰንብትማ!’ ሲሉ አፊዘውባቸዋል። ደጋፊዎቻቸውም ያንን ተቀብለው ‘ደህና ሰንብት ከማል’ እያሉ ሲያዜሙ ተሰምተዋል።
ምንም እንኳ በቱርክ የተደረገው ምርጫ ውጤት በይፋ በምርጫ ካውንስሉ አሸናፊው ባይገለጽም ማን እንዳሸነፈ አሻሚ አይደለም።
የኤርዶዋን ደጋፊዎች ከመላው አንካራ ድሉን ለማጣጣም ወደ ቤተ መንግሥት ሲተሙ ታይተዋል። አንዳንዶች የቱርክን ባንዲራ አንጥፈው ሲሰግዱም ታይተዋል።
ባለፈው ምሽት የቱርክ የኢኮኖሚ ችግር ለአንድ ቀንም ቢሆን ተረስቶ ነበር።
ሴይሃን የተባለ የኤርዶዋን ደጋፊ “የኢኮኖሚ ችግር አለ የሚባለው ውሸት ነው፤ በኤርዶዋን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደስተኞች ነን። በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ከዚህ በላይ ያሳካል” ብሏል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በበኩላቸው የቱርክን የዋጋ ንረትና ግሽበት ማከም መንግሥታቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
የቱርክ ገንዘብ ሊራ ከዶላር ጋር ሲወዳደር በታሪክ ዝቅተኛ ምጣኔ ያስመዘገበበት ጊዜ ነው።
የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ምጣኔም ከ84% በላይ ደርሷል።
ኤርዶዋን አሸባሪ ብለው የሚጠሯቸው የኩርድ መሪ ሰላሃቲን ዴሚርታስ እርሳቸው በሥልጣን እስካሉ ድረስ ከእስር እንደማይፈቱ ይፋ አድርገዋል።
በቅርብ ወራት በደረሰ ርእደ መሬት የተጎዱትን ሁለት ከተሞችም መልሶ ለመገንባት ቃል ገብተዋል።
የሶሪያ ስደተኞችን በበጎ ፈቃድ ላይ በተመሰረተ ሂደት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደሚያግዙም ተናግረዋል።
በቱርክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶሪያዊያን በስደት ይገኛሉ።
የኤርዶዋንን ድል ተከትሎ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከገልፍ አገራት ሳይቀር ቱርካዊያን ወደ ኢስታንቡል ታክሲም አደባባይ እየተመሙ ነው።