የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት የሩዋንዳ አቻቸው ካጋሜን ከሂትለር ጋር አነጻጸሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ትሺስከዲ የሩዋንዳ አቻቸው ካጋሜን ከሂትለር ጋር በማነጻጸር ወረፉ።
ፕሬዚዳንት ፌሊክስ የሩዋንዳውን መሪ ፖል ካጋሜን እንደ ሂትለር ዓይነት ባህርይ እያሳዩ ነው ያሏቸው ሲሆን “እመኑኝ መጨረሻው እንደ ሂትለር ነው የሚሆነው” ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት በሩዋንዳ ድንበር አቅራቢያ በቡካቩ በነበረ የምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ ነው።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ሩዋንዳ በአገራቸው ምሥራቃዊ ክፍል ያሉ አማጺያንን ትደግፋለች ሲሉ በተደጋጋሚ ወቀሳ ያሰማሉ።ሩዋንዳም በበኩሏ የሚቀርብባትን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
ፕሬዚዳንቱ ካጋሜን ከሂትለር ጋር ማነጻጸራቸውን ተከትሎ የሩዋንዳ መንግሥት ቃለ አቀባይ አስተያየታቸውን “ከባድ እና ግልጽ የሆነ ማስፈራሪያ” ሲሉ ገልጸውታል።
ሁለት ሳምንታት በቀረው የኮንጎ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ የሚወዳደሩት ፕሬዚዳንቱ ድጋፍ ለማሰባሰብ እየሞከሩ ነው። በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ያለውን ግጭት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ጨምሮ የቀጠናዊ እና የተባበሩት መንግሥታት ወታደሮች ቢሰፍሩም ፍሬ አላፈራም።
ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪዎቹ በአሁኑ ወቅት አገሪቷን ለቀው ሊወጡ በዝግጅት ላይ ናቸው።
በቱትሲ የሚመሩት ኤም23 አማጺያንን ጨምሮ በርካታ የታጠቁ ቡድኖች በአገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ ማስከተላቸውን ቀጥለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ኤም23 የተሰኙት አማጺያን በሩዋንዳ እንደሚደገፉ በተደጋጋሚ የሚናገሩ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የባለሙያዎች ቡድን ከወራት በፊት ባወጣው ዘገባም ይህንኑ የሚያጠናክር ግኝት አውጥቷል። አሜሪካም ይህንንም ግኝት ደግፋዋለች።
ኤም23 የተሰኘው አማጺ ቡድን የኮንጎ ግዛትን በመቆጣጠር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያፈሩትን ንብረት እና ቤታቸውን ጥለው እንዲሸሹ አስገድዷቸዋል።
ፕሬዚዳንት ፌሊክስ አርብ ምሽት ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር “እንደ አዶልፍ ሂትለር ግዛት የማስፋፋት ህልም ይዞ ስለተነሳ እመኑኝ መጨረሻው እንደ አዶልፍ ሂትለር ነው የሚሆነው” ሲሉም ተናግረዋል።
አክለውም “ነገር ግን አቻውን አግኝቷል- እሱን ለማስቆም እና አገሩን ለመጠበቅ የቆረጠ ሰው” ብለዋል።
ለስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆነው ሂትለር በአውሮፓውያኑ 1945 ራሱን ማጥፋቱ ይታወሳል። ሂትለር የጀርመንን ግዛት ለማስፋት ያደረገውም ጥረት ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አምርቶ ጥፋት አስከትሏል።
ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ከዚህ ቀደም የሩዋንዳውን ፕሬዚዳንት “የዲሞክራቲክ ኮንጎ ጠላት” ሲሉም ገልጸዋቸው ነበር። የሚቀርብባቸውን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ የሚያደርጉት ካጋሜም ፕሬዚዳንት ፌሊክስን “ጦርነት ቀስቃሽ” ሲሉ ከዚህ ቀደም ተችተዋቸው ነበር።












