ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘በተሳሳተ ማንነት’ የታሰሩት አንጋፋው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ተለቀቁ
በፖሊስ ‘በተሳሳተ ማንነት’ በቁጥጥር ስር የዋሉት አንጋፋው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ከእስር ተለቀቁ።
ፖሊስ የ65 ዓመቱን አንጋፋ ጋዜጠኛ ማቻሪያ ጋይቶን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲፈልገው የነበረው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪው ፍራንሲስ ጋይቶ ጋር ተሳስተውብኝ ነው ብሏል።
ማቻሪያ በመዲናዋ ናይሮቢ ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በጸጥታ ኃይሎች ሲወሰዱም ወደ አንድ የግል መኪና ገፍተው በኃይል ማስገባት ነው
ማንነታቸውን ሊገልጹ ያልፈቀዱ ሁለት መኪኖች ሲከተሏቸው እንደነበር ተገልጿል።
ጋዜጠኛው ለደህንነታቸው ሲባል በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ያቀኑት ከ19 ልጃቸው ጋር ሲሆን እሱም በኃይል መኪና ውስጥ ተገፍቶ እንዲገባ መደረጉ ተገልጿል።
ፖሊስ በኋላ እንዳስታወቀው ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር የዋሉት በተሳሳተ ማንነት እንደሆነ ገልጿል። የሚፈልጉት ተጠርጣሪ በቅርቡ በርካታ ሴቶችን መግደሉን አምኗል የተባለው ኬንያዊ እየተደረገ ያለውን የፖሊስ ምርመራ እያጣጣለ ያለ ሰው ነው ተብሏል።
“ዛሬ ጥዋት ጋዜጠኛ ማቻሪያ ጋይቶን በቁጥጥር ስር ያዋልነው በተሳሳተ ማንነት እንደሆነ ለህዝቡ ግልጽ ማድረግ እንፈልጋለን። በእስር ልናውለው የፈለግነው ምርመራ የከፈትንበት ፍራንሲስ ጋይቶን ነበር” ሲልም ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ሁለቱ ግለሰቦች ዝምድና የላቸውም።
በማህበራዊ ድረገጾች ላይ በስፋት በተጋራው ቪዲዮ የፖሊስ መለዮ የለበሱ መኮንኖች እና የሲቪል ልብስ የለበሱ ግለሰቦች ጋዜጠኛውን እየገፉ ወደ ነጭ መኪና በኃይል ሲያስገቧቸው ይታያል።
በቅርቡ በኬንያ ከተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ወጣቶችን በህገወጥ መንገድ ፖሊስ ያፍናል የሚሉ ጉዳዮችንም እንደገና እንዲያፋፍም ምክንያት ሆኗል።
የህዝቡን ቁጣ እና ወቀሳም ተከትሎ ባለፈው ሳምንት የኬንያ ፖሊስ ኃላፊ ከስራ መልቀቃቸው ይታወሳል።
ጋዜጠኛው በመኪና ውስጥ ሲቪል በለበሱ ሁለት ሰዎች መካከል ተጨናንቀው እንዲቀመጡ መደረጉንም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “እጄን በካቴና ታስሬ ነበር። ጥቃትም ደርሶብኛል” ብለዋል። ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ለመዋል አሻፈረኝ ለምን እንደሚሉ እንደጠየቋቸውም ገልጸዋል።
“እስርን እንደማልቃወም ነገርኳቸው። ነገር ግን ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር ሊያውሉኝ ሲሉ እየተቃወምኩ” ነው ያሉት ጋዜጠኛው ግለሰቦቹ ማንነታቸውን የሚገልጽ ነገር እንዳላሳዩ አስረድተዋል።
መንገድ ላይ መኪናቸውን ካቆሙ በኋላም ከተወሰነ የስልክ ጥሪ በኋላ ወደ ካረን ፖሊስ ጣቢያ በመኪና መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ ፖሊስ በተሳሳተ ማንነት ነው የታሰሩት የሚለውን መግለጫ በመቃወም በእሳቸው እና በፍራንሲስ ጋይቶ መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ በመጥቀስ “የሚፈልጉት እኔን ነበር” ብለዋል።
“ከእሱ በዕድሜ በዕጥፍ እበልጣለሁ። እኔ መኖሪያ ቤት አይኖርም፣ የተከታተሉኝ ከመኖሪያ ቤቴ ነው። እንደኔ አይነት መኪና አይነዳም” ብለዋል።
የተሞከረው “አፈና” ከጋዜጠኛ ስራቸው ጋር በተገናኘ እንደሆነም ገልጸዋል።
ፖሊስ በበኩሉ የተፈጠረው ክስተት “የሚያጸጽት መሆኑን” ገልጾ “ጋዜጠኞችን በምንም መንገድ ኢላማ አናደርግም” ብሏል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ በኬንያ ትልቁ ዴይሊ ኔሽን የረዥም ጊዜ አምደኛ ሲሆኑ መንግሥትን በሰላ የሚተቹ ጽሁፎቻቸው ይታወቃሉ።
ፖሊስ ያሳሳተው እና በተጠርጣሪነት እየፈለገው ያለው ፍራንሲስ ጋይቶ የተባለው የማህበራዊ ተጽእኖ ፈጣሪ እጁን እንደሚሰጥ ተናግሯል።
ግለሰቡ በቅርቡ አካላቸው ተቆራርጦ በቆሻሻ መጣያ ስፍራ የተገኙትን ዘጠኝ ሴቶችን ገድሏል በሚል የአንድ ግለሰብን ስም እና ማንነት ዝርዝር ለጥፏል ሲል ከሶታል። በሁኔታው የተደናገጠው ግለሰብ ለፖሊስ እንደከሰሰም ገልጸዋል። እነዚህን ግድያዎች በመፈጸም ጁማይሲ ካሉሻ የተባለ ግለሰብ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ቢያውልም ግለሰቡ ግድያዎቹን ፈጽሜያለሁ ብሎ እንዲናዘዝ እንደተሰቃየ ገልጿል።