የካናዳ የሕዝብ እንደራሴዎች ለደኅንነታቸው ስለሰጉ የፖሊስ መጥሪያ ቁልፍ ተሰጣቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የካናዳ የሕዝብ እንደራሴዎች ፖሊስ በአፋጣኝ እንዲጠሩ የሚያስችላቸው የድንገተኛ ጊዜ ቁልፍ ተሰጣቸው።
የሕዝብ እንደራሴዎች ከፍተኛ ማስፈራራት፣ ማንጓጠጥ እንዲሁም ዛቻ እየደረሰባቸው ስለሆነ ነው ቁልፉ (panic button) ያስፈለጋቸው።
የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትሩ ማርኮ ሜንዲቺኖ እንዳሉት፣ እሳቸውም የግድያ ዛቻ ደርሷቸዋል።
“በበይነ መረብ የምናየው የጥላቻ ትርክት እጅግ አስጊ ነው” ብለዋል።
የካናዳ የሕዝብ እንደራሴዎች በየመንገዱ ዛቻ ይደርስባቸዋል።
አምና ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ላይ ድንጋይ እንደተወረወረባቸውም ይታወሳል።
የደኅንነት ሚኒስትሩ ባለፈው ወር የመሣሪያ ቁጥጥርን የሚያጠብቅ ሕግ ካስተዋወቁ በኋላ ነበር ማስፈራሪያ የደረሳቸው።
ስለዚህም ፖለቲከኞች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ሲባል ፖሊስ በፍጥነት እንዲጠሩ አሠራር ተዘርግቷል።
የሕዝብ እንደራሴዎች ቤታቸው ውስጥ የደኅንነት ካሜራ እንዲገጥሙ ይደረጋል። ጥቃት ቢሰነዘርባቸው እንዴት ራሳቸውን መከላከል እንደሚችሉም ሥልጠና ይሰጣቸዋል።
“ሰዎች ለግብግብ ሳይጋበዙ ወይም እንገድላችኋለን ብለው ሳይዝቱብን በማንኛውም ጉዳይ ላይ ምክክር ማድረግ መቻል አለብን” ብለዋል የደኅንነት ሚኒስትሩ።
በፌደራል ደረጃ ጥበቃ የሚሰጠው የካናዳ ፖሊስ ለፖለቲከኞች ተገቢውን ጥበቃ አላደረገም ተብሎ ከዚህ ቀደም ሲወቀስ ነበር።
የግራ ዘመሙ ኒው ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ጃግሜት ሲንግ ባለፈው ወር በኦንትርዮ ጥቃት እንደደረሰባቸው ይታወሳል።
ፖለቲከኛውን “ከሀዲ” ብለው ሲጠሩ የነበሩ ተቃዋሚዎች “ብትሞት ይሻላል” እያሉም ሲዝቱባቸው ነበር።
“በጣም የሚያስጨንቅ እና የሚያዋርድ ክስተት ነበር” ብለዋል ፖለቲከኛው።
ሌላዋ የፓርቲያቸው አባል ሄዘር መክፈርሰን፣ ለቤተሰቦቿ ደኅንነት እንደምትሰጋ ተናግራለች።
ከዚህ ቀደም ውሻዋን ‘እንገድለዋለን’ የሚል ማስፈራሪያም ደርሷታል።
ከወራት በፊት ኦቶዋ ውስጥ የኮቪድ ክትባትን የሚቃወም ሰልፍ ከተካሄደ በኋላ የሕዝብ እንደራሴዎች የሚደርስባቸው ዛቻ ጨምሯል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪና ሹፌሮች መንገድ ዘግተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እና ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ ወደ ሚስጥራዊ ቦታ ተወስደዋል።
የሕዝብ እንደራሴዋ ጁዲ ሰግሮ፣ አንድ ግለሰብ ወደ ቤቷ ስትሄድ ከተከተላት በኋላ የድንገተኛ ጊዜ ቁልፍ ያስፈልጋል ብላ እንዳሰበች ተናግራለች።
“ሴቶች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። ብዙ የተቆጡ እና ጋጠ ወጥ ሰዎች አሉ። ከባድ ጊዜ ላይ ነን” ብላለች።
ከሁለት ዓመት በፊት አንድ ግለሰብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደሚኖሩበት ቅጥር ጊቢ መሣሪያ ታጥቀው፣ የጭነት መኪና መንዳታቸው አይዘነጋም።
ግለሰቡ በቁጥጥር ሥል ውሏል።












