አባት ከስድስት ልጆቻቸው ጋር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቅያ ፈተናን እንዴት ሊወስዱ ቻሉ?

የፎቶው ባለመብት, Oromiya Education Bureau
ነዋሪነታቸው በምስራቅ ቦረና ዞን በምትገኘው ምዕራብ ወላቡ ወረዳ የሆኑት ሼክ አብዱራዛቅ ሀጂ ከድር ከስድስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው ጋር የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ ፈተናን በጋራ ወስደዋል።
ሼህ አብዱራዛቅ ከስድስት ልጆቻቸው ጋር በመደ ወላቡ ዩኒቨርስቲ የ12ኛ መልቀቅያ ፈተና መውሰዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
43 ዓመት አንደሆናቸው የሚናገሩት ሼህ አብዱራዛቅ ከሁለት ሚስቶች 18 ልጆች ወልደዋል።
“ከመጀመርያ ሚስቴ 11፣ ከሁለተኛዋ ደግሞ ሰባት ልጆች አሉኝ” ይላሉ።
ሼህ አብዱራዛቅ 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቁት በ1999 ዓ.ም ነው።
ይኹን እንጂ ኪሳቸው ሲሳሳ፣ ለልጆቻቸው የሚያጎርሱት እያጠረ ሲመጣ አቋርጠው ተጨማሪ ገቢ ወደ መፈለግ ገቡ።
ሼህ አብዱራዛቅ ትምህርታቸውን ከ10ኛ ክፍል ያቋረጡት ልጆቻቸውን ለማስተማር ብለው መሆኑን ከቢበቢሲ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ገልጸዋል።
“እየሰራሁ ልጆቼን አስተምር ነበር። ብዙ ሀብት ስላልነበረኝ መማር ያቆምኩት ልጆቼን ለማስተማር ብዬ ነው። . . . የተለያዩ ነገሮችን እሰራለሁ። እነግዳለሁ። አርሳለሁ። ሌሎች ሌሎችንም እየሰራሁ ነው ልጆቼን ሳስተምር የነበረው።”
ሼህ አብዱራዛቅ 15 ልጆቻቸውን ያስተማሩ ሲሆን፣ ሦስት ልጆቻቸው እድሜያቸው ለትምህርት ባለመድረሱ ወደ ትምህርት ቤት አልሄዱም።
ከ13 ዓመት በኋላ፣ በ2012 ዓ.ም 11ኛ ክፍል ገብተው መማር የጀመሩት ሼህ አብዱራዛቅ፣ በ2013 ትምህርታቸውን ጨርሰው የመልቀቅያ ፈተና ቢወስዱም ነጥብ አልመጣላቸውም።
በዚህም ምክንያት ባለፈው ዓመት በ2014 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ከጨረሱ ሁለት ልጆቻቸው ጋር ለፈተና ተቀምጠው ነበር።
ነገር ግን እርሳቸውም ሆኑ ሁለቱ ልጆቻቸውም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባት የሚያስችላቸውን ነጥብ ማግኘት አልቻሉም።
በዚህም ምክንያት በ2015 ዓ.ም ከፍለው በግላቸው ለፈተና ተቀመጡ።
በ2015 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ሲማሩ የነበሩ ሌሎች አራት ልጆቻቸው በመደበኛ ተማሪነት፣ አባት እና ሁለት ልጆች ደግሞ በግል ተፈታኝነት ለብሔራዊ ፈተናው ስለተቀመጡ ለፈተና የተቀመጡት የአንድ ቤተሰብ አባላት ቁጥር ሰባት ደረሰ።
በዚህ ዓመት ለፈተና ከተቀመጡት የሼህ አብዱራዛቅ ልጆች መካከል የመጀመርያ ልጃቸው 22 ዓመቷ ሲሆን የእርሷ ተከታይ ደግሞ 19 ዓመቱ መሆኑን ይናገራሉ።
‘የታሪክ እና የቋንቋ መምህር መሆን እፈልጋለሁ’
የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ የሆኑት ሼህ አብዱራዛቅ፣ ከአራት ልጆቻቸው ጋር በመደወላቡ ዩኒቨርስቲ የመልቀቅያ ፈተናውን ተፈትነው ወደ ቤታቸው ገብተዋል።
የተቀሩት ሁለት ልጆቻቸው ደግሞ በአሁኑ ሰዓት የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተናውን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ለፈተናው እንዴት ይዘጋጁ አንደነበር ተጠይቀው “እኔ እንኳን እነርሱን ለማሳደግ ላይ ታች ስል ነበር። እነርሱ ግን ፕሮግራም አዘጋጅተው ሲያጠኑ ነበር። ሆኖም አንዳንድ ምሽቶች ፕሮግራም አውጥተን አብረን ስናጠና ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ፈተናውን አስመልክቶም “ፈተናው ደስ ይላል። የቦታ ቅያሬው ለሰው አዲስ ከመሆኑ ውጪ ፈተናው አይከብድም። ላነበበ ሰው በጣም ቆንጆ ነው።” ብለዋል
መንግሥት የፈተና ኩረጃን ለመቀነስ በሚል ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የብሔራዊ መልቀቅያ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ አድርጓል።
የ43 ዓመት ጎልማሳ በመልቀቅያ ፈተናው ጥሩ ውጤት ካመጡ የታሪክ እና የኦሮምኛ ቋንቋ መምህር መሆን እንደሚፈልጉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይኹን እንጂ በሚገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ ለልጆቻቸው ቅድሚያ እንደሚሰጡ ይናገራሉ።
“ፈጣሪ አሳክቶልኝ ዩኒቨርስቲ የምገባ ከሆነ ለእኔ ሳይሆን ልጆቼ የሚፈልጉትን ለምኜም ቢሆን አንዲያገኙ አደርጋለሁ። ልጆቼ ዩኒቨርስቲ ከገቡ ያለኝን ሁሉ ጨርሼ አስተምራቸዋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።












