አማካይ የዕድሜ ጣሪያ መቀነሱን የተባበሩት መንግሥታት ጥናት አመለከተ  

ታትሟል

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ አማካይ የዕድሜ ጣሪያ፣ የትምህርት እና የምጣኔ ሐብት እድገት መቀነሱን የተባበሩት መንግሥታት ጥናት አመለከተ።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በየዓመቱ ይፋ በሚያደርገው 'ሂዩማን ዲቨሎፕመንት ኢንዴክስ' ሪፖርት እንዳመለከተው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአስር አገራት ዘጠኙ ከነበሩበት ወደ ኋላ ተመልሰዋል።

ለዚህ የዓለም እድገት ወደ ኋላ መቀልበስ  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የዩክሬን ጦርነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ያሳደረውን ተጽዕኖን በምክንያትነት ጠቅሷል።

ሂዩማን ዲቨሎፕመንት ኢንዴክስ የተዋወቀው እንደ አውሮፓውያኑ በ1990 ሲሆን ዓላማውም ደኅንነትን ለመለካት የአገር ውስጥ ምርት ዕድገትን (ጂዲፒን) ከመጠቀም ባሻገር ለመመልከት ነው።

በዚህ ዓመት ባወጣው ሪፖርቱ ላይ የስዊዘርላንድ አማካይ የዕድሜ ጣሪያ 84 ዓመት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በጥናቱ ከተካተቱ አገራት በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ከዚህ ውስጥም ዜጎቿ በአማካይ 16.5 በመቶ የሚሆነውን ዕድሜ ያሳለፉት በትምህርት ሲሆን አማካይ የደመወዝ መጠናቸውም በዓመት 66 ሺህ ዶላር ነው።

በሌላው በኩል ደግሞ በደቡብ ሱዳን አማካይ የዕድሜ ጣሪያ 55 መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።

ዜጎቿም ከዚህ ውስጥ በትምህርት ያሳለፉት 5.5 በመቶ የሆነውን ዕድሜያቸውን ብቻ ሲሆን የሚያገኙት አማካይ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸውም 768 ዶላር ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህ ጥናት ከተካተቱ 191 አገራት አብዛኞቹ በተለይም በአማካይ የዕድሜ ጣሪያ ጥናት ላይ በ2016 ወደነበሩበት ተመልሰዋል።

በአሜሪካ በውልደት ወቅት ያለው የዕድሜ ጣሪያ ከአውሮፓዊያኑ 2019 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል አሽቆልቁሏል።

ጥናቱ ከተጀመረ ጀምሮ በነበሩት ባለፉት ዓመታትም አብዛኞቹ አገራት ቀውስ ያጋጠማቸው መሆኑን ያመላከተው ሪፖርቱ፤ አገራቱ ወደኋላ መመለሳቸውን ገልጿል።

የዕድሜ ጣሪያ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነሱን ያመላከተው ጥናቱ፣ የዚህ ዓመቱ ውጤት እያሽቆለቆለ መሆኑ በተጨባጭ የታየበት ነው ብሏል።

በዚህ ዓመት ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ሃብታም አገራት ባለፈው ዓመት ወደነበሩበት የተመለሱ ሲሆን የሌሎቹ ግን አሁንም ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል።

 የዚህ ዓመት ጥናት የተሰራው ከባለፈው ዓመት በተወሰደ መረጃ መሆኑን የጠቀሱት ከአጥኝዎቹ አንዱ የሆኑት አቺም ስቴነር፣ ከ80 በላይ አገራት ብሔራዊ ብድራቸውን በመክፈል ችግር ላይ ናቸው ብለዋል።

“ ከእንደዚህ ዓይነት ቀውስ አንድ እርምጃ የራቁት ስምንት አገራት ብቻ መሆናቸውም ችግሩ ከባድ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል አቺም ስቴነር።