‘ዘ ዊኬንድ’ መጠሪያውን ወደ ትውልድ ስሙ አቤል ተስፋዬ ቀየረ

አቤል ተስፋዬ
ታትሟል

ካናዳዊው አቀንቃኝ ዘ ዊኬንድ ከዚህ በኋላ መጠሪያው የትውልድ ስሙ አቤል ተስፋዬ እንደሆነ ገልጿል።

ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች የተወለደው ድምጻዊው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ ስሙን ወደ አቤል ተስፋዬ ለውጧል።

ዝነኛው ድምጻዊ ስሙን መቀየር ያስፈልገው እንደሆነ ባለፈው ወር በትዊተር ገጹ ላይ ለአድናቂዎቹ ጥያቄ አቅርቧል።

“ዘ ዊኬንድ በመባል የሚጠራው አቤል?” ብሎ የጻፈው ትዊት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ወደውታል።

ድምጻዊው ከደብሊው መጽሔት ጋር ባደረገው ቆይታ “ዘ ዊኬንድን ማጥፋት” እንደሚፈልግ ገልጾ ነበር።

ይህንን ስም ወደኋላ ትቶ ወደ ትውልድ መጠሪያ ስሙ መመለሱን የገለጸውም ከዚህ በኋላ ነው።

“በስሜታዊ ለውጥ ውስጥ ነው ያለሁት። የዘ ዊኬንድ ምዕራፍ እያከተመ ነው” ብሏል አቀንቃኙ።

ከዚህ ቀደም ‘ዘ ዊኬንድ’ በሚል የመድረክ ስም ለመጠራት የወሰነው ትምህር አቋርጦ ወጥቶ ለአንድ የሳምንት መጨረሻ ከቤት ከወጣ በኋላ እንደሆነ ዘ ዴይሊ ሜል ዘግቧል።

“ለአንድ የሳምንት መጨረሻ ቤት አለመመለስ” ሲል ነበር የገለጸው።

አሁን ደግሞ ከደብሊው መጽሄት ጋር ባደረገው ቆይታ “ዘ ዊኬንድ በሚለው ስም ማለት የምችለውን ሁሉ ብያለሁ። ቀጣዩ አልበሜ በዚህ ስም የምሠራው የመጨረሻ አልበም ይሆናል” ብሏል።

በቶሮንቶ ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች የተወለደው አቤል ተስፋዬ፣ እአአ በ2010 የመጀመሪያ ዘፈኑን ዩቲዩብ ላይ ከለቀቀ በኋላ ዝናው ናኝቷል።

በአር ኤንድ ቢ ስልት ስለ ጨለምተኛ ቀናት፣ ዕፅ ስለመጠቀም፣ ስለ መገለል እና ወሲብ ላይ የሚያጠነጥኑ ሙዚቃዎች ናቸው።

ካናዳዊው ራፐር ድሬክ ሙዚቃዎቹን በገጹ ላይ አጋርቶ አቤል ዘጠኝ ዘፈን ያለው ሚክስቴፕ እንዲሠራ አድርጓል።

ይህ ‘ሀውስ ኦፍ ባሉንስ’ የተባለው አልበም በነጻ በበይነ መረብ የሚጫን ሆኖ ነው የተለቀቀው።

አራት ጊዜ ግራሚ ከማሸነፉ በተጨማሪ 45 ፕላቲንየም የደረሱ ነጠላ ዜማዎች ለቋል። አልበሞቹ በርካታ ሪከርዶችን በመስበር ይታወቃሉ።

በ2023 ዓለም አቀፉ የድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጊነስ) በዓለም እጅግ ታዋቂው ድምጻዊ ብሎታል። ይህ ስያሜ የተሰጠው ስፖቲፋይ ላይ ባሉት አድማጮች ብዛት ነው።

እስከ መጋቢት 2023 ድረስ ስፖቲፋይ ላይ 111.4 ወርሃዊ አድማጮች አሉት።

በስፖቲፋይ 100 ሚሊዮን ወርሃዊ አድማጮች በማግኘት የመጀመሪያው ድምጻዊ ነው።

በሁለተኛነት የምትከተለው ማይሊ ሳይረስ ስትሆን 82.4 ወርሃዊ አድማጮች አሏት።

ድምጻዊው ከቀናት በፊት እናቱን እና የቤተሰቡን ትውልድ አገር ለማክበር በሚል የኢትዮጵያ ቡና ሽያጭ እንደሚጀምር ማስታወቁ ይታወሳል።

በእናቱ ስም ሳምራ ሲል የሰየመውን ቡና፣ ከብሉ ቦትል ኮፊ ጋር በመተባባር ለሽያጭ ማቅረቡን በትዊተር ገፁ ላይ ይፋ አድርጓል።

አቤል ተስፋዬ ከሪከርድ ኩባንያው በጋራ በመሆን “ብሉ ቦትል ኮፊ” በሚል ስም ባቋቋሙት ድርጅት ሥር የኢትዮጵያን ባህል እና የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ደረጃ ለመሸጥ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በድረ ገፁ ጽፏል።

“የኢትዮጵያ ባህል ወሳኙ የማንነቴ አካል ነው” ሲል የተናገረው አቤል፣ የኢትዮጵያ ባህል፣ እሴቶች እና ቡና ላይ የዓለም ዐይኖች እንዲያርፉ ለማድረግ ከብሉ ቦትል ኮፊ ጋር በመተባባር እየሠራ መሆኑን ጠቅሷል።