አሜሪካዊቷ ታዳጊ በቲክቶክ ቪዲዮዎች ምክንያት በፓኪስታን በአባቷ በጥይት ተገደለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በቅርቡ ቤተሰቡን ከአሜሪካ ወደ ትውልድ ስፍራው ፓኪስታን የወሰደው አባት ታዳጊ ልጁ በቲክቶክ ላይ በምትለጥፋቸው ቪዲዮዎች ምክንያት በጥይት መግደሉን ማመኑን ፖሊስ ለቢቢሲ ገለጸ።

አንዋር ኡል ሃቅ የተባለው ግለሰብ ልጁን ሂራን መግደሉን ማመኑን ተከትሎ በደቡባዊ ምዕራብ ኩየታ ከተማ በግድያ ወንጀል ተከሷል።

መጀመሪያ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ልጁን ተኩሰው እንደገደሏት ለመርማሪዎች ተናግሮ ነበር።

የአሜሪካ ዜግነት ያለው ይህ አባት ታዳጊ ልጁ በቲክቶክ የምትለጥፋቸው ቪዲዮዎች "አጸያፊ" ሆኖ እንዳገኛቸው ገልጿል።

ፖሊስ በሃገሪቱ ውስጥ ዘንድ የተለመደ በሆነው "የክብር ግድያ"ን ጨምሮ የተገደለችበትን ሁኔታ እየመረመርኩ ነው ብሏል።

በፓኪስታን ውስጥ በማህበረሰቡ ዘንድ "አስነዋሪና ክብርን የሚያዋርድ" ስራ ሰርተዋል የሚባሉ ታዳጊዎች እና ሴቶች በዚህ"የክብር ግድያ" ተብሎ በሚጠራው መንገድ በአብዛኛው በቤተሰብ አባላት ይገደላሉ።

በፓኪስታን ውስጥ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ሴቶች "በክብር ግድያ" ህይወታቸው እንደሚቀጠፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ይናገራሉ።

እነዚህ ግድያዎች ብዙውን ጊዜ የሚፈጸሙት የቤተሰብ ክብር እናስጠብቃለን በሚሉ የቤተሰብ አባላት ነው።

13 ወይም 14 ዕድሜ ያላት ታዳጊዋ ሂራን "አለባበሷ፣ አናናሯ እንዲሁም ጓደኞቿ " ላይ ቤተሰቦቿ የጸና ተቃውሞ እንደነበራቸው የፖሊስ ቃል አቀባይ አስታውቋል።

ቤተሰቡ በአሜሪካ ለ25 ዓመታት የኖረ ሲሆን ሂራ ወደ ፓኪስታን ከመምጣቷም በፊት በቲክቶክ ላይ የተለያዩ ይዘቶች ያላቸውን ቪዲዮዎች ትለጥፍ ነበር።

መርማሪዎች የታዳጊዋን ስልክ በቁጥጥራቸው ስር እንደሆነ እና እንደተቆለፈም ተናግረዋል።

የአባትየው የባለቤት ወንድም ከታዳጊዋ ግድያ ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

ጉዳዩ የክብር ግድያ ሆኖ ከተገኘ እና ግለሰቦቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በአውሮፓውያኑ 2016 በተደረገው የፓኪስታን ህግ ማሻሻያ መሰረት የዕድሜ ልክ እስራት ይጠብቃቸዋል።

ከዚህ ቀደም የተጎጂ ቤተሰቦች ይቅርታ ካደረጉ ገዳዮቹ ላይታሰሩ የሚችልበት አሰራር ነበር። ከሁለት ዓመት ዓመታት በፊት ወላጆቿ አግቢ ያሏትን ግለሰብ አሻፈረኝ ያለች የ18 ዓመት ልጃቸውን የገደሉ ጥንዶች ላይ የጣሊያን ፍርድ ቤት የዕድሜ ልክ እስራት ፈርዶ ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት በፖኪስታን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈችውን ካንዲል ባሎችን የገደላት ወንድሟ በይግባኝ ነጻ ወጥቷል።

ቀደም ሲል በአውሮፓውያኑ 2016 በቤተሰቡ ወርደት አስከትላለች ያላትን እህቱን መግደሉን በመናዘዙ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ነበር።