ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬናውያንን 'ደም መፍሰስ' ለማስቆም ለፑቲን እንደሚደውሉ ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ሰኞ ዕለት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ እንደሚነጋገሩ ገልጸው፤ እርምጃው "የሚፈስሰውን ደም" ለማስቆም ያለመ ነው ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ ከፑቲን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን እና አንዳንድ የኔቶ አገራት መሪዎችን እንደሚያነጋግሩ አስታውቀዋል።

ምንም እንኳን የእስረኞች ልውውጥ ላይ ከስምምነት ቢደረስም ሩሲያ እና ዩክሬን ከሦስት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ንግግራቸውን አርብ ዕለት በኢስታንቡል አካሂደው ያለውጤት ተበትኗል።

ፑቲን ኢስታምቡል ከተገኙ በቱርክ በሚደረገው ውይይት ላይ እንደሚሳተፉ ትራምፕ ቢገልጹም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ግን ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆኑም።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ጦርነቱን ለማስቆም ዕድል ሊኖር የሚችለው እርሳቸው እና ፑቲን ፊት ለፊት ሲነጋገሩ ብቻ ነው ሲሉ ከጠቆሙ በኋላ ነው።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሰኞ ዕለት በፑቲን እና በትራምፕ መካከል ለሚደረገው የስልክ ንግግር ዝግጅት መደረጉን ለሩሲያ የዜና ወኪሎች አረጋግጠዋል።

ሁለቱ መሪዎች ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ በስልክ ተነጋግረዋል።

ፔስኮቭ ለታስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "ውይይቱ በጥሩ መስመር ላይ ነው።"

ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "ውጤታማ ቀን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። የተኩስ አቁም ይኖራል። እናም ይህ በጭራሽ መከሰት ያልነበረበት በጣም ኃይለኛ ጦርነት ያቆማል።"

የአውሮፓ መሪዎች ሩሲያ ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንድትደርስ እየጠየቁ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ እና የሩስያ መሪዎች የተኩስ አቁም ስምምነትን እንዲሁም በመካከላቸው ሊኖር ስለሚችለው የመሪዎች ስብሰባ ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሞስኮ ትራምፕ በሚፈልጉት ፍጥነት ባትንቀሳቀስም የአሜሪካን የሽምግልና ጥረቶች በደስታ መቀበሏን ቅዳሜ ዕለት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና በሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ መካከል በነበረው የስልክ ውይይት አስታውቃለች።

በኢስታንቡል የተካሄደው ድርድር

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሩሲያ እአአ የካቲት 2022 ላይ ዩክሬንን መውረሯ ይታወሳል።

በኢስታንቡል የተደረገውን ውይይት ተከትሎ ዩክሬን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጥሪዋን በድጋሚ አቅርባለች።

እንደ አንድ የዩክሬን ባለስልጣን ገለጻ ክሬምሊን የተኩስ አቁም እንዲደረስ ኪየቭ ወታደሮቿን "ከግዛቷ ሰፊ ክፍል እንድታስወጣ ማስገደድን ጨምሮ" አዲስ እና ተቀባይነት የሌላቸውን ጥያቄዎችን አቅርባለች ብለዋል።

የሩሲያው የልዑካን ቡድን መሪ እና የፑቲን ረዳት የሆኑት ቭላድሚር ሜዲንስኪ በንግግሮቹ ደስተኛ መሆናቸውን እና ግንኙነታቸውን ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሰዓታት በኋላ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን በሱሚ ግዛት የመንገደኞች አውቶቡስን በመምታት ዘጠኝ ሰዎችን ገድለዋል። ይህንን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በሞስኮ ላይ ጥብቅ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።

የአውቶብሱን ጥቃት "በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ግድያ ነው" ብለዋል።

ሩሲያ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባትሰጥም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሱሚ ግዛት "ወታደራዊ ይዞታዎች" መመታታቸውን ዘግበዋል።