ፑቲን በጦርነቱ የሚሳተፉ ወታደሮች እናቶች የሚሰማቸውን ህመም እንደሚጋሩ ተናገሩ

ቭላድሚር ፑቲን ከእናቶች ጋር ውይይት ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቭላድሚር ፑቲን ከእናቶች ጋር ውይይት ሲያደርጉ
ታትሟል

በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት እየተዋጉ ያሉ እና የተገደሉ ወታደሮች እናቶችን ያነጋገሩት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ህመማችሁ እንጋራለን” አሉ።

በመንግሥት ቁጥጥር ስር በሚገኝ መገናኛ ብዙኃን በተላለፈው የመክፈቻ ንግግራቸው “ልጅን ማጣት በምንም አይተካም” ሲሉም ተደምጠዋል።

በስብሰባው ላይ የታደሙት አብዛኞቹ እናቶች ለሩሲያ መንግሥት ድጋፍ ያለው ንቅናቄ አባላት ሲሆኑ፣ የተመረጡት በጥንቃቄ ነው በሚል ትችት ይቀርባል።

ፑቲን በዩክሬን የፈጸሙትን ወረራ ተከትሎ በተከሰቱ ጫናዎች ምክንያት ከአገሬው የሚደርስባቸው ተቃውሞ እየጠነከረ ይገኛል።

በመላው አገሪቱ አሁን ግዳጅ ላይ ያሉ ወታደሮች እናቶች ልጆቻቸው በቂ ሥልጠና እና መሳሪያ እንዲሁም ለክረምቱ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን እና አልባሳት ሳይዙ ወደ ግምባሮች ተልከዋል በሚል ግልጽ ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ።

አንዳንዶች ደግሞ በቅርብ ጊዜያት ተከታታይ ሽንፈት የገጠመው የሩሲያ ጦር ወደ ከባድ ውጊያ ወታደሮችን በግድ ያሰማራል ሲሉ ይከሳሉ።

የአሜሪካ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ጄኔራል ማርክ ሚሊ በቅርቡ እንዳሉት ከሆነ፣ በዩክሬን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በሩሲያ በኩል 100 ሺህ በዩክሬን ወገንም 100 ሺህ ወታደሮች እንደተገደሉ ወይም እንደቆሰሉ አስታውቀዋል።

ባልተለመደ መልኩ የሩሲያ መንግሥት ባለውፈው መስከረም ተጠባባቂ ጦሩ ለማዝመት በተደረገው ጥረት ስህተት መፈጠሩን ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፑቲን ትላንት ከሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው መንግሥታዊ መኖሪያ ቤቶታቸው እናቶችን በትልቅ ጠረጴዛ ዙሪያ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በዚህም ወቅት ከ17 እናቶች ጋር ተመምጠው የታዩ ሲሆን፣ የተወሰኑት እናቶች የሐዘን ምልክት ተደርጎ በሚወሰደው ጥቁር ሻሽ ጭንቅላታቸውን ሽፍነዋል።

“በግሌም ይሁን አጠቃላይ የአገሪቱ አመራሮች ህመማችሁ ይሰማናል” ብለዋል ፕሬዝዳንት ፑቲን።

ፕሬዝዳንቱ ለአንዲት እናት ልጇ “ዓላማውን እንዳሳካ” እና “በከንቱ እንዳልሞተ” ነግረዋታል።

ፑቲን እናቶችን ገጽ ለገጽ የማውራቱን አስፈላጊነት ሲያስረዱ፣ ከጉዳዩ ባለቤቶች ስላለው ሁኔታ ማወቅ ስለፈለጉ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳቱ “ጀግና” ካሏቸው በውጊያ ላይ ካሉ የሩሲያ ወታደሮች ጋር በየጊዜው በቀጥታ እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።

እናቶች በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ የሚሰራጩ “የፈጠራ” እና “የሐሰት” መረጃዎችን እንዳይምኑም አሳስበዋል።

የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ እያደረገ ባለው ቁጥጥር ምክንያት በዩክሬን ያለውን ሁኔታ ማወቅ ከባድ ቢሆንም፣ ሰዎች ቪፒኤን የተባለውን እና የሩሲያ መንግሥት ሳንሱሩን ጥሶ የሚያልፍ ኔትዎርክ ወደ መጠቀም ፊታቸውን አዙረዋል።

ከስብሰባው በኋላ የፑቲን ጽህፈት ቤት ያሳራጨው መረጃ  አብዛኞቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች የሩሲያን መንግሥት የሚደግፍ ንቅናቄ አባል መሆናቸውን አመልክቷል።

ተሳታፊ እናቶቹ ከተለያዩ የሩሲያ ክፍሎች የመጡ ሲሆን፣ አንዲት እናት ደግሞ ሞስኮ በቅርቡ ከጠቀለለቻት በምሥራቃዊ የዩክሬን ግዛት ከሚገኝ እና ራሱን የሉሃንስክ ሕዝቦች ሪፐብሊክ ብሎ ከሚጠራው አስተዳደር የመጡ ናቸው።

ለሩሲያ ወታደሮች ሰብአዊ ድጋፍ የሚያሰባስብ እና በሩሲያ መንግሥት የሚደገፍ ድርጅት አባል የሆኑ እናቶችም በስብሰው ታድመዋል።

የተቃዋሚዎች መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ደግሞ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የምትሰራ እናትም የስብሰባው አካል ነበረች።