በምሥራቅ ወለጋ በፀጥታ ኃይሎች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ጊዳ አያና
ታትሟል

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ በተባለች ቀበሌ ባለፈው ሳምንት አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. በሃይማኖታዊ በዓል ላይ የነበሩ በርካታ ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች መገደላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ስለተፈጸመው ግድያ መረጃ እንደደረሰው ገልጾ ለመመርመር ባለሙያዎች መመደቡን ተናግሯል።

የኮሚሽኑ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ቢሮ ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ ስለጥቃቱ እና ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልጻው፣ አስፈላጊውን መረጃ ለማሰባሰብ እና ምርመራ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን የፀጥታ ኃላፊ ግን የተባለው አይነት ግድያ በአካባቢው አለመፈጸሙን በመግለጽ ክስተቱን አስተባብለዋል።

ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪዎች የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው የተባሉ የመንግሥት ኃይሎች በቀበሌዋ የመጋቢት አቦ በዓልን በማክበር ላይ በነበሩ 40 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን “ያለ ምክንያት” ገድለዋለዋል ሲሉ ከሰዋል።

ግድያው የጀመረው አርብ መጋቢት 6 ከሰዓት በኋላ የበዓል ድግስ ላይ ታድመው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንድ የ16 ዓመት ታዳጊ ነው የተባለን ልጅ የፀጥታ ኃይሎች ከቤት አስወጥተው በመግደላቸው እንደሆነ እማኞች ገልጸዋል።

የታዳጊውን ግድያ ተከትሎ “ለምን” ብሎ ከጠየቀው የአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር አለመግባባት እና ግርግር ተፈጥሮ የፀጥታ ኃይሎቹ ተኩስ መክፈታቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ ታዳሚ የነበሩ አንድ የሃይማኖት አባት “የተገደለው ተማሪ ነው፤ ተፈናቅሎ የተመለሰ ነው፤ አሁን በእግሩ ነው ከጎጃም የገባው፤ ‘ምን ተሰምቶበት ነው እንደዚህ አድርጋችሁ የምትገድሉት’ ብሎ እዚያ አካባቢ ያለ ማኅበረሰብ ሲጠይቃቸው…ነው ተኩስ የከፈቱት” ሲሉ ስለ ግድያው አጀማመር ተናግረዋል።

ይህኑ ሁኔታ ያረጋጡ ሌላ የዐይን እማኝ በተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ የመንግሥት ኃይሎች ተኩስ መጀመራቸውን ገልጸው፤ ሃይማኖታዊው ክብረ በዓሉ ላይ የነበረው ሰው ሕይወቱን ለማዳን በየአቅጣጫው እየሮጠ ነበር ብለዋል።

ጥቃቱን “ድንገተኛ ነበር” ያሉት አንድ ነዋሪ፤ በስፍራው እና መሳሪያ አስመዝግበው የያዙ ሰዎች “በመደናገር” ከመከላከያ ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ የመንግሥት ኃይል መሆናቸውን ሲረዱ ተኩስ አቁመዋል ሲሉ ተናግረዋል።

መሳሪያ የያዙ ሰዎችን ጨምሮ ተኩስ የከፈተው መከላከያ ሠራዊት መሆኑን ያወቁ የቀበሌዋ ነዋሪዎች ሮጠው ለማምለጥ መሞከራቸውንም ነዋሪው ገልጸዋል።

ተኩሱ ከተከፈተበት አካባቢ ሸሽተው ሕይታቸውን እንዳተረፉ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ ሁለት ወዳጆቻቸውን ጨምሮ ማምለጥ ያልቻሉ ሰዎች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“በሰዓቱ ግርግሩ ሲፈጠር እኔም እግሬ አውጭኝ ብዬ ከፈጣሪ ጋር በመሮጥ መቼም ሕይወቴ ተርፏል። መሮጥ ያልቻሉት አቅመ ደካማዎች እና ሴቶች ሞተዋል ይባላል” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ እና በአቅራቢያ ባለች አሊ ጎጥ በተለይም መጋቢት 6 እስከ 7 (አርብ እና ቅዳሜ) ደርሷል በተባለው ጥቃት የሟቾቹ ቁጥር “42 ደርሷል” ያሉት የሃይማኖት አባት የሆኑት የቀበሌው ነዋሪ፤ “አባረው የገደሉት ሰው” አስከሬኑ አሁንም በተለያዩ ስፍራዎች እየተገኘ ነው ብለዋል።

ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው “በየቀኑ በዚህ እና እዚያ ቦታ አስከሬን ተገኘ ነው የሚሉት። እስከ ማክሰኞ [መጋቢት 10] ድረስ እስከ 33 ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል። አሁን ደግሞ ጨምሯል እየተባለ ነው። ነዋሪዎች የጠፉ ሰዎችን አስከሬን ፈልገው እያገኙ ነው እያገኙ ነው፤ የጠፉም አሉ እየተባለ ነው” ብለዋል።

በዚህ ጥቃት በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሁለት ታናናሽ ወንድሞቻቸው እንደተገደሉባቸው ለቢቢሲ የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪ “ፀጉረ ልውጥ ሰው ታይቷል” በሚል “ጥቆማ” ጥቃቱ ስለመድረሱ ተናግረዋል።

ሁለቱም ወንድሞቻቸው ባለትዳር እና የልጆች አባት እንደሆኑ የተናገሩት ነዋሪው፤ ከዚያ በፊት እንደሚያደርጉት እህታቸው ቤት ሃይማኖታዊውን በዓል ለማክበር ሄደው መገደላቸውን ገልጸዋል።

ስለግድያቸውም በማግስቱ ቅዳሜ መጋቢት 07 መረዳታቸውን ተናግረው፤ አስከሬን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ግን “መከላከያ ሠራዊት ፈቃደኛ ባለመሆኑ” አለመሳካታቱን ተናግረዋል።

“የአገር ሽማግሌና የሃይማኖት አባት መጣ፤ ቦታው ላይ ከባድ መሳሪያ አጥምደዋል። እኛንም ‘አስከሬን አታነሱም፤ እናንተንም እንገድላችኋለን’ ብለው በማስፈራራት ነው ያባረሩን” በማለት ቀብር መፈጸምን እንኳ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

“እናት እና አባታችን ግድያውን ከሰሙ ቀን አንስቶ እስካሁን ራሳቸውን አያውቁም፤ ቤተሰቡ በጣም ተጎድቷል። አስከሬን ማንሳት እንኳ ባለመቻሉ ነው የተጎዳነው። . . .[ለወላጆቻችን] ስለአሟሟታቸው እና ስለሁኔታው እስካሁን አልነገርናቸውም። አስተባብረን እዚያው [ግድያው የተፈጸመበት ቦታ ላይ] እንደቀበርናቸው ነው የነገርናቸው” ብለዋል።

ቤተሰባቸው በሽሽት ምክንያት ሐዘን መቀመጥ እንዳልቻለም ተናግረዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎችን ቁጥር እንዲህ ነው ብለው መናገር እንደማይችሉ የጠቀሱ እኒሁ የሟቾች ቤተሰብ፤ “አርብ እንደዚያ ሆነ፤ በማግስቱ ደግሞ [መጋቢት] 7 በጣም በርካት ወታደር ገብቶ ነበር” በማለት በርካታ ሰዎች “ከቤታቸው እየወጡ ተረሸነዋል” ሲሉ ጥቃቱን ገልጸዋል።

“የታጠቀ ኃይል አለ” በሚል ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ ግድያ እና መሳሪያ መንጠቅ እንደተፈጸመም ነዋሪዎቹ ተናግረው፤ የሰላማዊ ሰዎችን ግድያ በተመለከተ መግለጫ ያወጣው እናት ፓርቲ “በአባሉ ላይ ባልታወቁ ሰዎች ግድያ የተፈጸመበት መከላከያ ሠራዊት አርሶ አደሮች ላይ የበቀል እርምጃ አድርሷል” ሲል ወንጅሏል።

ፓርቲው በጥቃቱ 16 ሰዎች ስለመገደላቸው በመግለጫው ላይ ያመለከተ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም የ10 ሰዎችን ማንነት በስም ጠቅሶ ዝርዝር አውጥቷል።

በመንግሥት ላይሎች ጥቃት የተገደሉት ሰዎች አርሶ አደሮች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ እና ፓርቲው ጠቅሰዋል።

ከሟቾቹ ውስጥ 15 የሚሆኑት ቀብር እንደተፈጸመ የተናገሩት የሃይማኖት አባት የሆኑት የአካባቢው ነዋሪ፤ በአራት አብያተ ክርስቲያናት ቀብሩ ስለመፈጠጸሙ ገልጸዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ መከላከያ ሠራዊት መሆናችሁን በምን እንዳወቁ በቢቢሲ የተጠየቁት ነዋሪዎች በአካባቢው የሰፈረ ኃይል እንዳለ ጠቁመው፤ በለበሱት የደንብ ልብስ፣ በታጠቁት መሳሪያ እና በተሽከርካሪያቸው መለየታቸውን ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ አንድ ሳምንት የሞላው ቢሆንም፣ በአካባቢው ያለው ውጥረት አሁንም አለመርገቡን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ “አሁንም ስጋት ላይ ነው፤ ከቤቱ ወጥቶ ጫካ ነው ያለው” ብለዋል።

“ዛሬ ይምጡ ነገ ይምጡ አናውቅም፤ ፈጣሪ ነው እንግዲህ የሚያውቀው። . . . ጫካ ውስጥ ከተቀመጥን [ካለፈው ሳምንት] ከአርብ ዕለት ጀምሮ ሳምንት ሊሞላን ነው” ሲሉ አንድ ነዋሪ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ተፈጸመ ስለተባለው ግድያ ቢቢሲ የጠየቃቸው የምሥራቅ ወለጋ ዞን የፀጥታ ኃላፊ ኮሎኔል ለሜሳ ደሬሳ፣ በአካባቢው ፀጥታ የሚያስከብር የመንግሥት ኃይል እንዳለ ተናግረው፤ “መከላከያ ሠራዊት ንጹሃን ላይ የሚተኩስ ሠራዊት አይደለም” ሲሉ ግድያውን አስተባብለዋል።

ኃላፊው “በመከላከያ ሠራዊት በዚህ ደረጃ የተፈጸመ ጥቃት የለም” በማለት ተፈጸመ የተባለውን ግድያ “ውሸት ነው” በማለት ከማጣጣል ውጪ በአካባቢው ስለተከሰተው እና አሁን ስላለው ሁኔታ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።