ኔታንያሁ የጦር ካቢኔያቸውን በተኑ

ታትሟል

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስድስት አባላት ያሉትን የጦር ካቢኔያቸውን በትነዋል። የተቃዋሚው መሪ ቤኒ ጋንትዝ እና አጋራቸው ጋዲ ኢዘንኮት ካቢኔውን መልቀቃቸውን ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ውሳኔ ተጠባቂ ነበር።

ቀደም ሲል የነበረው የደህንነት ካቢኔ እና ዋናው ካቢኔ ከሐማስ ጋር በጋዛ ስለሚካሄደው ጦርነት ውሳኔ እንደሚሰጥ የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ አስታውቋል።

ጋንትዝ ከስምንት ቀናት በፊት ለጦርነቱ በቂ ስትራቴጂ አልተዘጋጀም በማለት ውሳኔያቸውን ካሳወቁ ወዲህ፣ የቀኝ አክራሪ ሚኒስትሮች በእርሳቸው ቦታ ለመተካት ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ኔታንያሁ የጦር ካቢኔውን በመበተን ጥምር መንግስት አብረው ከመሰረቱ ፓርቲዎች እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቻቸው ጋር የሚመጣን ግፊት አስወግደዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ በበኩላቸው ውሳኔው የዕዝ ሰንሰለቱን አይነካም ብለዋል።

ጋንትዝ እና ኢዘንኮት ጦርነቱ በመስከረም ወር ተከጀመረ ቀናት በኋላ ከኔታንያሁ የቀኝ ክንፍ ጥምረት ጋር የብሔራዊ አንድነት መንግስትን ተቀላቅለዋል።

ሁለቱ የቀድሞ የአገሪቱ የጦር መሪዎች ከቀናት በፊት ሥራቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር "ወደ እውነተኛ ድል እንዳንቃረብ እንቅፋት ሆኖብናል" ብለዋል ጋንትዝ።

ቀኝ አክራሪው የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር በጦር ካቢኔው ውስጥ መካተት እንደሚፈልጉ በመጠየቅ ደብዳቤ ለኔታንያሁ እንደፃፉ ተናግረዋል ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን አዳዲስ አባላትን ከመቀበል ይልቅ ውሳኔ ሰጪውን አካል ለመበተን መወሰናቸውን እሑድ አመሻሽ ላይ ለሚኒስትሮች አሳውቀዋል።

"ኔታንያሁ’የጦር ካቢኔው... ቤኒ ጋንትዝ በጠየቀው መሰረት በጥምር ስምምነት ውስጥ ነበር። ጋንትዝ ለቅቆ ሲወጣ ተጨማሪው የመንግስት አካል አያስፈልግም’ ብለዋል” ሲሉ የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ ዴቪድ ሜንሰር በሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ።

"የደህንነት ካቢኔ ከዋናው ካቢኔ ጋር በመሆን ውሳኔዎችን የመወሰን ስልጣን ከመንግስት ተሰጥቶታል" ሲሉም አክለዋል።

የጦር ካቢኔው የተወያየው አንዳንድ ጉዳዮች ቤን-ጂቪር እና የቀኝ አክራሪው የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪችን ጨምሮ 14 አባላት ላሉት የደህንነት ካቢኔ ለውይይት እንደሚመራ የእስራኤል ሃሬትስ ጋዜጣ ዘግቧል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት፣ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሚኒስትር ሮን ዴርመር እና የአልትራ-ኦርቶዶክስ ሻስ ፓርቲ ሊቀመንበር አርዬህ ዴሪ ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው “በአነስተኛ የምክክር መድረክ” ከባድ የሆኑ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ዘግቧል።

ሦስቱ ግለሰቦች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከጋንትዝ እና ከኢዘንኮት ጋር በጦር ካቢኔው ውስጥ ነበሩ።

የአገሪቱ ጦር ዋና ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ በበኩላቸው እንዲህ አይነቱ እርምጃ በጦሩ እንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

"የካቢኔ አባላት እና አሠራሩ እየተቀየረ ነው። እኛ የስልጣን እርከን አለን። የዕዝ ሰንሰለትን እናውቃለን። በዕዝ ሰንሰለቱ መሰረት እየሠራን ነው። ይህ ነው ዲሞክራሲ" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

መስከረም 26 በደቡባዊ እስራኤል ሐማስ ባደረሰው ጥቃት አንድ ሺህ 200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎችን ደግሞ አግቶ መውሰዱን ተከትሎ የእስራኤል ጦር በጋዛ ዘመቻ ጀምሯል።

በጋዛ ከ37 ሺህ 340 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ሲል በሐማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በእስራኤል መንግስት ውስጥ ተጨማሪ የውጥረት ምልክቶች እየታዩ ነው።

ኔታንያሁ እና የቀኝ አክራሪ ሚኒስትሮቻቸው በራፋህ ከተማ አቅራቢያ የቀን ላይ የሚደረግ “ወታደራዊ እንቅስቃሴን በማቆም” ተጨማሪ እርዳታ እንዲገባ ጦሩ ያሳለፈውን ውሳኔ ተችተዋል።

መኪኖች በእስራኤል ቁጥጥር ስር ከሚገኘው ከረም ሻሎም ድንበር እርዳታ ጭነው ወደ ጋዛ እንዲጓዙ ለማስቻል የተወሰነ ነው። እስራኤል ባለፈው ወር በራፋህ ዘመቻ ከጀመረችበት ወዲህ በዚህ አቅጣጫ እርዳታ እየገባ አልነበረም።

ቤን-ጂቪር ፖሊሲውን ሞኝነት ነው ሲሉ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ኔታንያሁን ጠቅሰው “እኛ አገር ያለው ሰራዊት እንጂ ሰራዊት ያለው አገር አይደለም” ማለታቸውን ዘግበዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ በበኩሉ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እየደረሰ መሆኑን ለማረጋገጥ የፖለቲካ መሪዎችን ትዕዛዝ እየፈፀመ መሆኑን አስረድቷል።

እየተካሄደ ያለው ነገር የፈጠረውን ግራ መጋባት ተከትሎም ጦርነት ይቆማል ማለት አይደለም ሲል አክሏል።