የቻይና ሆስፒታሎች በኮሮናቫይረስ ህመምተኞች እየሞሉ እንደሆነ ተጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኮቪድ-19 አዲስ ማዕበል መቀስቀሱን ተከትሎ በቻይና የሚገኙ ሆስፒታሎች እየሞሉ ይመስላል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
የሃገሪቱ ባለስልጣናት የታካሚዎች ቁጥር “በአንፃራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ ነው” ቢሉም የፅኑ ህክምና ክፍሎች (አይሲዩ) ሥራ በዝቶባቸዋል ሲሉ ዶ/ር ማይክል ሪያን ተናግረዋል።
የቻይና መረጃዎች ረቡዕ ዕለት በኮቪድ የሞተ ሰው አለመኖሩን ቢገልጽም በሽታው በፈጠረው ጫና ዙሪያ ጥርጣሬዎች መነሳታቸው አልቀረም።
በቻይና የኮቪድ ማገርሸትን ተከትሎ ባለፉት ቀናት የቤጂንግ እና ሌሎች ከተሞች ሆስፒታሎች እየሞሉ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2020 ጀምሮ ቻይና ጥብቅ የጤና ገደቦችን የሚጥለውን የዜሮ የኮቪድ ፖሊሲ ተከትላለለች።
ጥብቅ ቁጥጥሮቹ ላይ ተቃውሞ በመነሳቱ ከሁለት ሳምንታት በፊት መንግሥት አብዛኛዎቹን እርምጃዎች አቋርጧል።
ከዚያ ወዲህ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አረጋውያን ላይ ሞት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ቁጥሩ እየጨመረ ቢመጣም፣ ይፋዊው መረጃ ማክሰኞ ዕለት አምስት ሰኞ ደግሞ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ያሳያል።
ይህም የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋዎች ኃላፊው ዶክተር ራያን ቻይና ስለ ቫይረሱ ወቅታዊ እና ጥልቀት ያለው መረጃ እንድትሰጥ አሳስበዋል።
“በቻይና አይሲዩ ውስጥ የሚገኙት ተብሎ የተዘገበው በአንጻራዊነት ዝቅተኛ ቢሆንም አይሲዩዎች እየሞሉ ነው” ብለዋል።
“በማህበረሰብ ጤና እና በማህበራዊ እርምጃዎች ብቻ ይህን በከፍተኛ ሁኔታ የሚተላለፍ ቫይረስ ሙሉ በሙሉ ለማቆም በጣም አዳጋች እንደሚሆን ለሳምንታት ስንናገር ቆይተናል” ሲሉ አክለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም በጄኔቫ ባደረጉት ሳምንታዊ መግለጫቸው “በቻይና እየተፈጠረ ያለው ሁኔታ በጣም ያሳስበናል” ብለዋል።
የበሽታውን ክብደት፣ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎችን እና የጽኑ ህክምና ላይ መረጃ ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዶክተር ራያን አክለውም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ “የመውጫው ስትራቴጂ ክትባት ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቻይና የራሷን ክትባቶች አዘጋጅታ ያመረተች ቢሆንም በተቀረው የአለም ክፍል ጥቅም ላይ ከዋሉት የኤምአርኤንኤ ክትባቶች አንጻር ከከባድ የኮቪድ በሽታ እና ሞት በመጠበቅ ረገድ ውጤታማ አይደሉም።
የጀርመን መንግሥት ረቡዕ ዕለት የመጀመሪያውን የባዮኤንቴክ ኮቪድ-19 ክትባቶችን ወደ ቻይና መላኩን አስታውቋል።
ከጀርመን የተላኩት ክትባቶች ወደ 20 ሺህ ለሚገመቱ በቻይና ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች በቅድሚያ ይሰጣሉ።
ለቻይና የተላከው የመጀመሪያው የውጭ ሀገር የኮቪድ-19 ክትባት ሲሆን ስለተላከበት ጊዜ እና መጠን ተጨማሪ መረጃ አልተሰጠም።
ባለፈው ወር የቤጂንግ ጉብኝት ያደረጉበት የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልስ ክትባቱ ለቻይና ዜጎችም በነጻ እንዲደርስ ግፊት አድርገዋል።












