ቻይና ድርቅን ለመቋቋም ሰው ሰራሽ ዝናብ ለማዝነብ ሙከራ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማዕከላዊ እና ደቡብ ምዕራብ ቻይና በከባድ ድርቅ እና እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ የሙቀት ማዕበል በመጠቃታቸው የቻይና ባለስልጣናት ሰው ሰራሽ የዝናብ ስርጭትን ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።
የእስያ ረጅሙ ወንዝ በመባል የሚታወቀው የያንግትዜ ወንዝ በዚሁ ድርቅ ምክንያት ከፍተኛ መቀነስ አጋጥሞታል። አንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በመደበኛነት ከሚያገኙት የዝናብመጠን ከግማሽ ያነሰ ማግኘታቸውም ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል።
የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች የያዟቸው የመጠባበበቂያ የውሃ ክምችቶች በግማሽ ያህል ቀንሰዋል ሲሉ ባለስልጣናቱ ይፋ አድርገዋል።
ሰዎች ከፍተኛ የሙቀት መጠኑን ለመቋቋም የአየር ማቀዝቀዣ ፍላጎታቸው በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ኩባንያዎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቷል።
ሁለት ወራት ያስቆጠረው የሙቀት ማዕበል በቻይና እስካሁን የተመዘገበ ረጅሙማዕበል ነው ሲል ብሄራዊ የአየር ንብረት ማዕከል አስታውቋል።
በድርቅ በተጠቃው ያንግትዜ ወንዝ ዙሪያ ያሉ ግዛቶች የዝናብ እጥረቱን ለመከላከል ደመናን ወደ ማዝነብ ጥረቶች ተዘዋውረዋል። ሁቤ እና ሌሎች በርካታ ግዛቶች ደግሞ ዝናብ ለማዝነብ የሚረዱ ኬሚካሎችን የጫኑ ሮኬቶችን ወደ ሰማይ ማስወንጨፋቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ነገር ግን ዝናቡን ለማዝነብ የሚረዳ የደመና ሽፋን እጦት በአንዳንድ አካባቢዎች ተመሳሳይ ዝናብ ለማዝነብ የሚደረጉ ጥረቶችን አዳጋች አድርጓቸዋል።
በተጨማሪም ሲቹዋን በተሰኘችው ግዛት እና አጎራባቾቿ ያለው የሙቀት መጠን ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሆኗል።
እንዲሁም የሃይል እጥረት መከሰቱን ተከትሎ የመብራት መቆራረጥ መኖሪያ ቤቶችን ብሎም ፋብሪካዎችን ጫና ውስጥ ከቷል።












