ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የክሪስቲያኖ ሮናልዶ ልጅ ለፖርቹጋል ከ15 ዓመት በታች ቡድን እንዲጫወት ጥሪ ቀረበለት
የክርስቲያን ሮናልዶ የመጀመሪያ ልጅ ለፖርቹጋል ከ15 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እንዲጫወት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሪ ቀርቦለታል።
የ14 ዓመቱ ክርስቲያን ሮናልዶ ጁኒየር እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ ለሳዑዲ ፕሮ ሊግ ለመጫወት ከፈረመው ከአባቱ ጋር በሳዑዲ አረቢያ አል ናስር ይገኛል።
የ40 ዓመቱ ፖርችጋላዊ ዝነኛ ሮናልዶ የልጁን ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ ስሙን የያዘ ፎቶ "ኮርቸብሃለሁ ልጄ" ከሚል ፅሁፍ ጋር በማኅበራዊ የትስስር ገፁ አጋርቷል።
ሮናልዶ ጁኒየር በሚቀጥለው ሳምንት በክሮሺያ ለሚጀመረው የወጣቶች ውድድር የተጠራ ሲሆን፤ በዚህ ውድድር ፖርቹጋል ከጃፓንን፣ ግሪክ እና እንግሊዝ ጋር ትጫወታለች።
የአምስት ጊዜ የባላንዶር አሸናፊ የሆነው ክርስቲያን ሮናዶ እስካሁን ድረስ ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን 136 ግቦችን በማስቆጠር በወንዶች እግር ኳስ ክብረ ወሰን ይዟል።
ሮናልዶ ጁኒየር አባቱ በተጫወተባቸው ክለቦች የታዳጊ ቡድኖች የተጫወተ ሲሆን፤ ሪል ማድሪድ፣ ጁቬንቱስ፣ ማንችስተር ዩናይትድ እና በአል ናስር አካዳሚዎች ተጫውቷል።
አንዳንድ ሪፖርቶች ሮናልዶ ጁኒየር በጁቬንቱስ በነበረው ቆይታ በአንድ የውድድር ዓመት ብቻ ለቡድኑ 58 ጎሎችን ማስቆጠሩን ይጠቁማሉ።
ሮናልዶ ዳግም ወደ ኦልድ ትራፎርድ ከተመለሰ በኋላ በማንችስተር ዩናይትድ ታዳጊዎች ቡድን ከዋይን ሩኒ ልጅ ካይ ጋር ተጫውቷል።
ሮናልዶ ጁኒየር ለአል ናስር ሲጫዎት የአባቱን ታዋቂ የሆነውን የደስታ አገላለፅን ሲደግም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ተለቅቆ በርካታ እይታ አግኝቷል።
ጂኒየር ምንም እንኳ ከቀናት በኋላ ለሚጀምረው ውድድር ከ15 ዓመት በታች የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ቢጠራም ለትውልድ አገሩ ዩናይትድ ስቴት እንዲሁም ከአባቱ ጋር ለኖረባት ስፔን መጫወትም ይችላል።