ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕንዳዊቷ ዶክተር በምትሰለጥንበት ሆስፒታል ተደፍራ መገደሏ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ
በሕንድ ኮልካታ ከተማ በአንድ መንግሥታዊ ሆስፒታል አንዲት ሰልጣኝ ዶክተር ተደፍራ መገዷሏን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የምዕራብ ቤንጋል ግዛት ነዋሪዎች ረቡዕ ነሐሴ 8/ 2016 ዓ.ም ምሽቱን በጎዳናዎች ላይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የ31 ዓመቷ ሰልጣኝ ዶክተር መንግሥታዊ በሆነው አርጄ ካር ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል ባለፈው ዓርብ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሏን ተከትሎ በመላው አገሪቷ የአደባባይ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ዶክተሯ እረፍት የለሽ የ36 ሰዓታት የፈረቃ ስራዋን ካጠናቀቀች በኋላ ለመኝታ የተዘጋጀ ስፍራ ባለመኖሩ ስልጠና በሚሰጥበት ክፍል መተኛቷ ተነግሯል።
በማግሥቱ ጥዋት ባልደረቦቿ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት የደረሰበት እና ግማሽ እርቃን የሆነውን ህይወት አልባ ገላዋን አግኝተውታል።
ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ አንድ የሆስፒታሉ በጎ ፈቃደኛ ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የቀረበውን የተቃውሞ ጥሪ ተከትሎ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሴቶች በኮልካታ ከተማ እንዲሁም በግዛቲቷ ዝናብ ሳይበግራቸው የአደባባይ ላይ ተቃውሟቸውን በትናንትናው ዕለት አሰምተዋል።
የተቃውሞ ሰልፎቹ በአብዛኛው ሰላማዊ ቢሆኑም ዶክተሯ በተገደለችበት ሆስፒታል ጥሰው በገቡ ሰልፈኞች እና በፖሊስ መካከል ግጭቶች መፈጠራቸው ተዘግቧል።
ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ የረጩ ሲሆን አንዳንድ የፖሊስ ተሽከርካሪዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
እንደ ደልሂ፣ ሃይደራባድ፣ ቦምቤይ እና ፑኔ ባሉ ሌሎች የሕንድ ከተሞች አነስተኛ ተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ባለስልጣናቱ ተደፍራ የተገደለችው ወጣት ላይ ቸልተኝነት አሳይተዋል በሚል ነው ከፍተኛ ቁጣ የተቀሰቀሰው።
ፖሊስ ወጣቷን ደፍሮ ገድሏል ያለው በጎ ፈቃደኛ በቁጥጥር ስር ቢያውልም ነገር ግን ወንጀሉን ለመሸፋፈን እንዲሁም ቸልተኝነት ታይቶበታል የሚሉ ክሶች ቀርበውበታል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ጉዳዩ ከአካባቢው ፖሊስ ወደ ፌደራል የምርመራ ቢሮ እንዲተላለፍ ተደርጓል።