ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ 'ፍሬንድስ' ተዋናዩ ማቲው ፔሪ ሞት ጋር በተያያዘ አምስት ሰዎች ተከሰሱ
ከተዋናይ ማቲው ፔሪ ሞት ጋር በተያያዘ አምስት ሰዎች ላይ ክስ ተመሠረተ።
የ ‘ፍሬንድስ’ ተዋናዩ ጥቅምት አጋማሽ 2016 ዓ.ም. ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕፅ ሳቢያ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል።
ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ከተከሰሱት መካከል የማቲው የግል ረዳት እና ሐኪሙ ይገኙበታል።
ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ከፍተኛ መጠን ያለው ኬቴሚን የተባለ መድኃኒት የሚዘዋወርበት “ሰፊ የወንጀል ትስስር” ማግኘቱን አስታውቋል።
ማቲው ከሞተ በኋላ በተደረገ ምርመራ በሰውነቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ኬቴሚን ተገኝቷል። ለሞቱ ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።
ዐቃቤ ሕግ ማርቲን ኤስትራዳ “ተከሳሾቹ የማቲውን ሱሰኝነት ገንዘብ ማግኛ አድርገው እራሳቸወን አበልጽገዋል። ሊጎዳው እንደሚችል ቢያውቁም ከድርጊታቸው አልተቆጠቡም” ብለዋል።
የማቲው የግል ረዳት ጨምሮ ሦስት ተከሳሾች ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል።
ቀሪዎቹ ተከሳሾች ሐኪም እና ‘የኬቴሚን ንግሥት’ በሚል ቅጽል ስም የምትታወቅ ሴት ናት።
ኬቴሚን ለድባቴ፣ ጭንቀትና ሕመም ለማስታገስ የሚውል ማደንዘዣ ነው። ከማቲው ጋር ‘ፍሬንድስ’ ላይ የተወኑ ጓደኞቹ እንደተናገሩት፣ ማቲው ይህን መድኃኒት በደም-ስሩ እየወሰደ ሕክምና ያደርግ ነበር።
ሕይወቱ ያለፈው ሕክምና ካገኘ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው። መድሃኒቱ በሰውነት ውስጥ የሚቆይበት ጊዜ አጭር ከመሆኑ አንጻር ማቲው ሕይወቱ ካላፈ በኋላ በሰውነቱ የተገኘው ኬቴሚን በሕክምናው ወቅት የወሰደው ሊሆን አይችልም ተብሏል።
በሕክምናው ወቅት የወሰደው መድኃኒት አንድ ሳምንት በሰውነቱ ሊቆይ እንደማይችልም ባለሙያዎች ገልጸዋል። በሰውነቱ ውስጥ የተገኘው የመድኃኒት መጠን ከቀዶ ሕክምና በፊት ሰውነትን ለማደንዘዝ የሚሰጥ መጠን ነው ብለዋል።
መርማሪዎች እንዳሉት፣ የዕፅ ዝውውር ሰንሰለቱ ለማቲው ሞት ምክንያት ሆኗል።
ኬነት ኢዋምሳ የተባለው የማቲው የግል ረዳት ከሁለት ሰዎች ጋር በመሆን ከማቲው ሞት ከአንድ ሳምንት በፊት ከ50 ሺህ ዶላር በላይ የወጣበት ኬቴሚን ለተዋናዩ ሰጥተዋል።
ተዋናዩ ሱሰኛ እንደሆነ እየታወቀ ሱሱን ለግል ጥቅማቸው ለማዋል መሞከራቸውን መሪማሪዎች ገልጸዋል።
ሳልቫዶር ፕላሰንካ የተባለው ተከሳሽ ሐኪም “ይሄ ቀሽም ምን ያህል እንደሚከፍል እስኪ እንየው” ሲል በተዋናዩ እየተሳለቀ የላከው የጽሑፍ መልዕክት በማስረጃነት ተጠቅሷል።
ይህ ሐኪም “ከተለመደው የሕክምና አካሄድ ውጭና ያለ ሕክምና ምክንያት” ከፍተኛ መጠን ያለው ኬቴሚን ለተዋናዩ አዟል።
ያለ ሐኪም እገዛ መድኃኒቱን እንዴት ለማቲው መስጠት እንደሚቻል ለግል ረዳቱ ማስተማሩንም መርማሪዎች ገልጸዋል።
ማቲው ከመሞቱ ከአራት ቀናት በፊት የግል ረዳቱ ቢያንስ 27 ጊዜ ኬቴሚን የያዘ መርፌ ወግቶታል።
ከአንድ ወር በፊት በዚህ መጠን የሰጠው ኬቴሚን ማቲው እንቅስቃሴ እንዲያቆም ስላደረገው፣ በዚያ መጠን እንዳይሰጠው ሐኪሙ ምክር ሰጥቶ ነበር።
ሆኖም ግን ሐኪሙ ከፍተኛ መጠን ያለው ኬቴሚን ከማዘዝ አልተቆጠበም።
ሌላዋ ተከሳሽ ‘የኬቴሚን ንግሥት’ በሚል የምትጠራው መድሃኒቱን የምታቀርብ ጃስቬን ሳንጋህ ናት።
ከሌሎች ሁለት ተከሳሾች ጋር በመሆን መድኃኒቱን እንዲያገኝ በመርዳት ተከሳለች።
ማቲው ከሞተ በኋላ ተከሳሾቹ ጥፋታቸውን ለመሸፈን መሞከራቸውን ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
‘የኬቴሚን ንግሥት’ በሚል የምትጠራው ሐኪም፣ ተከሳሾቹ ስልካቸው ላይ ያለ የጽሑፍ መልዕክቶችን እንዲያጠፉ ስትመክር ነበር።
የሕክምና ማስረጃውን ለማጭበርበርም ሞክራለች።
ማቲው መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ሞቶ መገኘቱ ይታወሳል። ተዋናዩ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒትና አልኮል ሱስ ለዓመታት ሲያሰቃየው ቆይቷል።
ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ በሱስ ምክንያት ‘ፍሬንድስ’ የተቀረፀበትን ሦስት ዓመታት መርሳቱን ተናግሮ ነበር።
እአአ ከ2001 በኋላ ግን ከሱስ ማገገሙን ተናግሮ ነበር።