ኢሬቻን ለማክበር ሽር ጉድ እያለች የምትገኘው ቢሾፍቱ

የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለማክበረ ሲወጣ እንደ ሳር ወይም አበባ ያሉ እርጥብ ነገሮችን በእጁ ይዞ ይወጣል።
ታትሟል

ኢሬቻ በየዓመቱ ከአዲስ አበባ አርባ ኪሎ ሜትር ያህል በስተምሥራቅ ርቃ በምትገኘው በቢሾፍቱ ከተማ ሆረ ሀርሰዴ በርካታ ሕዝብ ታድሞበት የሚከበር በዓል ነው።

ለበዓሉ ድምቀት ከሚሰጡት ክዋኔዎች መካከል ደግሞ ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ ከሚመጡት የኦሮሞ ተወላጆች በተጨማሪ የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም እንግዶች መገኘታቸው ነው።

በተለያየ ጊዜ እንደተስተዋለው ከሲዳማ፣ ከጋሞ፣ ከአላባ ወጣቶች በቢሾፍቱ በመገኘት በዓሉን ይታደማሉ።

በዓሉን ለመታደም በዚያ የሚገኙ ወጣቶች በባህል አልባሳት ደምቀው በቡድን በቡድን በመሆን ይጨፍራሉ።

ጭፈራው ቀንም ማታም ይቀጥላል።

በከተማዋ በባህል ልብስ የደመቁ ወጣቶች እየተዟዟሩ ፎቶ ይነሳሉ።

ቢሾፍቱ ለበዓሉ የምትደምቀው ታድያ በሰባት ሐይቆችና ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ፀጋዎቿ ቱሪስቶችን ብቻ ሳይሆን በእንግዶቿም ጭምር ነው።

ታድያ እነዚህ እንግዶች በዓሉን ለማክበር ወደ ስፍራው ሲንቀሳቀሱ ከመነሻቸው ጀምሮ እስከ መዳረሻቸው ወጪ ያወጣሉ።

በከተማዋ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ንግድ ቤቶችም እንግዶቻቸውን ባላቸው አቅም ሁሉ ለማስተናገድ ሽር ጉድ ይላሉ።

ኢሬቻ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠብቁት በዓል እንደሆነ በመጥቀስ “ብዙ እናተርፍበታለን” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት በከተማዋ የሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ አለማየሁ ባልቻ ናቸው።

በከተማዋ ከሚገኙ እንግዳ ማረፊያ እና መዝናኛዎች በተጨማሪ የባሕል አልባሳት የሚሸጡም በሺህ የሚቆጠሩ ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ ተፍ ተፍ እያሉ መሆኑን ቢቢሲ ተመልክቷል።

የከተማዋ አውራ ጎዳናዎች በባንዲራ እየተንቆጠቆጠ ነው።

ንግድ ቤቶች የባህል አልባሳትን በተለያየ ፋሽን አሰናድተው ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ ጀምረዋል።

አቶ አለማየሁ ባልቻ በበዓሉ ላይ የሚገኘው ሰው ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ፍቅሩ መተሳሰቡ ከፍ ያለ የደስታ ስሜት ይፈጥርባቸዋል።

“ኢሬቻ በየዓመቱ ስለሚከበር እኛም ቀደም ብለን ዝግጅት እንጀምራለን። ደንበኞቻችን ከዓመት ዓመት ይጨምራሉ። እኛም ማሻሻል ያለብንን ለይተን ተዘጋጅተን እንጠብቃለን። ሕዝባችንን ተቀብለን በጥሩ ሁኔታ አስተናግደን ለመሸኘት በዝግጅት ላይ ነን።”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቢሾፍቱ ከተማ በእንግዶቿ መሞላት የምትጀምረው ከበዓሉ ዋዜማው ጀምሮ ነው።

አቶ አለማየሁ እንደሚሉት በዚህ ጊዜ ሆቴላቸው በሰው እንደሚሞላ ሲያስረዱ “ቤቱ ውስጥ የጠጠር መጣያ ቦታ አንኳ አይገኝም” ይላሉ።

በኢሬቻ ቀን የሚዘፍነው፣ የሚጨፍረው፣ የሚጠጣው፣ የሚገባበዘው ሰው ስፍር ቁጥር የለውም።

እንግዶች ብቻ ሳይሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችም ሞልቶ በሚፈስ የደስታ ባሕር ውስጥ ይሆናሉ። ገበያ ይደራል፤ ፍቅር ይፈስሳል።  

አቶ አለማየሁ “የኢሬቻ ቀን እንግዶች በጣም የሚያስደስቱ እና እኛም ቀኑን በጉጉት እንድንጠብቅ የሚያደርጉ ናቸው” ይላሉ።

የኢሬቻ የበዓል ዋዜማ እና የዕለቱ ቀን ገበያ ዓመቱን ሙሉ ከሚኖረው ጋር አይወዳደርም።

ትርፍ በሽነው። ገንዘብ መምዘዝ፣ ማዘዝ፣ መጋበዝ የዕለቱ መርኅ ይመስላል።

ይህ ደግሞ እንደ አቶ አለማየሁ ላለ ነጋዴ እልል በቅምጤ ነው።

“በዓመት ካሉ ቀናት የኢሬቻ ቀን ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት ነው። ስለዚህ ለእኛ በገቢም ሆነ ባሕላችንን በማሳደግ ይህ ቀን ትልቅ ቦታ አለው።”

አቶ አሌክስ በዳሳ የፒራሚድ ሆቴል እና ሪዞርት ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

እርሳቸውም ለዚህ የኢሬቻ በዓል ከስር ከስር ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ወደ ቢሾፍቱ ከባሕር ማዶ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም ከየቤቱ ንቅል ብሎ የሚወጣው ነዋሪ የዕለቱ መገለጫ መሆኑን ያነሳሉ።

ታድያ በበዓሉ ሰበበብ ወደ ሆቴላቸው ጎራ ብለው የሚዝናኑትን ብቻ ሳይሆን ሐይቁ ዳር በነጻ ተዝናንተው እና ፎቶ ተነስተው መሄድ ለሚፈልጉም መሰናዶ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብሬ ዳቢ እንደሚሉት የቢሾፍቱ ከተማ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በሆራ ሀርሰዴ የኢሬቻን በዓል ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች ዝግጅቷን አጠናቃለች።

የሐይቁን አካባቢ እና የከተማዋ ውስጥ የማሳመር ሥራም እየተሰራ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ ከደኅንነት አካላት ጋር በመሆን ለኢሬቻ የሚመጡ ሰዎች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አስታውሰው “በዚህ በኩል ምንም ዓይነት ስጋት አይኖርም” ይላሉ።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ [ሆራ ፊንፊኔ] ቅዳሜ መስከረም 21/2015 ዓ.ም. በቢሾፍቱ [ሆራ ሀርሰዴ] ደግሞ እሁድ መስከረም 22/2015 ዓ.ም. እጅግ ብዙ ሕዝብ በሚገኝበት ይከበራል።