ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢንዶኔዥያ፡በእግርኳስ ሜዳ በተፈጠረ መረጋገጥ ከ174 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አለፈ
በኢንዶኔዥያ እግር ኳስ ጨዋታ ላይ በተፈጠረ መረጋገጥ ቢያንስ 174 ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት ገለጹ።
ከዓለማችን አስከፊው የስታዲየም አደጋዎች አንዱ ነው ተብሏል።
ፖሊሶች ነውጠኛ ደጋፊዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱን ተከትሎ መረጋገጡ አደጋው መከሰቱ ተሰምቷል።
በምስራቃዊ ጃቫ በተደረገው ጨዋታ አሬማ የተባለው ክለብ በፓርሴባያ ሱራባያ ከተሸነፈ በኋላ በተፈጠረው ክስተት 180 ያህል ሰዎች ቆስለዋል።
የሃገሪቱ የፀጥታ ጥበቃ ሚኒስትር እንደተናገሩት ስታዲየሙ መያዝ ከሚችለው በላይ 4000 ያህል ተመልካቾችን አስተናግዷል።
ፕሬዝደንት ጆኮ ዊዶዶ በጉዳዩ ዙሪያ የተጀመረው ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በኢንዶኔዢያ ከፍተኛ ሊግ የሚደረጉ ጨዋታዎች በሙሉ እንዲቋረጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስረው ፊሽካ መሰማትን ተከትሎ ደጋፊዎች ወደ ሜዳው ሲሮጡ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
የምስራቅ ጃቫ ፖሊስ አዛዥ ኒኮ አፊንታ እንደተናገሩት ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸውን ተከትሎ መረጋገጥ እና መታፈን አስከትሏል።
"ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ነበር። የፖሊስ መኮንኖችን ከማጥቃት ባለፈ መኪኖች ላይ ጉዳት አደረሱ" ያሉት አዛዡ ከሟቾቹ መካከል ሁለት የፖሊስ አባላት እንደሚገኙበትም ተናግረዋል።
የሚሸሹ ደጋፊዎች “ለመውጣት ወደ አንድ አቅጣጫ ሮጡ። በር አካባቢ መረጋገጥ ነበር። ሰው በመብዛቱም የትንፋሽ እና የኦክስጅን እጥረት ተከሰተ” ብለዋል።
በማህበራዊ ድር አምባ የተለቀቁ ቪዲዮዎች ደጋፊዎች በአጥር ለማምለጥ ሲሞክሩ ታይተዋል። ሌሎች ቪዲዮዎች ሕይወት አልባ ሰዎችን ሜዳ ላይ ወድቀው አሳይተዋል።
የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ የሆነው ፊፋ በፖሊሶች ወይም በሜዳ ጠባቂዎች “ብዛት ያለውን ህዝብ ለመቆጣጠር ምንም ዓይነት ጋዝ" መያዝም ሆነ መጠቀም አይቻልም ይላል።
የኢንዶኔዢያ እግር ኳስ ማህበር (ፒኤስኤስአይ) ምርመራ መጀመሩን ገልጾ ድርጊቱ የኢንዶኔዢያ እግር ኳስን ገጽታ አበላሽቷል ብሏል።
በእግር ኳስ ግጥሚያዎች ላይ የሚታዩ ብጥብጦች በኢንዶኔዥያ አዲስ አይደሉም። አሬማ እና ፐርሴባያ ሱራባያ የረዥም ጊዜ ተቀናቃኞች ቡድኖች ናቸው።
የፐርሴባያ ሱራባያ ደጋፊዎች ግጭቶች ይኖራሉ በሚል ፍራቻ የጨዋታው ትኬቶች ከመግዛት ታግደዋል።
የፀጥታ ሚንስትሩ ማህፉድ ኤምዲ 38,000 የመያዝ አቅም ባለው የካንጁሩሃን ስታዲየም 42,000 ቲኬቶች መሸጣቸውን በኢንስታግራም ላይ አስፍረዋል።
ፕሬዝዳንት ዊዶዶ ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም የሊግ 1 ጨዋታዎች እንዲቆሙ አዘዋል። ይህ በሃገሪቱ ውስጥ የመጨረሻው የእግር ኳስ አሳዛኝ ድርጊት እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።
እአአ በ1964 በሊማ በተደረገው የፔሩ እና የአርጀንቲና የኦሎምፒክ ቡኡድኖች የማጣሪያ ውድድር ላይ በተከሰተ ግጭት 320 ሰዎች ሲሞቱ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑት ቆስለዋል።
እንግሊዝ ውስጥ ደግሞ በ1989 በሼፊልድ ሂልስቦሮ ስታዲየም 97 የሊቨርፑል ደጋፊዎች ህይወታቸው አልፏል።