ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ የመለሰቻቸው ዜጎች ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ መድረሱ ተገለጸ

ከሳዑዲ የተመለሱ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

ታትሟል

ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ የመለሰቻቸው ዜጎች ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ መድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ።

ከሰሞኑ ባደረገው ውይይት አኃዙን ይፋ ያደረገው በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም የተመሰረተው ብሔራዊ ኮሚቴ ነው ። 

ከ16 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና አጋር ተቋማት የተውጣጣው ኮሚቴው እስከ ጥር 15፣ 2014 ድረስ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎች መመለሳቸውን ማስታወቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በትናንትናው ዕለት ሰኔ 19፣ 2014 ዓ.ም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል።

ኢትዮጵያ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎቿን ወደ አገራቸው የመመለስ ሥራ መጋቢት 21፣ 2014 ዓ.ም መጀመሯን ያስታወቀች ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችንም ከ7 እስከ 11 ባሉት ወራት ውስጥ ለመመለስ እቅድ ተቀምጦ ነበር።

በዚህም መሰረት ከመጋቢት 21 እስከ ሰኔ 15፣ 2014 ዓ.ም ባለው ወቅት በተደረጉ 111 በረራዎች 40 ሺህ 794 ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ብሔራዊ ኮሚቴው እስካሁን 40 በመቶ እቅዱ መሳካቱን በውይይቱ ላይ አመልክቷል።

ብሔራዊ ኮሚቴው በተከናወኑ ተግባራት እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ የተወያየ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ መጠባበቂያ ቦታዎች እንዲሁም ከሻንጣ መጓተት ጋር የተያያዙ ችግሮች ተነስተዋል።

ኮሚቴው በተለያዩ አፍሪካ አገራት የሚገኙ ዜጎች ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታም በተመለከተ መወያየቱ ተገልጿል።

በነዳጅ ምርት የበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰርቶ ለመቀየር መዳረሻ ከሚያደርጓቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ይሁን እንጂ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በተለያየ ወቅት በአገሪቱ የሥራ እና የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም በሚል በርካታ ኢትዮጵያውያን እጅግ አስቸጋሪ በሆኑና በማያፈናፍኑ እስር ቤቶች እንደቆዩና ለበርካታ የጤና እክሎች መጋለጣቸውን ቢቢሲ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

እስረኞቹ በቂ ምግብ እና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ በሕይወት ለመቆየት አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ እንደሚያዙ ይናገራሉ።

በማቆያ ማዕከላትም ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ከመቆያታቸው ባሻገር በጥበቃዎች ማሰቃየትና ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው የመብት ተቆርቋሪው ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች መግለጹ የሚታወስ ነው።

የማዕከሉ ጥበቃዎች በጎማ በተሸፈነ ብረት በፈጸሙባቸው ድብደባ ስደተኞች መሞታቸውም ተመልክቷል።