ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በዩክሬን ኒውክሌር ጣቢያ የሚገኙ የሩሲያ ወታደሮችን አስጠነቀቁ
የዩክሬን ፕሬዚዳንት በሩሲያ ይዞታ በሚገኘው የዛፖሪዝህዚያ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ የሚተኩሱ የሩስያ ወታደሮች በጸጥታ አካላት ጥቃት እንደሚደርስባቸው አስጠነቀቁ።
ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በትላንትና ምሽት ንግግራቸው በኒውክሌር ጣቢያው ላይ ሆኖ ወይም ወደ ጣቢያው የሚተኩስ የዩክሬን “ልዩ ኢላማ” ይሆናሉ ብለዋል።
በተጨማሪም ሩሲያ የኒውክሌር ጣቢያውን ወደ ጦር ሰፈር በመቀየር “ለኒውክሌር ማስፈራሪያነት” እየተጠቀመች ነው ሲሉም ከሰዋል።
ሩሲያ በመጋቢት ወር ከፍተኛ ፍልሚያ አድርጋ ጣቢያውን መቆጣጠሯ ይታወሳል።
ጣቢያው በአውሮፓ ውስጥ ትልቁ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ሲሆን በደቡባዊ ዩክሬን ኒኮፖል ከተማ ውስጥ ስትራቴጂካዊ የሚባል ቦታ ላይ ይገኛል።
ጣቢያው በሩሲያ ይዞታ ስር ቢሆንም የዩክሬን ቴክኒሻኖች አሁንም በስራ ላይ ናቸው።
በጣቢያው ላይ የሚገኙት በርካታ የዩክሬን ሰራተኞች በታጠቁ ጥበቃዎች እየተጠበቁና በፈታኝ ሁኔታ መሆናቸውን ቢቢሲ ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰራው የምርመራ ዘገባ አጋልጧል።
በዚህ ሳምንት ሐሙስ የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሩሲያ ጣቢያውን ለቃ እንድወጣ ጠይቀዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጣቢያው በከባድ መሳሪያ የተደበደበ ሲሆን ለጥቃቱም ሩሲያ እና ዩክሬንም እርስ በርስ ተወነጃጅለውበታል።
ፕሬዚዳንት ዘሌንስኪ ከመዲናዋ ኪዬቭ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ በኒውክሌር ጣቢያው ላይ በመተኮስ “የማያቋርጥ ትንኮሳዎችን” እንዳደረገች ገልፀው በዚያ የሰፈሩት የሩሲያ ወታደሮች ኒኮፖልን እና በአቅራቢያው የምትገኘውን ማርጋኔት ከተማን ለማጥቃት እንደ ጦር ሰፈር እየተጠቀሙበት ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት "እያንዳንዱ የሩስያ ወታደር በጣቢያው የተኮሳ፤ ጣቢያውን ሽፋን አድርጎ የተኮሰ በጸጥታ ኃይሎቻችን፣ በደህንነታችን እንዲሁም በሰራዊታችን ልዩ ኢላማ እንደሚሆን መረዳት አለበት “ ብለዋል።
አክለውም “ሩሲያ የኒውክሌር ጣቢያን ተቆጣጥራ መቀጠሏል በአውሮፓ ላይ የጨረር (ራዲዬሽን) ስጋትን ይጨምራል” በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።