በፈረንሳይ የነብዩ ሞሐመድን ሥዕል በማሳየቱ የተገደለው አስተማሪ የፍርድ ሒደት ተጀመረ

አስተማሪው ሳሙዔል ፓቲ

የፎቶው ባለመብት, x.com/ch_capuano

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከአራት ዓመታት በፊት ከሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ውጪ ታርዶ የተገደለው የሳሙዔል ፓቲ ፍርድ ሒደት ፓሪስ ውስጥ መታየት ጀመረ።

ከሩሲያዋ ቼቼን ግዛት የመጣው አብዱላኽ አንዞሮቭ በወቅቱ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ ቢላ በእጁ ጨብጦ ሳለ በፖሊስ መገደሉ አይዘነጋም።

የፍርድ ሒደቱ አስተማሪውን ማን ገደለው ሳይሆን እንዴት ሊገደል ቻለ የሚለውን የሚመለከት ይሆናል።

ለሚቀጥሉት ሰባት ሳምንታት የሚዘልቀው የፍርድ ሒደት እንዴት የአንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ ሕይወት በማኅበራዊ ሚድያ ምክንያት እንደተመሰቃቀለም ይመለከታል።

ፍርድ ቤት የቀረቡት አስተማሪው “የአምላክን ስም ያጎደፈ” ነው በሚል ማንነቱን በመለየት የተባበሩ ሁለት ግለሰቦች፤ ለአብዱላኽ እርዳታ ያደረጉ ሁለት ሌሎች ግለሰቦች እና ትብብር አድርገዋል የተባሉ ተጨማሪ አራት ሰዎች ናቸው።

የሳሙዔል ፓቲ ግድያ ፈረንሳይውያን ድንጋጤ ውስጥ እንዲገቡ ያደረገ ትልቅ ዜና እንደነበር አይዘነጋም።

ሳሙዔል ፓቲ በሚያስተምርበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተወዳጅነት የነበረው የታሪክ አስተማሪ እንደሆነ ይነገርለታል። ትምህርት ቤቱ ከፓሪስ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኝ ነው።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2020 ስለመናገር ነፃነት እያስተማረ ነበር። ለታዳጊ ተማሪዎቹ ይህን ርዕስ በተደጋጋሚ አስተምሯል።

በአውሮፓውያኑ 2015 ቻርሊ ሄብዶ መፅሔት የነብዩ ሞሐመድን ሥዕል አትሞ እንዴት አብዛኛው የመፅሔቱ አዘጋጆች ሊገደሉ እንደቻሉ በምሳሌ በመጥቀስ ነበር ሲያስተምር የነበረው። ለማስተማሪያ እንዲሆነው የካርቱን ሥዕሎቹን ምሥል ለተማሪዎች ሲያሳይ ነበር።

አስተማሪው ይህን ከማድረጉ በፊት ምናልባት ይህን ምሥል ማየት የማይሹ ተማሪዎች ካሉ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ጠይቆ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሚቀጥለው ቀን የ13 ዓመቷ ታዳጊ ለምን ትምህርት ቤት እንደማትሄድ በአባቷ ተጠየቀች። አስተማሪው የነብዩ ሞሐመድን እርቃን ሥዕል ሊያሳይ ስለሆነ ሙስሊም ተማሪዎች ውጡ ብሎ ሲጠይቀን በመቃወሟ መቀጣቷን ለአባቷ ተናገረች።

ነገር ግን አስተማሪው ሙስሊም ተማሪዎች ከክፍል ውጡ አላለም፤ ተማሪዋ ብትቀጣም ባለችው ምክንያት አልነበረም፤ አልፎም አስተማሪው ስለመናገር ነፃነት ትምህርት ሲሰጥ ክፍል ውስጥ አልነበረችም።

ቢሆንም በማኅበራዊ ሚድያ አማካይነት ወሬው በፍጥነት ተዛመተ።

የታዳጊዋ አባት ብራሒም ችኒና ታዳጊዋ ያለችውን ነገር በቪድዮ ቀርፆ የአስተማሪውን ስም እየጠራ በፌስቡክ ለቀቀው።

ቀጥሎ በአካባቢው ይኖር የነበረው ኢስላሚስቱ አብዱልሐኪም ሴፈሩዊ “እስልምና እና ነብዩ ሞሐመድ በሕዝብ ኮሌጅ እየተሰደቡ ነው” የሚል የ10 ደቂቃ ቪድዮ አሰራጨ።

በጥቂት ቀናት ውስጥ ትምህርት ቤቱ ከመላው ዓለም የማስፈራሪያ መልዕክት ይደርሰው ጀመር። አስተማሪው በተከፈተበት ዘመቻ ምክንያት ሕይወቱ በጣም እንደከበደ ለሥራ አጋሮቹ ተናግሮ ነበር።

ከፓሪስ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሩዌን የሚኖረው የ18 ዓመቱ ስደተኛ አብዱላኽ አንዞሮቭ ዜናውን ሰማ። ቀጥሎ አሁን ፍርድ ቤት የቀረቡትን ተከሳሾች እርዳታ ጠየቀ።

አንደኛው ግለሰብ ቢላ ሲገዛ አብሮት ነበር። ሁለተኛው ግለሰብ ደግሞ ተመሳስሎ የተሠራ ሽጉጥ ሲገዛ ተባብሮት ቀጥሎ ወደ ትምህርት ቤቱ እየነዳ ወስዶታል።

አንዲት ሴትን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ከገዳዩ ጋር ስናፕቻት እና ትዊተር በተባሉ ማኅበራዊ ሚድያዎች የተነጋገሩ ናቸው።

ተከሳሾቹ ከጉዳዩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ቢያምኑም “የሽብር ግድያ ለመፈፀም ተባብረዋል” የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉትም። ጠበቃቸው ተከሳሾቹ በግልፅ የአስተማሪውን ድርጊት ቢቃወሙም ይገደል የሚለው ሐሳብ ግን አላነሱም ይላሉ።

ታዳጊዋ ከዓመት በፊት ታዳጊዎች ፍርድ ቤት ቀርባ ሐሰተኛ ክስ በማቅረብ ተከሳ ብይን ተሰጥቶባታል። ታዳጊዋ ፍርድ ቤቱ የጣለባትን ፍርድ ተላልፋ የምትገኝ ከሆነ ወደ እስር ቤት ትላካለች።