እስራኤል 'ለመሠረታዊ ፍጆታ' የሚውል ምግብ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንደምትፈቅድ ተናገረች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል ምግብ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ካገደች 10 ሳምንታት በኋላ "ምንም የረሃብ ችግር እንዳይከሰት"፤ "መሠረታዊ መጠን ያለው ምግብ" ወደ ጋዛ እንዲገባ እንደምትፈቅድ አስታውቃለች።

የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ እንዳስታወቀው እርምጃው የተወሰደው በሃማስ ላይ ዳግም ወታደራዊ ጥቃትን መደገፍ በማስፈለጉ እና በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ምክረ ሃሳብ ነው ብሏል።

ይህ መግለጫ የወጣው የእስራኤል ጦር በመላው ጋዛ "ሰፊ የምድር ላይ ዘመቻ" መጀመሩን ከተናገረ ከሰዓታት በኋላ ነው።

እስራኤል ምንም ዓይነት ምግብ፣ ነዳጅ እና መድሃኒት ወደ ጋዛ እንዳይገባ ያደረገችውን ዕቀባ እንድታነሳ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባት ነው።

የተራድዖ ድርጅቶች በጋዛ 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል ያለውን የረሃብ አደጋ አስጠንቅቀዋል፤ የተራቡ ህፃናት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ምስሎች እና ዘገባዎችም መውጣት ጀምረዋል።

የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮት እስራኤል "አፋጣኝ፣ መጠነ ሰፊ እና ያልተደናቀፈ" ዕርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንድትፈቅድ ጠይቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት መግለጫ እንዳስታወቀው፤ "የረሃብ ችግር እንዳይከሰት እርግጠኛ ለመሆን" እስራኤል ለጋዛ ሕዝብ "መሰረታዊ መጠን ያለው ምግብ እንዲገባ" ትፈቅዳለች።

እንዲህ ያለው ሁኔታ "ኦፕሬሽን የጌዲዮን ሰረገላ" ተብሎ የተሰየመውን አዲሱን ጥቃት አደጋ ላይ ይጥላል ብሏል።

እስራኤል በተጨማሪም "ሃማስ የሰብዓዊ ርዳታ ስርጭትን ለመቆጣጠር ያለውን አቅም ለመንፈግ እርምጃ ትወስዳለች" ሲል መግለጫው አክሏል።

ቀደም ሲል እሁድ ዕለት፣ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኘውን ሆስፒታልን ጨምሮ ጥቃት ፈጽሟል።

እስራኤል በጋዛ የታገቱ ዜጎቿን ለማስለቀቅ እና ሃማስን ለማሸነፍ ዓላማ እንዳላት ተናግራለች።

በደቡባዊዋ ካን ዮኒስ ከተማ እና በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ ቤይት ላሂያ እና የጃባሊያ የስደተኞች ካምፕን ጨምሮ የእስራኤል ጥቃት ዒላማ መሆናቸውን የነፍስ አድን ሠራተኞች ተናግረዋል።

በጋዛ ባለፉት 24 ሰዓታት በትንሹ 67 ሰዎች ሲገደሉ 361 ቆስለዋል ሲል በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በቦምብ ፍንዳታዎች የምትባነንው በካን ዮኒስ የምትኖር አንዲት ሴት "በጣም አስቸጋሪ" ስትል ስለሁኔታውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

በተጨማሪም "ከከፍተኛ የዱቄት፣ የጋዝ እና የምግብ እጥረት" ጋር የታገለች መሆኑን አክላለች።

የጋዛ ዋና የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ተፈናቃዮች ተጠልለውበት የነበረው እና በደቡብ የሚገኘው የአል-ማዋሲላይ በአንድ ለሊት በደረሰ ጥቃት 22 ሰዎች ሲሞቱ 100 ሰዎች ቆስለዋል ብሏል።

ካምፑ ቀደም ሲል "ደህንነቱ የተጠበቀ ዞን" ተብሎ ተለይቷል።

የእስራኤል ጦር እንደ "የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ" በገለፀው ትእዛዝ እሁድ ዕለት "ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ በሚውል በማንኛውም ቦታ ላይ ሀይለኛ ጥቃት እንደሚሰነዝር" በመግለጽ ሰዎች "ወዲያውኑ ወደ ምዕራብ በአል-ማዋሲ ወደሚታወቁት መጠለያዎች እንዲሄዱ" አሳስቧል።

በእስራኤል የአየር ድብደባ እየተባባሰ ባለበት ወቅት ሦስት የሕዝብ ሆስፒታሎች አሁን በሰሜን ጋዛ ግዛት ውስጥ "ከሥራ ውጭ ናቸው" ሲል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በቤቴ ላሂያ የሚገኘው የኢንዶኔዥያ ሆስፒታል ከመካከላቸው በአንዱ የሕክምና ባልደረቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3፡40 አካባቢ የመከላከያ ታንኮች ከውጭ ሆነው በሆስፒታሉ ላይ እየተኮሱ ነው።

አራት ዶክተሮች እና ስምንት ነርሶችን ጨምሮ 55 ሰዎች ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል። ቀሪዎቹ ከጠዋቱ ጥቃት በኋላ ከሆስፒታል መሸሽ ያልቻሉ የማይንቀሳቀሱ ሕሙማን ናቸው ብለዋል ።

ከ50 ደቂቃ በኋላ ሠራተኞቹ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የሆስፒታሉን አካባቢ ለቅቆ መውጣቱን ተናግረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ወታደሮቹ ከኢንዶኔዥያ ሆስፒታል አጠገብ ያለውን አካባቢ ጨምሮ በሰሜናዊ ጋዛ "የአሸባሪ መሠረተ ልማት ቦታዎችን" እየተዋጉ ነው ብሏል።

እሁድ ቀደም ብሎ የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሠራተኞች እና ታካሚዎች "በከባድ ተኩስ" ውስጥ እንደነበሩ ተናግሯል። እስራኤል ሆስፒታሉን በመክበብ፣ ተደራሽ እንዳይሆን፣ እና "ሆስፒታሉን ከአገልግሎት ውጪ አድርጋለች" በማለት ክስ ሰንዝሯል።

የጤና ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከጥቃቱ በፊት ሆስፒታሉን እንዲለቁ ምንም አይነት ትዕዛዝ ወይም ማስጠንቀቂያ አልተሰጠም እና በማንኛውም ጊዜ በኢንዶኔዥያ ሆስፒታል ወታደራዊ ዒላማዎች አልነበሩም።

ጥቃቱ የመጣው ከእስራኤል እና ከሃማስ የተወከሉ ተደራዳሪዎች በኳታር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ ባለሉበት ሰዓት ነው።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጠቅሶ እንደዘገበው የእስራኤል ተደራዳሪ ቡድን በእሁድ ዕለት ስምምነት ላይ ለመድረስ "ያለውን አማራጭ" ሁሉ እየተጠቀሙ ነው።

የኔታንያሁ መግለጫ "ሁሉንም ታጋቾች መፈታትን፣ የሃማስ አሸባሪዎችን ማስወገድ እና የጋዛ ሰርጥ ትጥቅ ማስፈታትን ይጨምራል" ብሏል።

ከፍተኛ የሃማስ ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በቀጠለው የእስራኤል እምቢተኝነት ምክንያት በዶሃ እየተካሄደ ባለው ድርድር እስካሁን ምንም ለውጥ ወይም እድገት አልተገኘም።"

ምንጩ ሃማስ ሁሉንም የእስራኤል ታጋቾች በአንድ ምዕራፍ ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል "ሁሉን አቀፍ እና ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚያስችል ሁኔታ -[የእስራኤል] ተደራዳሪ ቡድናቸው ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣን ስለሌለው የእስራኤል ወገን ውድቅ ማድረጉን ቀጥሏል።"

ምንጩ ሃማስ "ማንኛውም ከፊል ወይም ጊዜያዊ ስምምነቶችን እንደማይቀበል" አፅንዖት ሰጥቷል።

ቡድኑ ስምምነት በተደረሰበት መጠን የፍልስጤም እስረኞች እንዲፈቱ፣ እስራኤላውያን ከጋዛ ሰርጥ ሙሉ ለሙሉ ለቅቀው ለመውጣት እና ሰብዓዊ ርዳታ እንዲገቡ ለማድረግ ሁሉንም ታጋቾች የመልቀቅ ሃሳብ አቅርቧል።

"እስራኤል ለጊዜያዊ የተኩስ አቁም ታጋቾቿን በአንድ ወይም በሁለት ቡድን መልሶ ማግኘት ትፈልጋለች" ሲል የሃማስ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በሰሜን ጋዛ የሚገኘው የአል-አውዳ የግል ሆስፒታል ዳይሬክተር መሀመድ ሳልሃ እሁድ እለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኢንዶኔዥያ ሆስፒታል መዘጋቱ ሊሰጥ በሚችለው ህክምና ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል።

አል-አውዳ ለኦክስጂን ማከማቻ እና ለፅኑ ሕክምና ክፍሉ የኢንዶኔዥያ ሆስፒታል ላይ ጥገኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ሠራተኞቻቸው ተቋሙን በፍጥነት ለመጠገን እየሞከሩበት ባለቡት ወቅት በአንድ ጀምበር በሆስፒታሉ አቅራቢያ የቦምብ ጥቃት ደርሶ "ብዙ ጉዳት" አድርሷል ሲሉ አክለዋል።

በካን የኑስ የሚገኙት ሁለት ግዙፍ የሕክምና ማዕከላት፤ የናስር ሜዲካል ኮምፕሌክስ እና የአውሮፓ ሆስፒታል በቅርቡ በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ሆስፒታሎች ናቸው።

ሃማስ በአውሮፓ ሆስፒታል ስር የማዘዣ እና የቁጥጥር ማዕከልን በመደበቅ የከሰሰችው እስራኤል፤ "በሃማስ አሸባሪዎች" ላይ "ትክክለኛ ጥቃት" ማድረሷን ተናግራለች።

የእስራኤል ሚዲያ እንደዘገበው የጥቃቱ ዋና ዒላማ የሃማስ ከፍተኛ ባለስልጣን መሀመድ ሲንዋር - የጋዛ የቀድሞ የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ታናሽ ወንድም ነው።

እአአ መጋቢት 18 ቀን እስራኤል ጥቃቷን እንደገና ከጀመረች በኋላ ለሁለት ወራት የቆየው ደካማ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረስ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

የእስራኤል ጦር ዘመቻውን የማስፋፋት ዓላማ ታጋቾችን ለመልቀቅ እና "ሃማስን ማሸንፍ" ጨምሮ "የጦርነቱን ዓላማዎች በሙሉ ለማሳካት" ያለመ ነው ብሏል።

ነገር ግን የታጋቾቹ ቤተሰቦች ኦፕሬሽኑ አሁንም በጋዛ ውስጥ ባሉ ታጋቾች ላይ "ከባድ እና አሳሳቢ አደጋ" እንዳለው ይናገራሉ።

"የተለቀቁት ታጋቾች የሚሰጡት ምስክርነት ወታደራዊ ጥቃቶችን ተከትሎ የከፋ አያያዝን፣ አካላዊ ጥቃትን፣ መገደድን እና የምግብ ቅነሳን ጨምሮ ይገልጻሉ" ሲል የታገቱት እና የጠፉ ቤተሰቦች ፎረም ተናግሯል።

ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ሃማስ በደቡብ እስራኤል ላይ በጥቅምት 7 2023 ባደረሰው ጥቃት ሲሆን ይህም ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ሲገደሉ ከ250 በላይ የሚሆኑት ታግተዋል።

በጋዛ 58 ያህል ታጋቾች የቀሩ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ እስከ 23 ያህሉ በህይወት እንዳሉ ይታመናል።

እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ከ53 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።