ጎርፍ የምጣኔ ኃብት ድቀት ያስከተለባት ፓኪስታን እርዳታ እንዲደርስላት ጥሪ አቀረበች  

ታትሟል

ጎርፍ በመላ ሃገሪቱ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ እርዳታ እንዲደረግላት ፓኪስታን ጠየቀች።

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ሌሎችም ለአደጋ ጥሪ አስተዋፅኦ ቢያደርጉም ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከሰኔ ወር ጀምሮ ከ1ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል ሲሉ ሳልማን ሱፊ ተናግረዋል።

የፓኪስታን መንግስት ሰዎችን ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው ብለዋል።

በሃገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ በምትገኘው በካይበር ፓክቱንክዋ ግዛት ወንዞች ሞልተተው በመፍሰሳቸው በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ሸሽተዋል።

"ለዓመታት ለፍተን የሠራነው ቤት ዓይናችን እያየ መስጠም ጀመረ። መንገዱ ዳር ተቀምጠን ቤታችን ሲሰምጥ ተመለከትን" ሲል የ23 አመቱ ጁናይድ ካሃን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግሯል።

በሃገሪቱ ደቡብ ምስራቅ የሚገኘው የሲንዲ ግዛትም ክፉኛ ተጎድቷል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ሳልማን ሱፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሀገሪቱ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ትፈልጋለች።

"ፓኪስታን ከኢኮኖሚያዊ መጎዳት ጋር ስትታገል ቆይታለች። ችግሩን ልናልፍ ነው ስንል  ይህ አደጋ ተከሰተ” ብለዋል።

ለበርካታ የልማት ፕሮጀክቶች የተመደበው ገንዘብ ለተጎዱ ሰዎች እንዲደርስ ተደርጓል ብለዋል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ እንዳሉት 33 ሚሊዮን ሰዎች (ከጠቅላላው ህዝብ 15 በመቶ የሚሆን ነው ) በጎርፍ ተጎድተዋል።

የዘንድሮው የጎርፍ አደጋ አእጅግ የከፋው ነው ከተባለለት የ2010/2011 አደጋ ጋር የሚነጻጸር ነው ብለዋል።

የሃገሪቱ ባለስልጣናት ለደረሰው ውድመት የአየር ንብረት ለውጥን ተጠያቂ እድርገዋል።

ቤቶችን ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከመገንባት ጨምሮ ከዚህ ቀደም ደካማ መንግስታዊ ዕቅድም ለጉዳቱ በምክንያትነት ሲጠጠቀስ ቆይቷል።