የአማዞኑ ባለቤት ለዶሊ ፓርተን 100 ሚሊዮን ዶላር ሊሰጣት ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ለዝነኛዋ የካንትሪ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዶሊ ፓርተን የ100 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አበረከተ።
የባለሃብቱ የትዳር አጋር ላውረን ሳንቼዝ ሙዚቀኛዋን ''በሁሉም የስራዋ አቅጣጫ በፍቅር እና በአዛኝነት የምትመራ ሴት'' ሲሉ ገልጸዋታል።
ቤዞንስ ከረጅ ኤንድ ሲቪሊቲ አዋርድ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ሽልማት ''መፍትሄዎችን በድፍረት እና በሰለጠነ መልኩ'' ለሚፈልጉ መሪዎች የሚበረከት ነው።
ሳንቼዝ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ''በዚህ 100 ሚሊዮን ዶላር የምታደርጊውን ነገር ለማየት እንጓጓለን'' ሲሉ ገልጸዋል።
''ዋው 100 ሚሊዮን ዶላር ነው ያላችሁት?'' ስትል ዶሊ ፓርተን የሽልማት ስነስርዓቱን ስትል ተደምጣለች።
''ሌሎችን ለመርዳት በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ገንዘባቸውን ልባቸው ያለበት ቦታ ላይ ማዋል አለባቸው። በዚህ ገንዘብ መልካም ነገሮችን ለማድረግ እሞክራለሁ'' ስትል ዶሊ ፓርተን ተናግራለች።
እአአ በ2001 የጀመረው ይህ ሽልማት በወቅቱ በመላው ዓለም በከባድ የምግብ እጥረት ውስጥ ላሉ ሰዎች ምግብ ለሚያቀርበው ሴንትራል ኪችን ለተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት መስራቾች ነበር የተበረከተው።
ዘፋኝ፣ የግጥም እና ዜማ ጸሃፊ፣ ተዋናይት፣ የንግድ ሰው ብሎም በጎ አድራጊ የሆነችው ዶሊ ፓርተን በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ወቅት ከፍተኛ ዘመቻዎችን በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
ሞደርና የተሰኘው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ በኮሮናቫይረስ ላይ ለሚያካሂደው ዘመቻ የ1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋ እንደነበረ ይታወሳል።












