ትራምፕ ዛቻና ማስፈራሪያ አደረሱብን ያሉ ባለሥልጣናት ቃላቸውን ሰጡ

ታትሟል

ባለፈው ዓመት የአሜሪካን ምርጫን ተከትሎ በተነሳው የካፒቶል ሒል ነውጥ ትራምፕን ተጠያቂ ለማድረግ ምርመራ እየተደረገ ነው፡፡

የመርማሪ ቡድኑ ትናንት ምሽት አራተኛ ዙር ምስክሮችን አዳምጧል፡፡

ይህ ለአሜሪካ ሕዝብ በቀጥታ የተላለፈው የምርመራ ሂደት አራት የቀድሞ የምርጫ ሠራተኞችን ቃል ያሰማ ነበር፡፡

የምርመራ ቡድኑ ሥራ ዶናልድ ትራምፕ ከዓመት በፊት በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ መሞከራቸውን፣ እንዲሁም የካፒቶል ሒል ነውጥ በርሳቸው ቀጥተኛ ትዕዛዝ ስለመፈጸሙ መረጃ መሰብሰብ ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ ላለፉት 12 ወራት በሺህ የሚቆጠሩ የጽሑፍ፣ የስልክና የቪዲዮ ሰነዶችን በማገላበጥ፣ የዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ረዳቶችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ሥራ ተጠምዶ ነበር፡፡

ትናንትና ለአራተኛ ዙር በተሰማው የምስክሮች ቃል ከትራምፕና ከቅርብ ረዳቶቻቸው እንዲሁም ከደጋፊዎቻቸው የሞት ማስፈራሪያ የደረሳቸው የምርጫ ሠራተኞችን ባለሥልጣናት ምስክርነት ተሰምቷል፡፡

"የግድያ ዛቻ ደርሶብኛል"

የአሪዞና ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት ረስቲ ባወርስ የመጀመርያ ቃል ሰጥተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት ከትራምፕ ሰዎች የሚደርስባቸው ዛቻና ማስፈራሪያው ዛሬም ድረስ የቀጠለ ነው፡፡

በተለይም በትናንትናው ምሽት የተሰሙት ምስክሮች ጆርጂያና አሪዞና ግዛት ላይ በምርጫ አስፈጻሚነት የሠሩ ኃላፊዎች ነበሩ፡፡

ሁለቱ ግዛቶች ዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ተጭበርብሮብኛል ብለው ተደጋጋሚ ክስ ሲያቀርቡባቸው የነበሩ በተለምዶ ሪፐብሊካኖች የሚያሸኑፉባቸው ናቸው፡፡

ሆኖም ከቆጠራ በኋላ በነዚህ ግዛቶች ባይደን በማሸነፋቸው ትራምፕ እጅግ ተቆጥተው እንደነበረ ምስክርነት ተሰምቷል፡፡

"ከ20ሺህ በላይ ማስፈራሪያ ኢሜሎችና የድምጽ መልእክቶች ይደርሱን ነበር፡፡ ሥራ መሥራት እስኪያቅተን ድረስ" ሲሉ ተናግረዋል የአሪዞና አፈ ጉባኤ ሚስተር ባውረስ፡፡

የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ቤታቸው ድረስ መጥተው ዛቻና ማስፈሪያ ያደርሱባቸው እንደነበረው መስክረዋል፡፡

በተለይም የዶናልድ ትራምፕ ጠበቃ የነበሩት ሩዲ ጁሊያኒ “ምርጫውን ትራምፕ እንዲያሸንፉ ካላደረክ ዘብጥያ እንድትወርድ እናደርጋለን፤ ባንተ ላይ ብዙ የወንጀል መላምቶች አሉ፤ መረጃዎችን ይዘናል ማስረጃ ነው የሚቀረን” እያሉ ይዙቱብኝ ነበር ብለዋል፡፡

በዚህ የትናንት ምሽቱ ምርመራ ሻዬ ሞስ የተባለች የጆርጂያ ምርጫ አስፈጻሚና እናቷ ሩቢ ፍሪማን ቀርበው ነበር፡፡

ሻዬ ሞስ እንባ እየተናነቃት ከትራምፕ የቅርብ ሰዎች ማስፈራሪያ ይደርሳት እንደነበረ ለኮሚቴው አስረድታለች፡፡

‹‹ለእናቴ ብቸኛ ልጅ ነኝ፣ በዚያ ላይ እናቴንም ዶናልድ ትራምፕ በስም እየጠሩ ያስፈራሯት ነበር፤ እጅግ ፈታኙን የሕይወቴን ክፍል ነው ያሳለፍኩት›› ስትል ለኮሚቴው አስረድታለች፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሚዲያ ወጥተው በጆርጂያ እናትና ልጅ ተመሳጥረው ምርጫ ሲያጭበረብሩ ተደርሶበታል በሚል የእናቷን ስም በመጥቀሳቸው ሕይወታቸው ምስቅልቅሉ እንደወጣም አብራርታለች፡፡

‹‹ስሜን፣ ዝናዬን፣ ሥራዬን፣ ደኅንነቴን ሁሉ በትራምፕ የተነሳ አጥቻለሁ›› ያሉት ደግሞ የሻዬ ሞስ እናት ሚስ ፍሪማን ነበሩ፡፡

‹‹ለመሆኑ አንድ ፕሬዝዳንት ድንገት ተነስቶ ስማችሁን ጠርቶ ሲዝትባችሁ ምን እንደሚሰማችሁ ታውቃላችሁ?" ሲሉም ሕይወታቸው እንዴት ቀውስ ውስጥ እንደገባ አስረድተዋል፡፡

የትራምፕን ዛቻ ተከትሎ እናትና ልጅ ለዚህ አጣሪ ኮሚቴ እንዴት የሞት ዛቻ ይደርሳቸው እንደነበረ፤ ከቤት መውጣት ስላቆሙ የሰውነት ክብደታቸው እንዴት እንደጨመረ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻ ምሥክርነት የሰጡት የጆርጂያ ምርጫ አስፈጻሚ ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩት ጋብሬል ስተርሊንግ ናቸው፡፡

 እኚህ ምስክር ትራምፕ ነጋ ጠባ እየደወሉ ጆርጂያ ግዛትን እንዲያሸንፉ የተወሰነ ድምጽ እንዲተባበሯቸው በቀጥታና በተዘዋዋሪ ይጠይቋቸው እንደነበር መስክረዋል፡፡

ይህን ለማድረግ ሕሊናቸው እንደማይፈቅድላቸው በተናገሩ ጊዜ ደግሞ ትራምፕና ጠበቃቸው ጁሊያኒ ከፍተኛ ዛቻ ያደርሱባቸው እንደነበር አብራርተዋል፡፡

በጆርጂያ ግዛት 10ሺህ 315 የሞቱ ሰዎች ድምጽ ለጆ ባይደን ሰጥተዋል በሚል ዶናልድ ትራምፕ ውጤቱን አልቀበልም ብለው ነበር፡፡

እኚህ ምስክር እንደተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ቁጥር በመጥቀስ የምርጫ ውጤቱን ለርሳቸው እንዳደርገው ይወተውቱኝ ነበር ብለዋል፡፡

ይሁንና ባደረግነው ማጣራት አራት ሰዎች ብቻ ነው ያገኘነው ብለዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ግን ይህን ባለመቀበል ምርጫው ወደርሳቸው እንዲያደላ በየዕለቱ ማስፈራሪያ ያደርጉባቸው እንደነበረ፣ ይህም ለሕይወታቸው አስጊ ደረጃ እየደረሰ እንደመጣ በስፋት አስረድተዋል፡፡

መርማሪ ኮሚቴው የትራምፕ ምክትል የነበሩትን ማይክ ፔንስን ጨምሮ በርካታ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ምስክርነትን ሰምቷል።

በተለይም የቀድሞ የአሜሪካ አቃቢ ሕግ ሚስተር ቢል ባር “ትራምፕ መሸነፋቸውን ብንነግራቸውም ሊቀበሉ ያልቻሉት አእምሯቸው ከእውኑ ዓለም ጋር ተጣልቶ ስለነበር ነው” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ይህ አጣሪ ኮሚቴ ከዚህ ሁሉ ምርመራ በኋላ ትራምፕ እንዲከሰሱ የማድረግ ሥልጣን የለውም፡፡ ሆኖም ለአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት መረጃዎቹን በመስጠት የክስ ምክረ ሐሳብ ሊሰጥ ይችላል ተብሏል፡፡

አንዳንድ ሪፐብሊካኖች በበኩላቸው የኮሚቴው ዋና ዓላማ የአሜሪካ ሕዝብን ከዓመት በፊት ምን እንደተፈጠረ በማስታወስ በቀጣይ የሚደረገውን የሚድተርም ምርጫ ዲሞክራቶች እንዲያሸንፉ ማገዝ ነው ሲሉ ይከሳሉ፡፡