ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራዊው 26 ሰዎችን በአነስተኛ ጀልባ በማጓጓዝ በእንግሊዝ ፍርድ ቤት እስራት ተፈረደበት
ጀማል አብደላ የተባለ ኤርትራዊ ስድስት ልጆችን ጨምሮ 26 ሰዎችን የያዘ አነስተኛ ጀልባ ወደ ኬንት የባሕር ዳርቻ በመንዳቱ የ18 ወራት እስራት ተፈረደበት።
የ32 ዓመቱ ጀማል በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 25 ፈቃድ ሳይኖረው ባሕር በመሻገር "የሌሎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል" በሚል ተከስሶ፣ ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።
ኤርትራዊው ተከሳሽ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ወደ ጀልባው ሲቀርቡ ጀልባውን እየነዳ የነበረው እሱ መሆኑን ለመደበቅ ሞክሯል ተብሏል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ግለሰቡ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ የእንግሊዝ ቻናልን በማቋረጥ "የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል" በሚል ከተያዙት አንዱ ነው።
ባለፉት አራት ወራት 20 ትንንሽ ጀልባዎች እንደተያዙ ተገልጿል።
ዐቃቤ ሕግ ማቲው ፓሪስ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት ተከሳሹ ጀልባውን እየነዳ ሳለ የፈረንሳይ የጸጥታ ኃይሎች ሲከታተሉት ነበር።
"ባርኔጣ አድርጎ ቦታ በመቀየር በጀልባው መሃል ላይ ገብቶ" እንደነበር ዐቃቤ ሕጉ ገልጸዋል።
ጀልባው ጂፒኤስ፣ ካርታ እንዲሁም የአደጋ ጊዜ መብራቶች እንደሌሉት ተገልጿል።
ሰዎቹን ለማጓጓዝ የተጠቀመው ጥቁር፣ በአየር የሚሞላ ጀልባ ነው።
ተከሳሹ የእንግሊዝ ቻናልን ለማቋረጥ 800 ዩሮ እንደከፈለ ለፖሊስ እንደተናገረም ተገልጿል።
በተጨማሪም ከጀልባው ካፒቴን አጠገብ ተቀምጦ እንደነበር እና ጀልባውን ለመንዳት እንደተገደደ ተናግሯል።
የተከሳሽ ጠበቃ ፍራንቼስካ ሃሌት እንደተናገሩት ግለሰቡ በጦርነት ከታመሰችው ኤርትራ "ማምለጥ" የቻለው በልጅነቱ ነው።
መጀመሪያ ላይ ወደ አዲስ አበባ ቢሄድም ኤርትራዊ በመሆኑ እንደታሰረ ጠበቃዋ ተናግረዋል።
በሱዳን እና በግብፅ በኩል ወደ ሊቢያ ከተጓዘ በኋላ በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተይዞ ለስምንት ወራት እንደተሰቃየ እና ከዚያም እንደተለቀቀ ገልጸዋል።
ወደ ጣሊያን እና ፈረንሳይ ቢያቀናም ሁለቱም አገራት "ለስደተኞች ምቹ እንዳልነበሩ" አክለዋል።
"እንግሊዝ የተሻለች አማራጭ እንደሆነች ተሰምቶት ነበር" ሲሉም ጠበቃዋ ተናግረዋል።
ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ጄምስ ብሮሚጅ እንዳሉት ተከሳሹ እስር ጊዜውን ሲያጠናቅቅ ከአገር ይባረራል።
የድንበር ደኅንነት እና የጥገኝነት ሚኒስትር አና ተርሊ ኤርትራዊውን "ኃላፊነት የጎደለው ወንጀለኛ" ሲሉ የገለጹ ሲሆን መታሰሩም "ተገቢ ነው" ብለዋል።