ዋይት ሐውስ የበሽታዎች መከላከያ ኃላፊን ሲያባርር ሌሎች የጤናው ዘርፍ ባለሥልጣናት ደግሞ ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ

ዶ/ር ሱዛን ሞናሬዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ሱዛን ሞናሬዝ ባለፈው ሐምሌ ነበር የሲዲሲ ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ዋይት ሐውስ የአገሪቱን የበሽታዎች መቆጣጠር እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ኃላፊ ዶ/ር ሱዛን ሞናሬዝ ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ አሻፈረኝ ማለታቸውን ተከትሎ ማባረሩን አስታወቀ።

ቢሮው ባወጣው መግለጫ የሲዲሲ ኃላፊ "ከፕሬዝዳንቱ አጀንዳ ጋር ባለመጣጣማቸው" ምክንያት ከተቋሙ ኃላፊነታቸው እንደተነሱ ገልጿል።

የአሜሪካ ጤና ሚኒስቴር የኃላፊዋን ሥራ መልቀቅ ቀደም ብሎ ማሳወቁን ተከትሎ የዶ/ር ሞናሬዝ ጠበቆች ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው እንዳልተነገራቸው እና ከሥራቸውም በፈቃዳቸው እንደማይለቁ ተናግረዋል።

ጠበቆቹ ኃላፊዋ "ሳይንሳዊ ያልሆኑ፣ ግዴለሽ መመሪያዎች ተፈፃሚ እንዳይሆኑ እና ትጉ የጤና ባለሙያዎችን ለማባረር ባለመተባበራቸው" ኢላማ ተደርገዋል ብለዋል።

የጤና ሚንስትር የሆኑት ሮበርት ኤፍ ኬነዲ ጁኒየር "የሕብረተሰብን ጤና እንደ መሣሪያ" እየተጠቀሙ ነውም ሲሉ ከሰዋል።

ዋይት ሐውስ ረቡዕ እለት የዶ/ር ሞናሬዝን ጠበቆች መግለጫ በመጥቀስ "ሱዛን ሞናሬዝ ከፕሬዝዳንቱ አጀንዳ ጋር አይሄዱም" ሲል ከሥራቸው መሰናበታቸውን አስታውቋል።

የፌደራል መንግሥቱ የረጅም ጊዜ ተመራማሪ የነበሩት ዶ/ር ሱዛን ሲዲሲን ለመመምራት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእጩነት ከቀረቡ በኋላ ባለፈው ሐምሌ ነበር ሹመታቸው የፀደቀው።

ዶ/ር ሞናሬዝ ለእጩነት የቀረቡት የትራምፕ የመጀመሪያ ምርጫ የቀድሞው የሪፐብሊካን የምክር ቤት አባል ዴቭ ዌልደን ክትባት ላይ እና ኦቲዝምን በሚመለከት ያላቸው እይታ ውዝግብ ካስነሳ በኋላ ነው።

ዶ/ር ሱዛን ሞናሬዝ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው በጤና ሚኒስቴሩ በኩል ይፋ ከሆነ በኋላ ወዲያውኑ ሦስት የሲዲሲ ከፍተኛ መሪዎች ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል።

ከእነዚህም መካከል ክትባትን በሚመለከት የጨመረው ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት አደገኛነነቱን በደብዳቤ ያሳሰቡት የሜዲካል ኃላፊ ዴብራ ሆሪ ይገኙበታል።

ኃላፊዋ የተቋሙን በጀት ለመቀነስ የተያዘውን እቅድም የተቃወሙ ናቸው።

ዳንኤል ጀሪንገን እና ዲሜትሪ ዳስካልስኪ የተባሉ ከፍተኛ ኃላፊዎችም በጤናው ዘርፍ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመጥቀስ ሥራቸውን ለቀዋል።

የከፍተኛ ኃላፊዎቹ ሥራ መልቀቅ የጤና ባለሙያዎች በክትባት በማያምኑት ኬኔዲ መሪነት የተቋሙን በሽታ የመከላከል አካሄድ በሚመለከት ስጋታቸውን እየገለፁ ባለበት ወቅት የመጣ ነው።

ረቡዕ እለት የአገሪቱ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር አዲስ የኮቪድ ክትባትን ማን መውሰድ እንዳለበት በመገደብ አፅድቋል።

ክትባቱን ሁሉም አዋቂ ሰዎች ማግኘት የሚችሉ ቢሆንም ከበሽታው ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች የሌለባቸው ወጣቶች እና ሕፃናትን ግን ያገለለ ነው።

ዶ/ር ሞናሬዝ በ50 ዓመታት ውስጥ የሜዲካል ድግሪ የሌላቸው የመጀመሪያዋ የሲዲሲ ኃላፊ ናቸው።

የትምሕርት ልምዳቸው የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ላይ ነው።

በወሩ መጀመሪያ የቀድሞ እና የአሁን የተቋሙ ሠራተኞች ለሕዝብ እይታ በዋለ ደብዳቤ የጤና ሚኒስትሩ ኬነዲ በፀረ ክትባት ንግግራቸው የጤና ባለሙያዎች ላይ ጥቃት እያነሳሱ ነው ሲሉ ከሰዋል።

የዶ/ር ሞናሬዝ ከሥራ መሰናበት የመጣው ተቋሙ 600 ሠራተኞችን ማባረሩን የሠራተኛ ማኅበር ባሳወቀ በሳምንት ውስጥ ነው።