በኦስካር ሽልማት ስለሚሰጠው ቅርጽ ትርጉም እና ምንነት ስድስት ነጥቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
95ኛው የኦስካር ሽልማት ሥነ ሥርዓት ከስድስት ሳምንታት በኋላ ይከናወናል።
በተለያየ ዘርፍ አሸናፊ ለሚሆኑ የፊልም ባለሙያዎች የሚሰጠው የወርቅ ቅርጽ ሽልማት ነው።
ለመሆኑ ስለዚህ ቅርጽ ምን ያህል ያውቃሉ? ስድስት ነጥቦችን እንዲህ እናስቃኝዎ።
ስለ ስሙ- በተለምዶ ኦስካር የምንለው ‘አካዳሚ አዋርድ’ የሚል መጠሪያ ያለው ዝነኛ ሽልማት ላይ የሚሰጠው ወርቃማ ቅርጽ ሽልማት ‘አካዳሚ አዋርድ ሜሪት’ ይባላል።
ስሙ እንዴት እንደተሰጠው ባይታወቅም፣ የአካዳሚው የቤተ መጻሕፍት ሠራተኛ የሆነችው ማርጋሬት ሄሪክ ቅርጹን ስታየር “አጎቴ ኦስካርን” ይመስላል ካለች በኋላ ይህ ስም እአአ በ1939 እንደተሰጠው ይነገራል።
ስለ አሠራሩ- ይህ ቅርጽ የተሠራው ከወርቅ ሳይሆን ከነሐስ ሲሆን በ24 ካራት ወርቅ ይጌጣል። በሦስት ወር ውስጥ 50 ቅርጽ ይሠራል።
ስለ ዋጋው- ይህ ቅርጽ እንዲሁ ገበያ ላይ ቢቀርብ የሚያወጣው 10 ዶላር ነው። እአአ በ2015 ተቋሙ የኦስካር ሽያጭን ለማስቆም መሞከሩን ተከትሎ ግን ዋጋው ወደ 79,200 ዶላር ደርሷል።
በ1951 የወጣ ሕግ እንደሚለው የኦስካር አሸናፊዎች ወይም ቤተሰቦቻቸው መጀመሪያ ላይ ሽልማታቸውን ለተቋሙ በ10 ዶላር ለመሸጥ ሳይጠይቁ ለሌላ ወገን መሸጥ አይችሉም።
ስለ ስርቆት- በ2000፣ 55 የሽልማቱ ቅርጾች ወደ ሥነ ሥርዓቱ እየተወሰዱ ሳለ ተሰርቀዋል። 52ቱ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ተገኝተዋል።
በተሰረቁት ምትክ ሌሎች ቅርጾች ስለቀረቡ አሸናፊዎቹ ሽልማታቸው አልቀረባቸውም።
በጦርነት ወቅት- በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የብረት እጥረት ስለነበር ለሦስት ዓመታት በፕላስቲክ ነበር የተሠራው።
ስለ መጠኑ- እያንዳንዱ የኦስካር ሽልማት 35 ሴንቲ ሜትር ነው ርዝመቱ። አራት ኪሎ ግራምም ይመዝናል። የተዋጊ ምሥል ያለው ሲሆን የቆመባቸው አምስት ቅርንጫፎች አምስቱን ዋነኛ የአካዳሚ ዘርፎች ማለትም ተዋንያን፣ አዘጋጆች፣ ፕሮዲውሰሮች፣ ቴክኒሻኖች እና ጸሐፊዎች ይወክላሉ።












